ስለኔ ፀሐይ እየተቃጠለ በጥላ ያሻግረኛል!!

መጋቢት 22 ቀን 2013. የጉዞ ማስታወሻ

‹‹ሰብዓዊነትና ፍቅር ለትግራይና ለመተከል ›› በሚል ከአርቲስት ፣ አክቲቪስትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ታማኝ በየነ ጋር ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ መስራት ከጀመርኩ ሁለት ወር ሲጠጋኝ ነው ፡፡

የመጀመሪያው ዙር ድጋፍ ወደ መተከል ከሚወስዱት አባላት ውስጥ ቦታውን በደንብ ስለምታወቀው ተብሎ ከሜሮን እና እዮብ ጋር ተመድቤያሁ ፡፡

በቀይ መስቀል የ2 ሚሊየን ብር ዱቄትና ዘይት ተገዝቶ በመኪኖች ተጭኖ ጉዞ ተጀምሯል ፡፡ ከ53 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ያለበት ቻግኒ ከተማ ስንደርስ ስለ ደህንነታችን ስጋት ስላለን ጀነራል ዓለማየሁ ደወልኩ ፤ ጀነራሉ ስልክ ቶሎ አነሱ ፤ በቅንነት እና በግርማ ሞገስ አናገሩኝ ፡፡

ስክን ባለ መንፈስ ‹‹ የመከላከያ ቴሎቪዥን እና የኢዜአ ጋዜጠኞች ከ 40 ደቁቃ በኋላ ቻግኒ ይቀላቀሏችኋል፡፡ መንታውኃ የምትባለው ከተማ ላይ አንድ ኦራል እና አንድ ፓትሮል ሠራዊት እንዲሁም አንድ ፓትሮል የፌደራል ፖሊስ ሠራዊት ይቀበሏችኋል፡፡ ጋሌሳ ቀበሌ አድርሰው ይመልሷችኋል፤ በየመንገዱ ችግር ወይም ስጋት ካለ ደውሉልኝ፡፡›› በማለት ተለያየን፡፡

ከጀነራሉ ቃል አንድ አልነጠፈም ፡፡ ከ40 ደቂቃ በኋላ ጋዜጠኞች ተቀላቀሉን፤ እህል የጫኑ መኪኖች እና የቀይ መስቀል መኪና ቀድመውን መንታውኃ ስለገቡ የሠራዊት ቡድኑ ሁሉም የተጠቃለለ መስሏቸው ትተውን ጉዞ ጀምረው ድባጤ ገቡ ፡፡ እኛ የያዘው መኪና ሹፌር በጣም ስለፈራ ቶሎ ቶሎ ለመሄድ አልቻለም፡፡

ሽበት ከተቀላቀለው ፀጉሩ ነጭ ላብ በግንባሩ ይንቆረቆራል ፡፡ ከመንታውኃ በድፍረት አልፈን አዲስ አለም ደረስን ፤ ወደ ጀነራል ዓለማየው ስልክ ደወልኩ፤ ቶሎ አነሱት ሠራዊቱ ትቶን ሄደ አልኳቸው፤ ለምን? መኪናችን ቶሎ ቶሎ ስለማይሄድ ዘግይተን ነው መንታወኃ የደረስነው፡፡ አልኳቸው የት ናችሁ? አዲስ አለም አልኳቸው ለምን ከመንታወኃ ተንቀሳቀሳችሁ! በሉ እዛው ቁሙ ተመልሰው ይመጣሉ፡፡ አሉኝ፡፡ በድንጋጤ እሺ ብየ ስልክ ተዘጋ ፡፡

አምስት ደቂቃ ሳይቆይ ፓትሮሏ ከ10 በላይ ከባድና ቀላል መሳሪያ የታጠቁ ሠራዊቶች ይዛ ከተፍ አለች፡፡ ከጋቢና ኮሎኔሉ ወረዱና እናንተ ናችሁ ከጀነራል ጋር የተደዋወላችሁት? አሉን አዎ አልኋቸው በፊልም ያየኋቸው አክተሮችን ይመስላሉ፡፡ ግን አክተር ሳይሆኑ የእውነታው ዓለም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ናቸው ፡፡

See also  የውጭ ጫናዎችን ለመቋቋም ዳያስፖራው ገንዘቡን በህጋዊ መንገድ በመላክ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተጠቆመ

እየተከተልናቸው ወደ ድባጤ ሄድን ፤ ከተማው ላይ ስንገባ ሁሉም መኪኖች ጠበቁን፡፡ ከፊታችን ብዙ ሠራዊት የያዘ ኦራል ይበራል፤ ከኋላችን አንድ ፓትሮል ሠራዊት አጅቦናል ፡፡ ከጭነት መኪኖች መሃል አንድ ፓትሮል የፌዴራል ፖሲስ ሠራዊት ይከተለናል፡፡

ኦራሉ ራቅ ሲል ይቆምና ይጠብቀናል ፡፡ የኛ መኪና ሹፌር ሰራዊቱን ካየ በኋላ ላቡ ደርቋል፤ መኪናውም በጣም መብረር ጀምሯል፤ ድሮም ፍርሃቱ እንጂ መኪናው ደህና ነው፡፡ እኔ በለሆሳስ እየፀለይሁ ነው ፤ ሜሮን ፊቷ ዝናብ ያዘለ ደመና መስሏል፤ ለማልቀስ ሰበብ እየፈለገች ይመስላል ፤ እዮብ የሚያወራውን አያውቀውም ፡ ኢዜአ ጋዜጠኞች በየራሳቸው ዓለም ገብተዋል፡፡ በተለይ ካሜራ ማኑ ጾም ላይ ስለሆኑ የልጆቼ አምላክ ተከተለኝ ሲሉ ይሰማል፡፡

መንገዱ በጣም አስቸጋሪና አቧራ የሚበንበት ነው ፡፡ ፓትሮሏ ቀድማ ሄደች ፤ ቦታው የስጋት ጥርጣሬ ያለበት ነው፤ ሶስት ሽፍታ የሚመስሉ ሰዎች መሳሪያ ታጥቀው ከመንገዱ ራቅ ብለው ቆመዋል ፤ የሠራዊቱ አባላት ፊት ለፊት ተጋፍጠው እንዲያልፉ ምልክት ሰጧቸው ፤ መሳሪያቸውን ዘቅዝቀው አለፉ ፡፡ ለምን ዝም አሏቸው ግራ ገባኝ ! መኪናችን ኦራሉን ተጠግታ ቆማለች፤ ወርጄ ሬዲዮ የያዘውን የሠራዊት አባል ለምን ዝም አሏችኃቸው? ስለው ከቀዮች ጋር ሰላማዊ ኑሮ እየተለማመዱ ነው፡፡ አለኝ ፡፡ እውነትም ከብት የሚነዱ ቀዮች (ሽናሾች፣አማራዎች፣ አገዎች፣ ኦሮሞዎች ) በቀኝ በኩል መሳሪያ ታጥቀው መሳ ለመሳ ይሄዳሉ ሁሉም በተጠንቀቅ ያሉ ይመስላሉ፡፡

የሠራዊት አባላቱ ፀጉራቸው ፣ ትከሻቸው ፣ ፊታቸው ቀይ አፈር መስሏል፤ እኛ ያለንብት መኪና ሽፍን ነው፤ መስኮት ብንከድንም ትንሽ አቧራ ጠጥተናል ፡፡ ሆኖም ወታደር የያዘው ከፊት ቅድሙ አለን ፤ እናንተ ቅደሙ አቧራ ያስቸግራችኋል አልናቸው ፡፡ ‹‹አይ አይሆንም ከፊት ኦራል ቀድሟል እና ከኋላ የሚመጣውን መጠበቅ አለብን አለኝ ፡፡›› አቧራውስ? አልኩት ‹‹እሱማ ስለ እናንተ የምንጠጣው ትንሹ የፍቅራችን መገለጫ ነው፡፡›› አለኝ ፡፡

አእምሮዬ ያቃጭል ጀመረ ፡፡ አቧራው ዐይናቸው ላይ ምርጊት መስሏል ፣ ፀጉራቸው ከተመኛው የተቀባውን ቀለም መስሏል ግን አቧራ ነው ፡፡ ፊታቸውን ካልታጠቡ ወይም ካተወለወሉ በስተቀር ማንም አይቶ እገሌ ነህ ሊላቸው አይችልም ፡፡ ከተክለ ቁመናቸው መቀያየር በስተቀር መንታ ቤተሰቦች መስለዋል ፡፡ ይህ ሁሉ ስለኔ ፣ ስለሁላችን ነው ፡፡

See also  በትግራይ ለ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች እርዳታ ቀረበ- 9 ሚሊየን የኮቪድ19 ክትባት ሊገባ ነው

የእምዬ ኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ስለኔ አቧራ ይጠጣል፤ እኔን ግን ከአቧራ ከልሎ ያሻግረኛል ፡፡ ስለኔ በፀሃይ ተመቶ ተቋቁሮ እኔን በጥላና በምቾት ያሳልፈኛል ፡፡ ስለኔ ሞትን ተጋፍጦ እኔን በሕይወት እንድኖር ይጋደልልኛል፡፡

ጋሊሳ ቀበሌ ደረስን፤ ያመጣነው ድጋፍ አወረድን፤ ጋዜጠኞችም ስራቸውን ጨረሱ፡፡ ኮሎኔሎ ወደ እኔ ጠጋ አሉና ‹‹ዛሬ እዚ አታድሩም›› አሉኝ ፡፡ ምነው? አልኩ፤ በልባችን አድረን ለተፈናቃዮች አከፋፍለን ለመውጣት አስበን ነበር፡፡ ‹‹ሁሉም ሚስጢር አይነገርም፤ ግን ጥሩ ሁኔታዎች የሉም፤ ምንም ባትሆኑም የሆነ ነገር እንኳ ቢፈጠር መደንገጥ የለባችሁም፡፡›› አለኝ ፡፡ የኛ ተልእኮ ድጋፉን እዚህ ማድረስ ነው፤ የማከፋፈሉን ስራ የሚሰራው ቀይ መስቀል ነው ፡፡ መሄድ እንችላለን አልኩ ፡፡

እንደተለመደው አንዱ መኪና ከፊት እየቀደመ አካባቢውን ይቃኛል ፡፡ እኛ ከመሃል ሁነን ደህንነታችን ተጠብቆ በኋላ ሁለት ፓትሮል እየጠበቀን ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልን ለቀን ወጣን ፡፡

መኪና አቁመን ሰላምታ ተለዋወጥን፣ የጋራ ፎቶ ተነሳን ስላደረጉልን ሁሉ አመስገናቸው፤ ስልክም ተለዋወጥን ፤ ከምሽቱ 1፡30 ቻግኚ ከተማ ስንገባ ስልክ ተደወለ፤ ሄሎ አልኩ፤ ሄሎ፤ ከሠራዊቱ አንዱ ነው፤ አበበ? አቤት! በሰላም ገባችሁ? አዎ ለምስጋና ቃላት አጥሮኝ በጣም እናመሰግናለን አልኩ ፡፡ እንኳን ሰላም ገባችሁ ደህና ሁኑ ብሎ ተሰነባበተኝ፡፡ እኔም በልቤ እናንተም ደህና ሁኑ!! ስለኔ ለከፈላችሁትም! ለምትከፍሉትም ተመን የለለው ዋጋ አመሰግናለሁ!!!

የሀብከ ጥላሁን – ከአዲስ አበባ

Leave a Reply