በሞጆ ጉሙሩክ ወደብ የጉሙሩክ ስነ ስርአት ሂደቱን ሳይጠብቁ ከውጭ ሃገር የገቡ 68 ኮንቴነር እቃዎች ተሸጠው 82 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ታክስና ቀረጣቸው ገቢ ተደረገ።
በጨረታ ከተወገዱት እቃዎች መካከል ኤሌክትሮኒክስ፣ የፋብሪካ ጥሬ እቃዎችና የግንባታ ግብአቶች የሚገኙበት ሲሆን፥ እቃዎቹ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ሃገር ገብተው በቀነ ገደባቸው ያልተነሱ ናቸው ተብሏል።
የሞጆ ጉሙሩክ ቅርንጫፍ የጉሙሩክ ኦፕሬሽን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ግርማ በንቲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ለእቃዎቹ ባለቤቶች ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ እቃዎቹን ባለማንሳታቸው ተሸጠው ታክስና ቀረጡ ለመንግስት ገቢ ተደርጓል ብለዋል።
በዚህ መልኩ በአሁኑ ወቅት የጉሙሩክ ስነ ስርአት ሂደቱን ያልጠበቁ 752 ኮንቴነር እቃዎች ከወደቡ የሚነሱበት ቀነ ገደብ በማለፉ በጨረታ ተወግደው ታክስና ቀረጣቸውን ለመንግስት ገቢ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
(ኢ ፕ ድ)