ስዊዝ ካናል ወድቃ የዘጋችው 400ሜትር የምትረዝመው መርከብ በፍጥነት ልትነሳ አለመቻሏ ከፍተኛ ቀውስ አስከተለ

በስዊዝ ካናል ለቀናት የቆመችውንና 400 ሜትር የምትረዝመውን ኤቨር ግሪን መርከብ ከወደቀችበት በማንሳት ወደቡን ወደ ቀደመው እንቅስቃሴ ለመመለስ ቀናት እንደሚወስድ ተገለጸ፡፡

የታይዋን ስሪቷ ኤቨር ግሪን መርከብ 400 ሜትር ርዝመትና 59 ሜትር ስፋት ያላት ሲሆን ሰዉ ሰራሹን የስዊዝ ካናል ወደብ በደረሰባት አደጋ ከዘጋች ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ኤቨር ግሪን ብልሽት የአለማችን 12 ከመቶ የሚሆነዉ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበትን ይህንን ካናል ስትዘጋ በአለም ኢኮኖሚ ላይ ገና በቀናት እድሜ ዉስጥ ብቻ በርካታ መሰናክሎች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡ የመርከቧ ወደቡን መዝጋት ከ30 የሚበልጡ የነዳጅ ድፍድፍ የጫኑ መርከቦች እስከ ነዳጃቸዉ እንዲቆሙ ምክንያት የሆነ ሲሆን፣ ይህም በአለም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ሊያከትል እንደሚችል እየተዘገበ ይገኛል፡፡

የሜዲትራኒያንን ባህር ከቀይ ባህር ጋር የሚያገናኘዉ ብሎም በእስያ እና አዉሮፓ መካከል ያለ አጭሩ የንግድ መስመር ተብሎ የሚወሰደዉ የስዊዝ ካናል በቀን 400 ሚልየን ዶላር የሚተመን የንግድ እንቅስቃሴ ይካሄድበታል፡፡ ከወደቡ ወደ ምእራባዊ የአለም ክፍል የሚጓዙ እና የንግዱን እንቅስቃሴ የሚያሳልጡ መርከቦች ብቻ 5 ነጥብ 1 ቢልየን ዶላር በቀን የሚያስገኙ ሲሆን በተቃራኒዉ አቅጣጫ ምስራቃዊ የአለም ክፍልን በንግድ የሚያስተሳስሩ መርከቦች በወደቡ በኩል ሲያልፍ 4 ነጥብ 5 ቢልየን ዶላር በቀን ያስገኛሉ ፡፡

አራት የእግር ኳስ ሜዳ የምታክለዉ ኤቨር ግሪን 20 ሺህ የሚደርሱ ኮንቴነሮችን የተሸከመች ሲሆን፣ ከድፍድፍ ነዳጅ ባሻገር እንሰሳትን፣ የመኪና መለዋወጫዎችን፣ አልባሳት እና ሌሎች ቁሳቁሶችን የጫኑ በርካታ የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴን በመግታት ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበትን የአለማችን ሰዉ ሰራሽ ወደብ ሰቅዛ ይዛለች፡፡እስከ አሁንም 9 ነጥብ 6 ቢልየን ዶላር የሚገመት ቁሳቁስ ወደታሰበዉ አቅጣጫ እንዳይጓጓዝ አድርጋለች፡፡

የወደቡን እንቅስቃሴ ወደቀደመዉ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እያረጉ የሚገኙት ባለሙያዎች አንድ ቀን በሄደ ቁጥር ሌላ ተጨማሪ ሁለት ቀን ሁኔታዉን ለማስተካከል የሚጠይቀን ይሆናል ያሉ ሲሆን ይህም የተጫኑት ቁሶች በተገቢዉ የጊዜ ገደብ እንዳይደርስ በማድረግ በገበያ ዉስጥ የቁሳቁስ እጥረትን ሊያስከትሉ ይችላሉ የሚል ግምታቸዉን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

በአሁኑ ሰአትም የተፈጠረዉ የሶስት ቀናት መጨናነቅ የስድስት ቀናት ኪሳራ ማድረስ ችሏል ልንል እንችላለን ሲሉ ለቢቢሲ መናገራቸዉ ታዉቋል፡፡የግብፅ ስዊዝ ካናል ባለሰልጣናት በበኩላቸዉ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያረጉ መሆኑን ገልፀዉ መርከቧ የጫነችዉን ኮንቴነር በማራገፍ በከባድ እና ዘመናዊ መሳሪያዎች በመታገዝ በአጭር ጊዜ ወደቡን ለመክፈት እና የንግድ እንቅስቃሴዉን ወደ ቀደመዉ እንዲመለስ ለማድረግ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል ፡፡400 ሜትር የምትረዝመዉ ኤቨር ግሪን መርከብ በንፋስ አማካኝነት መስመር መሳቷ ይታወሳል፡፡ (ምንጭ፡-ቢቢሲ) – walata

See also  "የኢትዮጵያ ጦር የበረበራ ወደብን ሊከረብ ይችላል"

Leave a Reply