“ … ግብርና ወደ ሜካናይዜሽን ማስገባት በግብርና ምርቶች ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለመከላከል ወሳኝ ሚና ይኖረዋል”

የአማራ ክልል ምክር ቤት በ5ኛ ዙር 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 17ኛ መደበኛ ጉባዔ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ከሰሞኑ ጠንከር ያለ የውሳኔ ሃሳብ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡ አብመድ የአስፈፃሚ አካላት ውሳኔ አተገባበር ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ በባሕር ዳር ከተማ በገበያ ማዕከላት እና በኅብረት ሥራ ማኅበራት ቅኝት አድርጓል፡፡

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች በየደረጃው ከሚገኙ ባለሙያዎች፣ የጸጥታው አካላትና የሥራ ኀላፊዎች ጋር በመሆን የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር እየሠራ መሆኑን ከቢሮዉ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

ወይዘሮ የዝባለም መሉነህ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው። ሽምብጥ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበር ለዕለት ፍጆታ የሚሆኑ ዕቃዎችን ሲሸምቱ ነበር ያገኘናቸው። ወይዘሮ የዝባለም መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፤ አሁንም የዋጋ ንረቱ እንደቀጠለ ነው ብለዋል፡፡ በርካታ ሥራ የለላቸውና አነስተኛ የደሞዝ ተከፋይ ዜጎች በሚኖሩባት ሀገር መንግሥት ገበያውን በመቆጣጠር ሰው በልቶ የሚያድርበትን ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ነጋዴዎችም የዋጋውን ዝርዝር በግልፅ በመለጠፍ ለተጠቃሚዎች በአግባቡ መሸጥ እንዳለባቸው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የሽምብጥ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አያሌው ንጉሥ እንደገለጹት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ገበያን ለማረጋጋት በመንግሥት ድጎማ የሚቀርቡትንና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወቅቱን ባገናዘበ ዋጋ ለተጠቃሚዎች እየሸጡ ናቸው፡፡ መንግሥት በድጎማ የሚያቀርባቸውን የዘይትና የስኳር ምርቶች የትራንስፖርት ተመን በመጨመር እየሸጡ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ የኅብረት ሥራ ማኅበሩ ለአባላቱ አንድ ሊትር ዘይት በ44 ብር፣ አንድ ኪሎ ስኳር በ29 ብር እየሸጠ መሆኑን አቶ አያሌው ተናግረዋል፡፡ የኅብረት ሥራ ማኅበራቸው ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ባወጣው የዋጋ ተመን መሠረት ነጭ ጤፍ በኩንታል 3 ሺህ 917 ብር እየሸጡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የጣና ክፍለ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፍሰሃ እመኜ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የዋጋ ንረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄዱ የክልሉ መንግሥት ሸማቾች እንዳይጎዱ መሠረታዊ የግብርና ምርቶች ላይ የዋጋ ተመን ወጥቶላቸው ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎችና የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት “የዋጋ ተመን ከመውጣቱ በፊት ሊነገረን ይገባል” ብለው ላነሱት ጥያቄ ከዚህ በፊት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይትና መግባባት ላይ መደረሱን ኀላፊው አስገንዝበዋል፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማኅበረሰቡን እንዲያገለግሉ በመንግሥት ነፃ የመሥሪያና መሸጫ ቦታ የቀረበላቸው፣ ተዘዋዋሪ የብድር አገልግሎት የሚሰጣቸውና ልዩ ልዩ ምርቶችን ሲያስገቡ ከጨረታ ነፃ ሆነው እንዲያስገቡ የተፈቀደላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም የክልሉ መንግሥት ያወጣውን የዋጋ ተመን መተግበር ግዴታ እንዳለባቸውም አስረድተዋል፡፡

ኀላፊው ማኅበራት ሲቋቋሙ የተሰጣቸውን ኀላፊነት መወጣት እንጂ የግለሰቦች መክበሪያ መሆን እንደሌለባቸውም አስገንዝበዋል።

በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ካሱ ኃይሉ እንዳስረዱት አቅርቦቱ ለፍላጎት መልስ መስጠት ሳይችል ሲቀር የአግልግሎቶች ዋጋ ይጨምራል፤ የኑሮ ውድነትም ይከሰታል፤ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ኑሮውን ለመቋቋም ይከብዳቸዋል፡፡ እንደ ምሁሩ ማብራሪያ የዋጋ ንረቱ ምክንያት ዜጎች በቀጣይ በሚኖረው የገበያ ሁኔታ መለዋወጥ ምክንያት እህል ገዝተው ያከማቻሉ፡፡ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች በአግባቡ ማኅበረሰቡን ማገልገል ሲገባቸው የተለያዩ ምርቶችን ከዝነው ያስቀምጣሉ፤ የሕግ ማስከበር ዘመቻን ተከትሎና በተለያዩ ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎች ከሥራ ውጭ መሆን፣ የአምበጣ መንጋ መከሰትን ለዋጋ መናሩ ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ምሁሩ ነፃ ገበያ ሥርዓት የሚሠራባቸው ተቋማዊ አሠራሮች (ሕጎች) ጠንካራ አለመሆን፣ ሰፋፊ የእርሻ ሥራዎች አለመኖር፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉን አለማሳደግ፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ደካማ መሆን፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት አለመቻል፣ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረ የሠላም እጦት ምርቶች ከቦታ ቦታ አለመዘዋወራቸውና ሌሎችም በአሁኑ ወቅት ለተከሰተው የዋጋ ንረት እንደምክንያት የሚጠቀሱ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ “የዋጋ ንረቱም የሁሉንም ቤት የሚያንኳኳ ነው” ብለዋል የምጣኔ ሀብት ምሁሩ፡፡

መንግሥት የአጭርና የረጅም ጊዜ የመፍትሔ አማራጮችን ሊያስቀምጥ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ከአጭር ጊዜ መፍትሔም የንግዱን ማኅበረሰብ በማወያየት ለሚደረጉ ግዳጆች ግንዛቤ መፍጠር፣ ብዛት ያላቸውን ምርቶች በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ለተጠቃሚዎች ማቅረብ፣ በአቅርቦቱ በኩል የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት አቅራቢዎችን ማሳተፍ፣ ምርት ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ በሠላም የሚዘዋወርበትን ሁኔታ መፍጠር ተገቢ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

ከረጅም ጊዜ መፍትሔ አንፃር በዋናነት “80 በመቶ ሕዝብ የሚተዳደርበትን ግብርና ወደ ሜካናይዜሽን እርሻ ማስገባት በግብርና ምርቶች ላይ የሚከሰተውን የዋጋ ንረት ለመከላከል ወሳኝ ሚና ይኖረዋል” ብለዋል፡፡

እንደ ምጣኔ ሀብት ምሁሩ ገለጻ ለጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በተበጣጠሰ መንገድ በአርሶ አደሮች የሚታረሰውን ማሳ ወደ ሰፋፊ እርሻ ማስገባትና ድጋፍ ማድረግ ይገባል፤ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር እውን እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት ማድረግም ግድ ይላል፤ የከተማ ነዋሪዎች የቤት ባለቤት የሚሆኑበትን አሠራር መፍጠር፣ ከተሞችን ማዘመን፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ላይ እሴት መጨመር፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅም ማሳደግና የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ በተደራጀ መንገድ መደገፍ ይጠበቃል፡፡

ዘጋቢ ፡- አዳሙ ሽባባው – (አብመድ)

Leave a Reply