«በጎና ቀና ህልም ይዞ የመጣው ለውጥ ስር በሰደደ ክፉ የከፋፍለህ ግዛው ሴራ ምክንያት የታሰበውን ያህል ስኬታማ ሊሆን አልቻለም»

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ብዙ ዋጋ ከከፈሉ ሰዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት ስማቸው ይጠቀሳል። በተለይም ባለፉት 27 ዓመታት ህወሓት መራሹ ስርዓት በህዝቦች ላይ የሚፈፅመውን ግፍና በደል በይፋ በመቃወም፣ የቀረበላቸውን መደለያ አሻፈረኝ በማለትና እስከ ትጥቅ ትግል ድረስ ለነፃነት ሲሉ በከፈሉት ዋጋ በብዙዎች ዘንድ ከበሬታ ያተረፉ ናቸው ።

ለውጡን ተከትሎ በተፈጠረው እድል ያደርጉት በነበረው ትግል ምክንያት ለዓመታት በግፍ ታስረው ከነበሩበት ወህኒ ቤት በዶክተር አብይ ፅኑ ተጋድሎ መፈታታቸውን ይመሰክራሉ። ለለውጡ መጠናከር በቅንነት ያላቸውን እውቀትና ምክረ ሃሳብ ሲለግሱ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት ምንም እንኳ በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ገብተው ባይሳተፉም በሚመሩት ሚዲያ አማካኝነት በአገሪቱ ትክክለኛ ዲሞክራሲ እንዲመጣ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ። የሁልጊዜ ተባባሪያችን አንጋፋው ፖለቲከኛ እንዲሁም የኢሳት ስራአስኪያጅ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ዛሬም የለውጡን ሶስተኛ ዓመት እንዲሁም የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበትን አስረኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ አነጋግረናቸዋል። እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን፡- ያለፉት ሦስት ዓመታት የለውጡ አጠቃላይ ሂደት በእርሶ እይታ ምን ይመስላል?

አቶ አንዳርጋቸው፡- ያለፉት ሶስት ዓመታት የለውጥ ሂደት አጀማመሩ በጣም ጥሩ የሚባል ነው። ጥሩ ከሚያደርጉት ነገሮች እንዱ እንደ ከዚህ ቀደሙ የለውጥ ሙከራዎች በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ትርምስና እልቂት ያስከተለ አለመሆኑ ነው። ያ የቆየ የለውጥ ባህላችን ፣ አዲስ ስልጣን ላይ የሚወጣው ድሮ የነበረውን በጠላትነት የሚፈርጅ፣ ህብረተሰቡም በቂም በቀል እንዲሁም ቁርሾን እንደያዘ የሚቀርበት ሁኔታ ነበር። እንግዲህ የዚህ ለውጥ አንዱ ትልቁ ነገር ያንን የተለመደውን አይነት ከስልጣን የሚወገዱ ሰዎች በብዛት የሚታሰሩበት ፣ ከዚያም አልፎ የሚወገዱበት አለመሆኑ ነው።

ከዚህ አኳያ እንደምታስታውሽው የአፄ ኃይለስላሴ ባለስልጣናት በደርግ የደረሰባቸው ይታወቃል። የደርግ ባለስልጣናትም ወያኔ ሲመጣ ተመሳሳይ እጣ ነው የደረሰባቸው። ከዚህ አንፃር ለውጡ ከዚህ በተለየ መልኩ ያለአንዳች ደም መፋሰስና ያለመሳሪያ ሃይል መምጣቱ የተለየ ያደርገዋል። ህብረተሰቡም በጠቅላላ መሰረቱ ሳይናጋ ነገሮች የሚቀጥሉበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። በዚህ ለውጥ አብዛኞቹ ነገሮች ዶክተር አብይ ደጋግሞ እንደሚለው በፍቅርና በይቅርታ እንድናልፈው ተደርጓል። የነበረው መጠፋፋት በይቅርታ መተካቱ በመልካም ጎኑ የሚታይ ነው። ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ይዞ ሊሄድ የሚችል ፈጣንና ጤነኛ የሆነ የፖለቲካ ስርዓት፣ እድገትና ብልፅግና ሊያመጣ የሚችል ስሜት ፈጥሯል ባይ ነኝ።

አዲስ ዘመን፡- ይህ ሁኔታ በአገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ባህል አምጥቷል ማለት ይቻላል?

አቶ አንዳርጋቸው፡- እንዳልሽው በአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ በሚባል ደረጃ ነበር የመጣው። ችግር የሆነው ነገር በዚያ መንገድ መቀጠል አለመቻሉ ነው። የዚህ አይነት ነገር ቀጣይነት እንዲኖረው ይህንን ፖለቲካ ምዕራፍ ወይም ባህል ለሁላችን ይበጃል በሚል ለትልቋ አገርና ህዝብ እስከጠቀመ ድረስ ትንሽም ቢሆን የማይመች ነገር ቢኖረውም እንሂድበት በሚል አስፍተው አይተው የሚቀጥሉበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቢሆን ትልቅ ለውጥ ነበር የሚሆነው። ነገር ግን በዚያ መንገድ ተጀምሮ ይህንን እውነት ተቀብለው ገብቷቸው ሊቀጥሉ የሚችሉ ሃይሎች ማግኘት አልተቻለም።

አብዛኞቹ ሃይሎች የተጀመረው ለውጥ እንዲደፈርስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል ። ሁሉን ነገር በፍቅር ፣በሰላምና በይቅርታ እንለፈው፣ ከቂም በቀል ነፃ እናድርግ ተብሎ በተለይም በለውጥ ሃይሉ የቀረበውን ሃሳብ ህዝቡ ከሞላ ጎደል ተቀብሎት ነበር። የበደሉን ሁሉ ይታሰሩልን ይሰቀሉልን ብሎ ግፊት የሚያደርግበት ሁኔታ አልተፈጠረም። ከዚህ በፊት ግን እንደምናውቀው አገሪቱን በሁሉም መልኩ ሲቆጣጠሩ የነበሩ ሃይሎች የዚህን አዲስ ባህል ጠቀሜታ ለራሳቸውም ሆነ ለሀገራቸው መረዳት አቅቷቸው ተመልሰው አገሪቷ ወደ ጦርነትና ወደ ምስቅልቅል እንድትገባ የሚያደርግ ሁኔታ ፈጥረዋል።

ይህ የቀደመው ሥርዓት ቅሪት የለውጥ ሃይሉ የሚያደርገውን ጥረት ለማሰናከል የተቻለውን ያህል ሰርቷል። የለውጡ ሃይል አዲስ ፖለቲካ ባህል ለማምጣት ሃሳቡ ቢኖርም ደግሞም በተወሰነ መልኩ ከጥቂት ወራት በላይ ሊቀጥል ያልቻለበት ሁኔታ ነው የታየው። ስለዚህ ሃሳብ ነበር፤ ለጥቂት ወራት ተሄዶበታል፤ ነገር ግን ይሄ አዲስ ባህል የማይገባቸው ሃይሎች ለውጡ ስር እንዳይሰድና እንዳይጠናከር የሚያደርግ ሁኔታ ፈጥረዋል። ስለዚህ ባህሉ አገሪቷ ውስጥ ይሰራል፣ አይሰራም የሚለው ነገር ገና እየተፈተሸ ያለ እንጂ በስራ ላይ ያለ አይደለም።

አዲስ ዘመን፡– ከኢኮኖሚ አኳያ ለውጥ ለማምጣት የተደረገው ጥረት ምን ያህል ውጤታማ ነው ብለው ያምናሉ?

አቶ አንዳርጋቸው፡ አገሪቱ በአጠቃላይ ለውጥ ውስጥ ነው ያለችው። ከለውጡ ጋር ተያይዞ አለመረጋጋቶች በተለያዩ ቦታዎች ተቀስቅሰዋል፣ የሰላምና መረጋጋት ጉዳይ ደግሞ ለኢኮኖሚ እድገት ፣ ለብልፅግና በጣም አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ይሄ ለውጥ ከመጣ ጀምሮ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የተረጋጋና ሰላማዊ ሁኔታ መፍጠር ባለመቻሉ ምክንያት መዋእለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ለሚፈልጉ የአገር ውስጥ ሆነ የውጭ አገር ባለሃብቶች የሚያበረታታ ሁኔታ አይደለም። በዚያ ላይ ደግሞ ኮቪድ ሲመጣ የአለምን ኢኮኖሚ እንዳደቀቀው ሁሉ እዚህም አገር ላይ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ጉዳት አስከትሏል። በሌላ በኩል ደግሞ ኮቪድንም ሆነ አገሪቷ ውስጥ ያለውን አለመረጋጋት ግምት ውስጥ አስገብቶ በተወሰነ ደረጃ በመንግስት በኩል የተወሰዱ እርምጃዎች ከሚገባው በላይ ኢኮኖሚው እንዳይሞትና የበለጠ ደግሞ ሌላ ችግር ውስጥ እንዳይገባ አድርጓል የሚል እምነት አለኝ ። ግን በዚህ በለውጥ ሂደቱም ቢሆን ኢኮኖሚው አዎንታዊ በሆነ መንገድ ትልቅ ነገር ተገኝቶበታል ብሎ ለመናገር አይቻልም። ምክንያቱ ደግሞ አስቀድሜ የገለፅኩልሽ አለመረጋጋቱና ኮቪድም ትልቅ ተፅዕኖ አሳድሮበታል።

አዲስ ዘመን፡– የህዝቦች ማህበራዊ ግንኙነትን ለማሻሻል የተሰራው ስራስ ምን አይነት ድክመቶች ነበሩበት?

አቶ አንዳርጋቸው፡ በዚህ ረገድም ቢሆን በዋነኝነት ማየት የሚገባን ጉዳይ አስቀድሞ የነበረውና ህዝብን ከህዝብ በመከፋፈል የተሰራው ስራ ለማህበራዊ ግንኙነታችንም ሆነ ህዝባዊ አንድነታችን ላይ አደጋ ጥሎበታል የሚል እምነት ነው ያለኝ። በተለይም ሰውን በማንነቱ፣ በዘሩ ፣ በእምነቱ ጭምር ከፋፋሎ በቀላሉ መግዛት ይቻላል ከሚል መጥፎ እሳቤ ተነስቶ ወያኔ የሰራው ስራ ወይም የዘራው ከፋፋይ ዘር ፍሬውን ማፍራት የጀመረው በለውጡ ጊዜ ነው። እናም በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሰዎች ማንነታቸውን እየለዩ ሌሎች ወገኖቻቸውን የሚያፈናቅሉበት ሁኔታ በስፋት ነው ያየነው። ስለዚህ በጎና ቀና ህልም ይዞ የመጣ ለውጥ ስር በሰደደ ክፉ ከፋፍለህ ግዛው ሴራ የታሰበውን ያህል ስኬታማ ሊሆን አልቻለም። በአገሪቷ ዜጎች መካከልም ወንድማማችነትና እህትማማችነት አጠናክሮ ለመቀጠል አልተቻለም። አገሪቷን ካለችበት ድህነትም ሆነ ያልተረጋጋ ሁኔታ አውጥቶ ጠንካራ የፖለቲካ ስርዓት የተገነባባት አገር ለማድረግ የለውጥ ሃይሉ አስቦት የነበረውን ነገር በከፍተኛ ደረጃ ነው የተገዳደረው።እናም ገና ብዙ ስራ እንደሚጠብቀን ነው አሁንም የሚያሳየው። ስለሆነም በጣም ከልባችን ሆነን ራሳችንን ሳናታልልና ሳናጭበረብር በፖለቲካውም፣ በኢኮኖሚውም ሆነ በማህበራዊ ግንኙነት አገሪቱ ያጋጠማትን ተግዳሮት መመርመር ያስፈልጋል። ለዚህ የሚሆኑ መፍትሄዎችንም ትኩረት ሰጥቶ ማሰብ ይጠይቃል። እዚህ ጋር የተወሰነ ጥርጣሬ አለኝ። ይኸውም በእርግጠኝነት እነዚህን መፍትሄዎች በሚገባ እያሰበ የሚሰራ አካል አለ ወይ? የሚለው ነው።

አዲስ ዘመን፡– ከውጭ ዲፕሎማሲ ግንኙነት አኳያ ምን አይነት እምርታ ታይቷል?

አቶ አንዳርጋቸው፡ በዲፕሎማሲ ረገድ ያለውን እውነታ በሁለት መንገድ ከፍለን ማየት እንችላለን። ለውጡ እንደተጀመረ ሌላም ቦታዎች ላይ ቀና ነገሮችን እንዳየነው በዲፕሎማሲውም አካባቢ በጣም ጥሩ ነገሮች ታይተዋል። የቀጠናውን ዲፕሎማሲ ብትመለከቺ ከሱማሊያ ጀምሮ ደቡብ ሱዳንም ሆነ በሌሎቹ ጎረቤት አገራት ዋናዋ አስታራቂ፣ እዛ አገር ያሉትን ችግሮች ፈቺ የሆነችበት ሁኔታ ነው የነበረው። በተለይም ደግሞ ከ20 ዓመት በላይ ጦርነት አይሉት ሰላም የሌለበት የኢትዮ- ኤርትራ ግንኙነት በአስገራሚ ሁኔታ መለወጥ የተቻለበት ሁኔታ ታይቷል ። በአጭር ጊዜ ውስጥ በጣም ቅርበት ወዳለው ግንኙነት ውስጥ የተመለሱበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። በአለም ላይም በዚህ አካባቢ በተሰሩት የዲፕሎማሲ ስራዎች ከኤርትራ ጋር በተፈጠረው እርቅና ስምምነት የተነሳ እንደ አፍሪካዊ መሪ ኖቤል ሽልማት ማሸነፍ የተቻለበት ሁኔታ የተፈጠረው በዲፕሎማሲያዊ መስክ በተሰራው ስራ ነው። ይህንን ተከትሎ የአለም መንግስታትም ከኢትዮጵያ ጋር በጣም አዎንታዊ የሆነ ዲፕሎማቲክ እይታ ነው የነበራቸው። ግን ይሄ ነገር ልክ እንደሌሎቹ ነገሮች በፍጥነት እየተሸረሸረ የሄደበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። ለዚህም ትልቁ ምክንያት ከአባይ ግድብ ጋር ተያይዞ ግብፅና ሱዳን በተለይም የዲፕሎማቲክ መድረክ በፊት ለፊትም ሆነ በድብቅ የሚሰሯቸው በርካታ አጥፊ የሆኑ ስራዎች ናቸው። ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲ መልኩ ማዳከም፣ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ከሚቀርቧትና ከሚደግፏት አገሮች የመለየት ስራ ትልቁ ነገር ነው።

ሌላው ከዲፕሎማሲ ስራ ጋር ተያይዞ ችግር የሆነው በቅርቡ የወሰደችው ህግ የማስከበር እርምጃ ነው። እርምጃው ትግራይ ውስጥ በተወሰደበት ጊዜ ከዚህ ቀደም ወያኔ ስልጣን ላይ በነበረበት ሰዓት ከፍተኛ ቅርበት ኖሯቸው ሲሰሩ የነበሩ የተለያዩ መንግስታት፣ የተለያዩ አለምአቀፍ ድርጅቶች፣ አለምአቀፍ የሚዲያ ተቋማት ለዚህ ሃይል ውለታ ለመክፈል በሚመስል መልኩ በኢትዮጵያ ላይ በደል ፈፃሚ ሆኖ ሳለ በደል

  እየተፈፀመ ያለው በወያኔና በትግራይ ህዝብ ላይ አድርገው የሚያቀርቡበት ነገር ተጨማሪ የዲፕሎማቲክ ተግዳሮት ሆኖ መጥቷል። ይህንን ጉዳይ ደግሞ በተለያዩ በአለምአቀፍ ድርጅት ውስጥ ያሉ በጣም ከፍተኛ ገንዘብ በእጃቸው ያሉ የወያኔ ደጋፊዎችና ከእነሱ ጋር የሚሰሩ የውጭ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲ መልኩ ያገለግላል ብለው የሚያስቡ እነግብፅና ሱዳንም ይህንኑ ጉዳይ ከአባይ ግድብ ወጥተውም እያራገቡት ነው።

በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ህዝብ እያለቀ ስለመሆኑና ወንጀል እየተፈፀመበት እንደሆነ ስራዬ ብለው በሃሰት ውንጀላ ውስጥ ናቸው ።

ግብፅና ሱዳን ቁጭ ብለው በስትራቴጂ ደረጃ ኢትዮጵያን በአለምአቀፍ ዲፕሎማሲ ለማዳከም እየሰሩ ነው። ከአባይ ግድብ ባለፈ ውስጣዊ ቁስላችንን በመጠቀም ከአለም ህብረተሰብ እንድትለይ የማይፈነቅሉት ጉድጓድ የለም ። ለዚህ ደግሞ ያኮረፉ የውስጥ ሃይሎች እርስበርስ እንዲጋጩ በማድረግ፣ ሰላም እንዳይፈጠርና እንዳይረጋጋ በማድረግ ፣ ግጭቱንም በማባባስ በገንዘብም ሆነ በሌላ መልኩ ይደግፋሉ። ከዚያም አልፈው የወያኔ ሰዎች የሚያራግቡትን በማራገብ ተጨማሪ የሆነ የዲፕሎማሲ ችግር ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ ነው ። ስለዚህ በዲፕሎማሲ መልኩም ወርቃማው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ዘመን ተብሎ ሊገለፅ እና ጅማሮ ላይ ያለውን የለውጥ ሂደት ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ችግር ውስጥ የወደቀበት ሁኔታ ነው ያለው።

በአጠቃላይ እነዚህ ነገሮች የሚያሳዩት እኛ እንደምናስበው ወይም በኢትዮጵያውያን በኩል ብቻ ያለው ቀናነት፣ በጎ አሳቢነት ላይ የተመሰረተ ፍቅር ብቻ ስላልን፣ መደመር ስላልን፣ ይቅርታ ስላደረግን ችግሮቻችን ሊቃለሉ የማይችሉ መሆናቸውን ነው። ችግሮቻችን በአንድ በኩል ሰውን በፍቅር ለመዳሰስ የተዘረጋን እጅ የሚያሳይ ሆኖ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የተዘረጋውን እጅ ሰብስቦ እንደቡጢም መጠቀም የሚያስፈልግ ሁኔታ መኖር ያስፈልጋል። በመሆኑም የሰላሙም፤ የይቅርታውም ነገር የማይገባቸው የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሃይሎች መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም። እነዚህን ሃይሎች በምን መንገድ ነው የምንቋቁማቸው የሚለውን ነገር ስትራቴጂክ በሆነ መልኩ ማየት ይጠይቃል። ያለፉት ጊዜያት የነበሩት ችግሮች አንደኛውን ብቻ የሚያይ የለውጥ ሃይል ለሌላው በደንብ የተዘጋጀበት ሁኔታ አለመኖሩን ጭምር ያሳየ ይመስለኛል።

አዲስ ዘመን፡– ባለፉት ሶስት ዓመታት የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት በሚፈለገው ደረጃ ተጠብቋል ማለት ይቻላል?

አቶ አንዳርጋቸው፡ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅበት ሁኔታ በጣም ስፋት ያላቸው ሚዲያዎች ነፃ የሆኑበት፣ እንደፈለጉ የሚዘግቡበት፣ ብዙም የሚያሳስብ ነገር ያለ የማይመስልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። የፈለጉትን ቢዘግቡ እንኳን ህዝቡም ሆነ መንግስትም የማይጨነቅበት ሁኔታ ነበር። ከዚህ አንፃርም የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ወርቃማው የኢትዮጵያ ሚዲያ ነፃነት ዘመን ተብሎ የሚጀመርበት ሁኔታ ውስጥ ነው የገባው።

እዚህም ላይ ግን በደንብ ያልታሰበበት ነገር እንደነበር ማየት እንችላለን። አገሪቷ ምንም ችግር ውስጥ ባልወደቀችበት ሰዓት፤ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ በሚመስልበት ሁኔታ ላይ የፈለገውን አይነት አክራሪ አመለካከት ቢያንፀባርቅ ካመለካከት ያለፈ ሊሆን ስለማይችል ጉዳት ላይኖረው ይችላል ተብሎ የሚታሰብበት ሁኔታ ነው የነበረው። ነገር ግን በሁሉም መስኩ ፈተናዎች መምጣት ሲጀምሩ በሚዲያ ነፃነት ስም የተለቀቀ ነገር ሁሉ በጎ ነገር እንዳልሆነ ለመገንዘብ ችለናል። አገር ውስጥ ያለ ህዝብ ከህዝብ በመጫረስ የአገር መሰረታዊ ጥቅሞችና ደህንነቶችን የሚጎዳ አደገኛ የሆነ ነገር የተፈጠረበት ሁኔታ ነው ያለው። እናም የሚዲያ ነፃነት ሲባልም ገደብ ሊኖር እንደሚገባ ተምረንበታል። ነፃነት ከግዴታ ጋር የሚሄድ ነገር መሆኑን ፣ መጀመሪያ ላይ ታይቶ ያልነበረና ዝም ብሎ የተለቀቀ ነገር ነበር ፣ መብትና ግዴታ የያዘ የሚዲያ ባህል ሊዳብር እንደሚገባ አስገንዝቦናል።

ከመጀመሪያው ሚዲያ ምን ሊያደርግ እንደሚችል በተለይም ኢትዮጵያን በመሰለ ከፈተና ባልወጣ አገር ላይ የሚዲያ ሃላፊነት ምን መሆን ይገባዋል ፣ ሃላፊነታቸውን የማይወጡ ሚዲያዎች በምን መልኩ መቆጣጠር ይገባዋል የሚለው ነገር የታሰበበት አይመስለኝም። ይሕም ማለት ሃሳብ የመግለፅ ነፃነት መገደብ ማለት አይደለም። ነገር ግን ሃሳብ በመግለፅ ነፃነት ስም አገር ወደማፍረስና ህዝብ ለህዝብ የሚያጫርስ ሚዲያ እንደልብ ሊለቀቅ የማይገባው መሆኑን ከመጀመሪያው መስመር አስምሮ መነሳት ያስፈልግ እንደነበረ ትምህርት የሰጠ ነው። ስለዚህ አሁንም ቢሆን መንግስት በተወሰነ ደረጃ ፈቃድ የሰጣቸው ሚዲያዎች ሃላፊነት ባለው መንገድ ስራ እንዲሰሩ የሚያስደርግ የሚዲያ ህግ አውጥቷል። የራሳቸውም የሚዲያ ባለቤቶች ራሳቸውን በራሳቸው መቆጣጠር የሚችሉበት በግለሰብም ሆነ በቡድኖች ያለአግባብ የሚቀርቡ ነገሮች መስማትና ማቃለል የሚችልበት መስመር እንዲኖር አድርጓል።

አዲስ ዘመን፡– በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩትም ሆነ ነፃነታቸው ተገድቦ የኖሩ ፓርቲዎች ለውጡ የፈጠረላቸው ምቹ ምህዳር ተጠቅመውበታል ማለት ይቻላል?

አቶ አንዳርጋቸው፡ ምንም ጥያቄ የለውም። መጀመሪያ ምህዳሩ ለሚዲያው እንደሰፋው ሁሉ ለፖለቲካ ድርጅቶችም በአሸባሪነት የተፈረጁትም ጭምር አገር ውስጥ ገብተው መንቀሳቀስ የጀመሩበት ሁኔታ በጣም የሚያበረታታ ነበር። ግን እንደሌላው ነገር ሁሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ጉዳይ ብዙ ፈተናዎች ያሉበት ነው ። አንዱ ፈተና ከተቃዋሚዎች ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም። መጀመሪያ ሰሞን ላይ የሁሉም የመንግስት አስተዳደሮችና መዋቅሮች ለውጡ ይዞት በመጣው ተፅዕኖ የተነሳ ከፋፍተውት የነበረውን የፖለቲካ ምህዳር ትንሸ ቆይተው ከእነሱ መዋቅር ውጭ መገልገያ መዋቅር እንደሌለው ሲያውቁ እንደማይተኩም፣ መተካትም እንደማይቻል በተረዱቡት ሰዓት የመጀመሪያዎቹ ምህዳር አጥባቢዎች የክልሎቹ ባስልጣናት ፣ የወረዳዎቹ ሃላፊዎች ሆኑ ። ከእነሱ ጋር ተያይዞ ሌሎች ሃይሎች የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ ወደ ሃገር የገቡትም ሆነ ሀገር ውስጥ የነበሩት ልክ እንደመንግስት መዋቅር በተለያዩ ክልሎች በራሳቸው የፖለቲካ ምህዳር አጥባቢ ሆነው የተፈጠሩበት ሁኔታ ተፈጠረ። እዚህ አካባቢ ከእኔ ድርጅት ሌላ ማንም መምጣትም ሆነ ህዝብ መሰብሰብ አይችልም፤ ማነጋገር አይችልም፣ ቢሮ መክፈት አይችልም ወደሚል ሁኔታ ውስጥ ነው የተገባው ። ስለዚህ የፖለቲካ ምህዳሩ ችግር የአንድ ወገን አይደለም። በአጠቃላይ ፖለቲካ ምን እንደሆነ፣ ምን ሊሆን እንደሚገባው ያልተረዳ ነው ያለው። ሌላውን ለማጥፋት አሻጥር የሚሰራ የፖለቲካ ሃይል ያለበት ሁኔታ በመኖሩ የተፈለገውን ያህል የፖለቲካ ምህዳሩ ሊሰፋ አልቻለም።

ሌላው ከተቃዋሚዎች ጋር የሚነሳው ነገር የፖለቲካ ምህዳሩን በደንብ ሊጠቀሙበት ያልቻሉት አብዛኛዎቹ እንደፖለቲካ ድርጅት መስራት የሚገባቸውን በደንብ የሚያውቁ ባለመሆናቸው የተነሳ ነው። ፖለቲካ የህዝብ ህይወትንም ሆነ የአገርን አጠቃላይ ሁኔታ የሚነካ እንደመሆኑ በተለያዩ ዘርፎች የተሻለ ፖሊሲ ቀርፆ መገኘትን ይጠይቃል። የዚህ አይነት የፖለቲካ ባህል ባልኖረበትና አንዱ ሌላውን በማሳጣት፣ በመስደብ፣ በመወንጀል ሲሄዱበት የነበረው ሁኔታ፣ በሃሳብ ላይ ተመስርቶ የሚደረግ ተቃውሞ ባልነበረበት የፖለቲካ አሰራር ምህዳሩ ሲከፈትለት በብዙ ቦታዎች ላይ የሄደው ተመሳሳይ የሆነ ጥላቻን በስሜት ማህበረሰብን በመቀስቀስ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ በማድረግ እውነተኛ ፖለቲካ ባልሆነ መንገድ የሚሄዱ ናቸው። ብዙዎች ትልልቅ ናቸው ያልናቸው ድርጅቶች ምንም ፖሊሲ ማቅረብ ካለመቻላቸው የተነሳ መሪዎቻቸው በየቦታው እየዞሩ ያደረጉት ነገር የሰለጠነ ፖለቲካ ከሚያውቅ ሰው የሚጠበቅ አይደለም። የተጋቡ ሰዎች በዘራቸው ምክንያት እንዲፋቱ ጥያቄ እስከማቅረብ፣ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ለዘመናት ሲግባቡ የኖሩበትን ቋንቋ እንዳይጠቀሙ፣ አንዱ ከአንዱ ሱቅ እንዳይገበይ እስከማድረግ የተሄደበት መንገድ ፖለቲካ አይደለም።

ይህ ተግባር ፖለቲካ ምን እንደሆነ ከማያውቅ ለረጅም ዘመን ፖለቲከኛ ነኝ ወይም የፖለቲካ ድርጅት አለኝ ብሎ ቢያስብም ያቋቋመው የፖለቲካ ድርጅት እንዳልሆነ ሲያወራም የነበረው ፖለቲካ እንዳልነበር የሚያሳይ ነው። ስለዚህ የፖለቲካውን ምህዳር ያጠበበው ነገር የቆየው የፖለቲካ ባህላችን ነው። ፖለቲካ በስርዓትም እንደሆነ እና በሚገባ የፖለቲካ ሊሂቅ እዚህ አገር ላይ በስፋት አለመኖሩም ጭምር ያሳየ ነው። ይሄ ትልቅ የሆነ ችግር ፈጥሯል፤ በዚህ የተነሳ ትልቅ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች በፖሊሲ ደረጃ አማራጭ ይዘው ቢመጡ ኖሮ ሌሎች ከሚያቀርቧቸው ጋር በንፅፅር አይቶ ሊመረጥ የሚችልበትን ሁኔታ ያመከነ ፣ እነሱም ከፖለቲካ ፉክክሩ የወጡበትን ራሳቸውንም ሆነ አገርን አደህይተው ቁጭ ያሉበት ሁኔታ አለ።

የፖለቲካ ምህዳሩ ጉዳይና ለፖለቲካ ሃይሎች የተሰጠው ነፃነት በተመሳሳይ በዲፕሎማሲ ፣ በሰላምና መረጋጋት ፣ በኢኮኖሚ የተከሰተው አይነት ነው። ሁሉንም ስትደምሪያቸው ከስራቸው አንድ አይነት የጋራ የሆነ ችግር ቆልፎ የያዛቸው እንደሆነ ትረጂያለሽ። በሁሉም መስክ ተመሳሳይ የሆነና እያደገ የሚሄድ ነገር ምንድን ነው? እንዴትስ ነው የምንወጣው? የሚለው ነገር ጥልቅ የሆነ ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። የለውጥ ሃይሉም ይሁን በአገሪቷ ብቃትና እውቀት አለን ብለው የሚያስቡ ምሁራን መሰረታዊ ጉዳይ ላይ ስራ እየሰሩ ነው የሚል እምነት የለኝም። ትልቁ ነገር እሱ ነው የሚመስለኝ።

አዲስ ዘመን፡ከዚህ አንፃር ፓርቲዎች መጪውን ምርጫ ነፃና ሰላማዊ ለማድረግ የበኩላቸውን ሃላፊነት እየተወጡ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ አንዳርጋቸው፡ እንዳልኩት ትልቁ ነገር ፖለቲካ ሲባል ቅድም ያልኩት ትርጉም ነው ያለው። ፖለቲካ ውስጥ ስትገቢም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት ስታቋቁሚ ስልጣን ይዘሽ አገር ለማስተዳደር ስለሆነ የአገሪቷን መሰረታዊ ችግሮች ማወቅ ያስፈልግሻል። እነዚህን ችግሮች ስልጣን ላይ ካለው መንግስት በተሻለ መንገድ እፈታዋለሁ ብሎ ማሰብ ይጠይቃል። ይህንን ደግሞ መመለስ የምትችይው በጥናት ላይ ተመስርተሽ ነው ። በዚያ መልኩ ተቋቁመው ያንን ስራ እየሰሩ ያሉ ድርጅቶች በጣም ውስን ናቸው። ምርጫ ውስጥ የገቡት አብዛኞቹ ድርጅቶች እንደዚህ አይነት ነገር የላቸውም። አንዱ ምርጫውን አስቸጋሪ የሚያረገው በአማራጭ ደረጃ ለትምህርት ለጤና የኑሮ ውድነት ለማቃለል የወጣቱን ስራ አጥነት ለመቀነስ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግሮች ለመፍታት በሙሉ ጥናት አጥንተው መፍትሄያቸው ይሄ ነው ብለው የማይመጡ ናቸው።

90 በመቶ የሚሆነው ወደ ምርጫ የገባ ፓርቲ መሪ የአገሪቱን አመታዊ በጀት ስንት እንደሆነ የማያውቅበት አገር ላይ እንዴት ነው ፖለቲከኛ ነው የሚባለው? ምክንያቱም የአገሪቱን በጀት ስንት እንደሆነ አለማወቅ ማለት ስልጣን በሚይዝበት ጊዜ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለመከላከያ ምንያህል ማውጣት እንዳለበት አያውቅም ማለት ነው። ለወደፊት እሰራዋለሁ፣ እገነባዋለሁ ለሚለው ትምህርት ቤት፤ እፈጥረዋለሁ ለሚለው ስራ ብሩን ከየት እንደሚያመጣ አያውቀውም ማለት ነው። ሌላ አገር ላይ እንዲህ አይነት ፖለቲካ የለም። ስልጣን ይዘሽ በእያንዳንዷ ማኅበራዊ ክፍል የምታወጪያትን ወጪ ዘርዝረሽ፣ ደምረሽ ከአገሪቱ በጀት ጋር እንደሚስተካከል አሳይተሸ ነው ምርጫ የምትገቢው። ይሄንን አይነት ነገር ያልሰሩ የፖለቲካ ድርጅቶች በምንድን ነው ህዝብን ምረጡኝ የሚሉት። ይሄ ከምርጫ ጋር የተያያዘ ትልቁ ችግር ነው።

ሁለተኛ ቅድም ያልነው የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ጉዳይ ነው። በዛ በኩል የህግ ማስከበሩ ስራ ትግራይ ላይ አለ። ትግራይ ላይ የህግ ማስከበር ስራ ይሰራ እንጂ ከዛ ተነስቶ የነበረውና በሃሳብም ሆነ በገንዘብ ሌላ ቦታ ላይ አገር እንዳይረጋጋ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አሁንም አልበረደም። ስለዚህ ከትግራይ ክልል ውጪም ስፋት ባላቸው ቦታዎች ላይ የሰላምና መረጋጋት ችግሮች

 አሉ። እና ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ችግር ያለበት ቦታ ላይ የሚደረግ ምርጫ ነው። ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በተያያዘ ችግር ያለበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። በውጪም የዲፕሎማሲ ተጽእኖ ባለበት ነው ምርጫ ውስጥ የሚገባው። ስለሆነም ይሄ ምርጫ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ የሚደረግ ምርጫ ነው። ምርጫው መደረግ አለበት ተብሎ ተወስኗል።

እንደኔ ቢሆን ደጋግሜ የምናገረው ለሚቀርቡኝ ድርጅቶችም ያቀረብኩት ሃሳብ በትክክል ኢትዮጵያንና አገሪቱን የሚወድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አሁን ባለንበት ሁኔታ ከመንግስት ጋር መምከር የሚገባው የዛሬ አንድ አመት ተኩል በፊት ምንም ነገር ሳይኖር ኢትዮጵያ በዛን ጊዜ በነበረችበት ሁኔታ የአተካራ ፖለቲካ መሸከም የምትችል አገር ናት። የወጣቱ ስራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነት፣ በዲፕሎማሲው በኩል ከአባይ ጋር ተያይዞ ያለው ችግር፣ ነጻና ገለልተኛ የሚባሉ ለምርጫ አስፈላጊ የሆኑና ከምርጫ በኃላ አስፈላጊ ተቋማት ባልተገነቡበት፣ ኢኮኖሚው ከፍተኛ ችግር ውስጥ በገባበት ሁኔታ ጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን ምርጫ መደረግ አለበት ስላሉ ወይም ደግሞ በፈረንጆቹ ምርጫ ማድረግ የሰለጠነ ሀገር መገለጫ ነው ብለዋል ተብሎ የእነርሱን ፍላጎት ለማርካት ወደ ምርጫ መግባት አስፈላጊ ነው ወይ ? የአንድ አገር የፖለቲካ ችግር መፍትሄ ከአገሩ ከራሱ ነው መምጣት ያለበት። ምርጫ ማድረግ አያስፈልግም፤ ቅድሚያ መስጠት ያለብን አገር ወደ ማረጋጋት፣ ተቋማት መገንባት፣ በጋራ በተስማማንባቸው ፖሊሲዎች አማካኝነት የኑሮ ውድነትን፣ ስራ አጥነትን፣ የቤት ችግርን ማቃለል ከሆነ ለምን ስልጣን ላይ ካለው መንግስት ጋር በጋራ ተቃዋሚዎች ተስማምተው ከምርጫ ነጻ የሆነ የአምስት አመት እረፍት ለአገሪቱ አይሰጣትም።

ከዛ በኋላ ሁኔታዎች ታይተው፣ ተቋማት ተገንብተው፣ ኢኮኖሚው ትንሽ መልክ ይዟል፣ ወጣቱም ትንሽ ተስፋ እያየ ነው፤ ስለዚህ አሁን ተበታትነን በምርጫ መንገድ ብንገባ እና ሌላ ነገር ብንሞክር የተሻለ ነገር መስራት እንችላለን ወደሚል መሄድ ይሻላል ። እኔ ለምቀርባቸው ለተቃዋሚ ፖርቲዎች ግፉ ነበር ያልኳቸው። ምርጫ ለአገሪቱ ቀዳሚ አይደለም። በርግጥ የተለያዩ ፖለቲካ ድርጅቶች ምርጫ መደረግ አለበት፣ ካልተደረገ ስልጣን በህገ ወጥ መንገድ እንዲቀጥል ሊያደርግ ነው በሚል መንግስት ላይ ተጽእኖ ያደርጋሉ። መንግስትም አገሪቱ ምርጫ ማድረግ እንደማትችል ቢገባውም አሁን ባለንበት ሁኔታ ምርጫ ማድረግ አያስፈልግም ብሎ ያላግባብ ለማስቀጠል ስለፈለገ ነው የሚል አጣብቂኝ ውስጥ ነው የሚገባው። ስለዚህ ተቃዋሚዎችም ተሰብስበው ምርጫ አያስፈልግም የሚሉበት ሁኔታ፣ መንግስትም ደፍሮ ይህንን ማለት በማይችልበት ሁኔታ አገሪቱ ወደ ምርጫ እየገባች ነው።

ይህ ምንድን ነው ማህበረሰቡ የራሱን ሰላምና ጸጥታ በማስከበር፣ ስርዓት ባለው መንገድ ምርጫው ተጀምሮ እንዲያልቅ ማድረግ ይገባል። በተለይ ጤነኛ የሆኑት የፖለቲካ ድርጅቶች አባላትና ደጋፊዎቻቸውን ከምንም ነገር በላይ የምርጫ ውጤት የፈለገው ነገር ቢሆን በህጋዊ ሰላማዊ መንገድ ችግሮች ካሉ እንዲፈቱ ማገዝ ያስፈልጋል። ማሸነፍ የሚባል ነገር ሁሉም እንደማይችል ተሸናፊና አሸናፊ ሊኖር እንደሚችል አስቀድሞ ማስገንዘብ ጠቃሚ ነው። ያኮረፉ ደጋፊና አባላትን አሰባስቦ አገሪቱን ለግጭት መዳረግ የማይጠቅም መሆኑን ማስተማር ይገባል። ችግሩ ቀላል ነገር አይደለም። ወደ ምርጫ የምንገባው ፈጽሞ በማይመች ሁኔታ ውስጥ ነው ፤ ምርጫው አማራጭ የለውም ስለተባለ ነው።

አዲስ ዘመን:- ለችግሮቻችን ያሉ መፍትሄዎች ምንድናቸው ይላሉ፤ ከተግዳሮቶቻችን በላይ ያሉ ተስፋዎቻችንስ እንዴት ይገለጻሉ ?

አቶ አንዳርጋቸው:- ሁሉም ሰው መረዳት ያለበት ለሀገራችን ችግሮች ፈጣን ዕልባት/መፍትሄ / ማግኘት አይቻልም ። ማለትም ዛሬውኑ መድሃኒት ሰጥተሸ ዛሬውኑ የምታድኛት አይደለችም። ለረጅም ጊዜ በሽታ ውስጥ እንድትወድቅ ስራዬ ተብሎ የተሰራባት አገር ስለሆነች ችግሮቹዋን መፍታት ጊዜ መፍጀቱ አይቀርም። ትልቁ ቁም ነገር መሆን ያለበት በትክክል የአገሪቱ በሽታ ምንድን ? የሚለው ነው። ረጅም ጊዜም ቢወስድ ለረጅም ጊዜ መድሃኒት የሚሆኑትን መድሃኒት ዛሬ እያሰብናቸው ነው ወይ ? መሰረታቸው እየተጣለ ነው ወይ ? የእኔ ትልቁ ጥርጣሬና ስጋት ነው። አንዳንዶቹ መፍትሄዎች ጊዜ የሚፈጁ ቢሆኑም መሰረታቸው የዛሬ ሶስት ዓመት መጣል የነበረባቸው ስራዎች እየተሰሩ አይደለም የሚል እምነት አለኝ።

ሌሎች ቦታዎች ላይ የምናያቸውን አይነት ስራዎች እኩል በእኩል ጎን ለጎን መካሄድ ያለባቸው፣ የአገሪቱን መሰረታዊ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ ከሰው ግንባታ ጋር የተያያዙ ልክ እነ ሸገርን ማስዋብ ለመስራት እንደ ገበታ ለአገርና መሰል ተግባራት ሰው ተስፋና ሞራል ሊሰጡት የሚችሉትን አንዳንድ ነገሮችን በመስራት ለማሳየት የሚደረገውን ነገር በሙሉ ከእርሱ ጋራ ጎን ለጎን መሄድ የሚገባቸውን ነገሮች ትልቅ ጉዳት የደረሰበት ግንባታና ስልጠና ጋር የተያያዙ ነገሮች መሰረት ሊጣልባቸው ይገቡ ነበሩ።

እነዚህ ነገሮች ከፋፋይ ከሆነ አመለካከት ነጻ፣ አገራዊ የሆነ አመለካከት ያለው ህዝብን ብቻ አስቀድሞ የሚመለከት የተማረ የሰው ሃይል በተለይም ቁልፍ በሆነ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ዘርፎች ከመከላከያው አንስተሽ በመንግስት ሲቪል ቢሮክራሲው፣ በደህንነት ተቋም ውስጥ የሚገቡ፣ በአገሪቱ የሚዲያ ተቋማት በጋዜጠኝነት ውስጥ የሚሰሩ ሰዎችን በከፍተኛ ደረጃና ብቃት አሰልጥኖ በማውጣት ከፋፋይና ዘረኛ በሆነ መንገድ አገርና ህዝብን በማያስቀድም መልኩ የሚመለከትን የሰው ሃይል በፍጥነት የሚተኩበትን ሁኔታ ስራ መጀመር ያለበት የዛሬ ሶስት አመት ነበር ብዬ አስባለሁ ።

ለዚህ የሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች መሰረቱ መጣል ነበረበት። በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ምን አይነት ትምህርትና ስልጠና ነው እንዲህ አይነት ሰው የሚያበቃው የሚል ስርዓተ ትምህርት በሶስቱ ዓመት ምሁራን ተሰብስበው ቢሰሩ የቀጣዩ አመት ቢያንስ የመጀመሪያው ዙር ተመራቂዎች ያወጡ ነበር። የዚህ አይነት ረጅም ጊዜ የሚፈጅ የሰው አስተሳሰብ ካልቀየርሽ በልመና፣ በተማጽኖ፣ በሰበካ፣ በንግግር ልትፈቺ አትችይም። መሰረታዊ ችግር ያለው ሰው ላይ ነው። እናም ከዛ ጋር የተያያዘው ስራ ረጅም ጊዜ የሚፈጅ ነው። አንድን በተጣመመ መንገድ የተገነባን ትውልድ አስተካክሎ የማውጣት ስራ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ተቋማት ድረስ የሚያልፈውን የሚጠይቅ ነው። በመሆኑም አሁን ነው መጀመር ያለበት።

ሁለተኛው ነገር ጊዜያዊ የሆኑትን ችግሮች በተቻለ መጠን ብዙ ጉዳት ሳያደርሱ እየቀረፉ መሄድ ይገባል። ለምሳሌ አሁን ከምርጫ ጋር በተያያዘ ምርጫው ከነበረበት ደረጃ ወደ ከፋ ሁኔታ እንዳይወስደን ለማድረግ ጊዜያዊ ነገር በመንግስት ደረጃ በቂ ዝግጅት መደረግ አለበት። ትልቁ ነገር ሰላምና መረጋጋት የጸጥታ ጉዳይ ነው። ምን ያህል በተደራጀ መንገድ ሰላምና መረጋጋት በምርጫ ወቅት አሁን ካለበት ሁኔታ እንዳይደፈርስ በሚያደርግ ሁኔታ መንግስት ዝግጅት አድርጓል?

ይህንን ሃላፊት የሚወስዱት አካላት እርስ በእርስ እየተናበቡ ከምርጫ ቦርድ አካላት ጋር ይሁን፤ ከደህንነት መዋቅሩ ፌዴራል መከላከያ ሃይሉ ዝርዝር በሆነ መንገድ ጥናት ማድረጋቸውንና የትኛው ቦታ ላይ እንዲህ አይነት ችግር ቢከሰት ነገሮቹን በአጭሩ ሊከላከሉ ይችላሉ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል።

ሌላው ትልቁ ነገር በለውጡ ውስጥ የለውጥ ሃይሉ ለራሱም ሆነ ለአገር ችግር እንዲመጣ ያደረገው ትልቁ ድክመቱ የለውጡ ባለቤት የሆነውን ህዝብ ለውጡን በመከላከል፣ የራሱን ሰላምና መረጋጋቱን እንዲጠብቅ በማድረግ፣ የህግ የበላይነቱን በየአካባቢው እንዲያስከብር በማድረግ፣ በየአካባቢው የመንግስት ባለስልጣናት የሚያካሂዱትን የመሬት ወረራና መሰል ሌብነትና ዘረፋ ተደራጅቶ መከላከል የሚችልበትን አደረጃጀት ያለማምጣት ችግር አለ።

በጣም በቀላሉ የምታይው አዲስ አበባ መሬት ውስጥ የመንግስት መዋቅር የማይሰራውን በቀበሌ ደረጃ ያደራጀሽን ያለናንተ እውቅና አይሰጥም የሚል ከህዝቡ የተማረ፣ ሰላምና መረጋጋትን፣ የህግ የበላይነትን በተመለከተ ከህዝቡ የተመረጠ፣ የፓርቲ አደረጃጀት የሌለው ህዝቡ ራሱ የአካባቢውን የመሬት ወረራ፣ ሰላምና የህግ ችግሮች እንፈታለን የሚሉ በህዝብ የተመረጡ ሰዎች ከመንግስት መዋቅር ጎን ለጎን የሚሄዱበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ አብዛኛው ችግር ይቃለል ነበር።

አሁንም ከምርጫ ጋር በተያያዘ ቅድም ያልኳቸው ተቋማት ደህንነቱና ምርጫ ቦርድ አብረው መስራታቸው ብቻ ሳይሆን ከምርጫ ጋር በተያያዘ ምን ያህል ህዝብ በተደራጀ መንገድ የራሱን ሰላም፣ ደህንነት ለመጠበቅ ተዘጋጅቷል የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ነው። ከኢትዮጵያ ደህንነት በበለጠ ማን መሳሪያ በየመንደሩ እንደሚሸጥ፣ ህገ ወጥ መሳሪያ በቤቱ ማን እንደደበቀ፣ ማን ጸጉረ ልውጥ እንደሆነና መሳሪያ ይዞ በቅጥረኝነት በህዝቡም ሆነ በተቋማት ላይ አደጋ ለማድረስ እንደሚንቀሳቀስ ከነዋሪው ህዝብ በላይ የሚያውቀው የለም።

ህዝቡን ሳታሳትፊ በጣት በሚቆጠሩና በሚገባ ባልተደራጁ፣ አቅም በሌላቸው፣ በስራ ባህላቸው አገርና ህዝብን በማስቀደም ቀንና ሌሊት የመስራት ሞራልና ባህል በሌላቸው የመንግስት ባለስልጣናት የከተማና የአገርን ደህንነት መጠበቅ አይቻልም። እናም ህዝብን ያላሳተፈ ነገር ትልቅ ችግር ውስጥ የጣለን አንዱ ነገር ነው። በእዚህ ምርጫም ህዝቡን ያሳተፈ ነገር በማድረግ፣ አንድ ላይ ሆኖ በመስራት የሰላም፣ የጸጥታና የመረጋጋት ስራን መንግስት ሊሰራ ይገባል ።

አዲስ ዘመን፡– ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተጀመረበት አስረኛ ዓመት ላይ ሁለተኛው የውሃ ሙሌት በዝግጅት ላይ እንገኛለን። በአጠቃላይ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለእርስዎ ምን ማለት ነው ? በቀጠናው ከአባይ ውሃ ጋር ተያይዞ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አኳያስ ምን አይነት ጥንቃቄ መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ አንዳርጋቸው:- የታላቁ የህዳሴ ግድብ ህዝቡ ከፍተኛ መስዋዕትነትን ከፍሎበታል፣ ንዋይም አፍስሶበታል። ግድቡ ከዚህ በኋላ ምንም ማድረግ የማትችይው ነገር ነው። መጀመሪያ የህዳሴ ግድብ እንዴት ነው የተጀመረው፣ ትልቅ ግድብስ ያስፈልገን ነበር ወይ፣ በአለም ላይ እንዲህ አይነት ግድብ ለመገደብ የተደረጉ ሙከራዎች ከፕሮጀክት አፈጻጸም፣ ከበጀት አኳያ፣ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የፈጠሯቸው ችግሮች ብዙ ናቸው። እነዚህን አይነት ነገሮች ግምት ውስጥ አስገብቶና ታስቦበት የተጀመረ ግድብ ነው ወይ ? በዲፕሎማሲ ሁኔታ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮች የተገነባበት ቦታ በደንብ አድርጎ ለሚመለከት ሰው ይህ ግድብ ከመጀመሪያው ብዙ ችግር ያለበት እንደሆነ መዘንጋት የለብንም።

ሁኔታውን በብዙ መልኩ መተንተን ይቻላል። ኢትዮጵያ በጣም አነስተኛ ግድቦችን በመገደብ ከፍተኛ ወጪ ቀንሳ ኤሌክትሪክ ለማስተላለፍ የሚወጣውን ወጪ ጭምር ለመቀነስ በከፍተኛ ደረጃ የሚያስችላት በስፋት ያለውን ማህበረሰብ በኤሌክትሪክ ማዳረስ የሚያስችላት በአካባቢው መለስተኛ ግድቦች ማድረግ የምትችልበት በጣም ሰፊ ዕድል የነበረበት ሁኔታ ማየት የሚቻልበት ሁኔታ አለ። የአለምን የግድብ ሁኔታ ለሚመለከት ሰው ብዙ አጠያያቂ ጉዳዮች አሉ።

በርግጥ ይሄንን ጉዳይ ብዙም ባናነሳው ብንተወው ጥሩነው። ምክንያቱም በዛ ሰዓት ላይ ይህንን አገር ትልቅ መከራ ውስጥ የጨመረው መለስ ዜናዊና የወያኔ መንግስት የኢትዮጵያን ዘለቄታዊ ጥቅም ግምት ውስጥ አስገብቶ አባይ ላይ ግድብ ገንብቷል የሚል እምነት የለኝም። ስለዚህ ከግድቡ ኤሌክትሪክ ማመንጨት በላይ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅምና ብሄራዊ ደህንነት ግምት ውስጥ ያስገባ ነው የሚለውን ተረት እኔ አልቀበለቀውም። ሊያደርጉ የሚችሉ ሰዎች አይደሉም። ምክንያቱም ሌላ ቦታ ላይ አገር እያፈረሱ ያንን አይሰሩም፡ ስለሆነም እርሱን እንተወው። በተለያዩ ምክንያቶች ይሄ ነገር እንዲጀመር አድርገውታል፣ በጣም ከፍተኛ ሃብት ዘርፈውበታል፤ አንዱም እርሱ ሊሆን ይችላል።

ለእነ መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሸቀጥ ማራገፊያ ነው። ለራሳቸው ሰዎች ገንዘብ መዝረፊያም ነው። መለስ ዜናዊ ከራሱ ክብርና ዝና ጋር አባይን የገነባ መሪ ነው ብሎ እንዲሄድ ታስቦና የእርሱ ተላላኪዎች የእዛን ያህል ስም እንዲሰጠው ካደረጉት ነገር ጋር ሊያያዝ ይችላል። ግን በሚገባ ከተጠናና ከተመለከትነው ብዙ ነገሮች አሉት። እንደው የኢትዮጵያን ህዝብ በዛም በዚህ አድርገው ግድቡን በራሱ አቅምና ጉልበት እንዲገነባ አድርገውታል። ነዋይ አፍስሶበታል። በቃ! የእኔ ነው ብሎ ልቡንም፣ ነፍሱንም ከዚህ ግድብ ጋር አቆራኝቶታል። አሁን ምንም ማለት አንችልም። ተጀምሮ የሆነ ቦታ ላይ ደርሶ ነው ያለው። 10 አመቱ ነው ብለሻል፣ በአምስት አመት ይጠናቀቃል የተባለ ግድብ ነው አስር አመት የፈጀው። ከ10 ዓመት በኋላም ገና ጊዜ መፍጀቱ አይቀርም፣ በዓሉም በሚከበርበት ሰዓት በዋነኝነት የሚነሱ ጉዳዩች ምን ያህል ገንዘብ ፈሰሰበት፣ አምስት አመት ተብሎ አስር አመት ለምን እንደፈጀ፣ የፕሮጀክት አፈጻጸም ችግር ያለብን አገር መሆናችንን፣ በአስር አመት የውድቀትና የቅልጥፍና ውድቀት በዓል ልናከብር አይገባንም። እኔን በመድረኩ ላይ ብታስቀምጪኝ በማስተማሪያነት ነው እንጂ፤ በተለያዩ ዝግጅቶች፣ ምግቦችና መጠጦች አላከብርም።

በርግጥም ውሃ ሰጥቼ ነበር እንዲያከብሩት የማደርጋቸው። የሆነው ሆኖ እዚህ ደርሰናል። መጨረስ አለብን። ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ የሚባል ነገር አይደለም። መብራትም ወይም ሃይል ብቻ የሚያመነጭ አይደለም። ቅድም ያልሽውንም ጥቅም ይዞ መጥቷል። የእነ ግብጽ እብሪት ማስተንፈሻ ነው። በሌላ መንገድ ይቻል ነበር ግን ይሄ አሁን ትልቅ ተጽእኖ ማሳደሪያ ነው። ግብጽ በኢትዮጵያ ታሪክ በተከታታይ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እጇን እያስገባች ኢትዮጵያን ያላመሰችበት የታሪክ ዘመን የለም።

በርግጥ ከጥንት ጊዜ የነበሩ ነገስታት እንደ አንዱ እንደማስፈራሪያ በመጠቀም ግብጽ እንደውም አገሯ ላይ ባሉ ኮብቲክ ክርስቲያኖች ላይ እስራትና ሌሎች ነገሮች ስትፈጽም አባይን እንገድባለን በማለት እስከማስፈታት የሄዱበት ዘመን እንደነበረ የተመዘገቡ ታሪኮች አሉ። እናም ግብጽ ላይ ተጽእኖ ማሳደር የሚያስችል ከፍተኛ ጉልበት ያለው ነገር መሆኑ ግልጽ ነው። እኔ ብሆን በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ የምትገቡ ከሆነ እናንተም አባይን እንደህልውናችሁ ነገር ነው የምታዩት፤ እኛም በአባይ ጣልቃ መግባታችሁ ህልውናችንን እያናጋው ነው። ስለዚህ ለህልውናችሁ እንደምታደርጉት ጥንቃቄ እኛም ከማድረግ አንመለስም። አንዲት የግብጽ እጅ የገባበት ነገር አለ ከተባለ ወደ ኋላ አልመለስም ብዬ ነበር ፊት ለፊት የምነግራቸው። በዛ በኩል ትልቅ ፋይዳ ያለው ነገር ነው። የአባይ ግድብ ግብጽ እጇን እንድትሰበስብ የሚያደርግ ትልቅ ግድብ ነው።

ሌላው ያነሳሽው ጉዳይ ተጽእኖ እያደረጉ ነው ብለሽ ያነሳሽው ነው። እሱን ተቋቁሞ መጨረስ ነው። ዋናው ትልቁ ነገር በሌሎቹም ችግሮቻችን በዚህም ያለው ፈረንጆቹም ሆነ ሌሎች ያግዙናል፤ በእነርሱ ላይ የተመሰረተ መፍትሄ ይመጣል አይደለም። ዞሮ ዞሮ ኢትዮጵያውያን የሁሉም ነገር መፍትሄ ያለው በእጃችን ነው። እዚሁ አገር አምርረን ተርበንም ቢሆን ተሰቃይተን የማንንም ምጽዋትና እርዳታ ሳንፈልግ በራሳችን አቅም ማንኛውንም ችግራችንን መፍታት አለብን። ፈረንጆቹ እርዳታ በመከልከል፣ በሌላ ነገር የእኛን አገር አንገት ሊያስደፉ ይሞክራሉ። ደግነቱ እያየሁት ያለሁት የአብይ መንግስት በፊት ለፊት በሚናገራቸው ነገሮች ደሃዎች ልንሆን እንችላለን። ግን ክብራችንን አሳልፈን አንሰጥም የሚል ነው። ይሄንን የበለጠ አጠናክሮ መሄድ የሚገባው ነው።

በርግጥ ኢትዮጵያውያን በእንዲህ አይነት በነጮችና በሌሎቹ ኮርነር በምንደረግበት /በምንገለልበት/ ጊዜ በአንድ ላይ የመቆም የረጅም ጊዜ ባህል አለን። ወያኔ የቦረቦረው ቢሆንም ያ ባህል አሁንም ቢሆን አለ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሆነ ችግር ተፈጥሯል ቢባል ከመላው አገሪቷ ሰራዊት ሆኖ ለመነሳት የተፈለገው ቦታ ሄዶ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር መስዋዕትነት ለመክፈል ወደ ኋላ አይሉም። መንግስት በህዝቡ ላይ መተማመን አለው። በህዝቡ ላይ በሚተማመንበት ሰዓት ላይ መንግስትና የመንግስት ባለስልጣናት በሚናገሩበት ሰዓት ሕዝቡ እንዲያምናቸው እውነት ተናጋሪ መሆን አለባቸው። በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሕዝቡ ላይ በደል የሚፈጽሙ የራሳቸውን ሰዎች ዝም ብለው ማለፍ የለባቸውም። የችግርና የመከራ ዘመን ነው እስከተባለ ድረስ የመንግስት ባለስልጣናት ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ የአገሪቱ ባለሃብትም ጭምር ችግር ውስጥ ከሚወድቀው ስፋት ካለው ማህበረሰብ ጋራ ያለውን ተጋርቶ ለመኖር፣ ለማካፈል፣ ስፋት ያለው ማህበረሰብ የሚገባበትን ስቃይ ለመሰቃየት ዝግጁ መሆኑን በተለያየ መንገድ ማሳየት እስከ ቻልን ድረስ የፈለገውን ነገር ቢል፣ ቢፎክር ኢትዮጵያን ምንም ሊያደርጋት እንደማይችል ይታወቃል። ስለዚህ ትልቁ ስራችን ራሳችን ላይ ሊሆን ነው የሚገባው ብዬ ነው የማስበው።

አዲስ ዘመን:- ከጎረቤት አገራት ጋር በግድቡ ጉዳይ ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም። በዚህ ላይ የመንግስት አቋም ተገቢ ነው?

አቶ አንዳርጋቸው:- አካሄዱ ተገቢ ነው፤ ትክክልም ነው። ኢትዮጵያ ግልጽ በሆነ መንገድ አስቀምጣለች። ተስማሙም አልተስማሙም ትቀጥላለች። ካልተስማሙም ግልጽ ነው ውሃውን ትሞላለች። ዝም ብሎ እያስፈራሩ ኢትዮጵያ ሙሉ መብቷን መጠቀም በማትችልበት ሁኔታ ውስጥ ሊያስገቧት መፍቀድ የለባቸውም። መንግስትም ይሄንን ለህዝብ ግልጽ ማድረግ አለበት። በዚህ ደረጃ ግልጽ አድርጎ ቁርጠኛ አቋም እስከያዘ ድረስ ህዝቡ ይከተለዋል። እንደውም መንግስት በወላወለ ቁጥር ነው ንዴቱንና ቁጭቱን የሚጨምረው። ስለዚህ መወላወል አያስፈልግም። ዲፕሎማሲያዊ የሆነውን መንገድ በሙሉ መጠቀም ተገቢ ነው። ግን አግባብነት በሌለው መንገድ የዲፕሎማሲ ጫና አድርጎ ለመጉዳትና ለመበደል የሚደረግን ማንኛውንም ሙከራ ከህዝብ ጋር ሆኖ እምቢ ማለትና ወደፊት መቀጠል ያስፈልጋል።

ዝናብ ይመጣል፤ ኢትዮጵያ መሙላቷ አይቀርም፤ ግብጽ ያንን ምንም ማድረግ አትችልም። ግብጽ ምንም ማድረግ የማትችልበት ዋናው ምክንያቱ ምንድን ነው፤ ኢትዮጵያ እኮ ግብጽ ወዳልሆነ መንገድ ከገባች የአባይን ግድብ በጦርነት አንድ ነገር አደርጋለሁ ብላ ብትሄድ እኮ አባይን ለመገደብ የፈጀውን ያህል ኢትዮጵያ አይፈጅባትም፤ የአባይን ውሃ ለማድረቅ ከፈለገች።

በተለያዩ ቦታዎች ያሉ የአባይን ገባሮች በሙሉ ገድባ ለመስኖ ስራ አውላ 80 በመቶ መካከል አንድ በመቶ ውሃ ወደ ሱዳን እንዳያልፍ ለማድረግ ትችላለች። የማያዋጣቸው ነገር ነው። ያንን ካደረጉ ፈጽሞ እስከ ዛሬ ድረስ ገብተውበት ከሚያውቁት መከራ በላይ ኢትዮጵያ ልትጨምራቸው የምትችልበት ሁኔታ ነው ያለው። ይሄንንም ፊት ለፊት መናገር ያስፈልጋል። በሰላም ለሁላችን በሚጠቅም መንገድ እንፍታው። በሌላ መንገድ ሄዶ ሌላ ችግር እፈጥራለሁ ለሚል ከኢትዮጵያ በበለጠ ተጎጂዎቹ እናንተ ናችሁ። ኢትዮጵያ መከራና ችግር ተሸክሞ የራሱን ክብር መከላከል የለመደ ህዝብ ከግብጽና ከሱዳን ህዝብ በላይ መከራ ይቋቋማል። ፈትኑን እስቲ ማናችን እንደምንጎዳ ብሎ መጠየቅ ነው።

ጠብታ ውሃ እንዳያልፍ ማድረግ ትችላለች፤ በሁለትና በሶስት ዓመታት ውስጥ። ግድቡ እኮ ውሃ ለመስጠትና ለመከልከል አስፈላጊ አይደለም። ገባሮቹ ላይ በሙሉ መስራት ነው፤ አበቃ። ከዛ መስኖ ነው የሚሆነው። 85 በመቶ ባይገባበት እኮ ነጭ አባይ የሚገፋው ነገር ስለሌለ አስራ አምስት በመቶ ውሃ እንኳን አይደርስም። ኦምዱርማን ላይ ካርቱም ከተማ ላይ ተገናኝተው ጥቁር አባይ በሚሰጠው ተጨማሪ የውሃ ግፊት ነው ሺ ኪሎ ሜትሮ አቋርጦ በረሃው ላይ ይደርቅ የነበረው ነጭ አባይ። ስለዚህ ምንም ውሃ የሌላት አገር ልትሆን ትችል ነበር። ምንም ውሃ የሌላት ግብጽ ማለት እንደ አገር ከነፎቁ ከነምኑ በታሪክ የሚታወስ የከተማ ሃውልት ሆኖ ህዝቡ ወደሌላ አገር ሄዶ የሚኖርበት ሁኔታ ነው የሚፈጠረው። የመረረ ነገር ውስጥ ኢትዮጵያን መጨመር የሚጎዳው ግብጽን ነው እንጂ ኢትዮጵያን አይደለም።

አዲስ ዘመን:- የህዳሴ ግድብ ለጎረቤት አገራት ፋይዳው ምንድን ነው?

አቶ አንዳርጋቸው:- እነ ግብጽና እነሱዳን እኮ ህዳሴ ግድብ መገደብ በአግባቡ ጥናት ላደረጉ ሰዎች ይጠቀማሉ እንጂ የሚጎዱበት ነገር አይደለም። ብዙ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከእነርሱ ምክንያቶች መካከል አንዱ ግብጽ ላይ አስዋን ላይ ከሚያከማቹት ውሃ የበለጠ ከሚተን ውሃ የአየር ሙቀቱ ዝቅተኛ የሆነበት ቦታ የሚጠራቀም ውሃ ለእነርሱ የሚያተርፉበት ነገር ብዙ ነው። በተለያዩ የችግር ወቅቶችም የአባይን ግድብ በመክፈት በድርቅ ጊዜ ማግኘት የማይችሉትን የተጠራቀመ ውሃ ሁሉ ማግኘት የሚችሉበትን ዕድል የሚፈጥርላቸው ነገር ነው። ከግድቡ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይልም በተለይ ሱዳንንና ሌሎች አጎራባች አገራት ከፍተኛ የሆነ ሃይል መስጠት የሚችል ነው። በሁሉም መልኩ ለቀጣናው የኢኮኖሚ ፋይዳው በኤሌክትሪክና በሌሎች ነገሮች መተሳሰር ሲጀመር ኢኮኖሚው እየተሳሰረ ይሄዳል። አንዱ በአንዱ ላይ ተቀራርቦ የሚኖርበትን፣ የገበያ ትስስርን ያመጣል።

አዲስ ዘመን:- የህዳሴ ግድብ ከለውጡ በፊት ለብልሹ አሰራር ተጋልጦ እንደነበር አንስተውልኛል፤ አሁን ያለውን የፕሮጀክቱን አፈጻጸም እንዴት አገኙት ?

አቶ አንዳርጋቸው:- አሁን ያለው የለውጥ ሃይል ትልቁ ጥንካሬ ፕሮጀክቶችን በደንብ መቆጣጠርና መፈጸም ነው። የተጀመሩ ትናንሽ ነገሮችም እንደ ሸገር፣ የአንድነት ፓርክ፣ ገበታና ሌሎቹም ኢትዮጵያ ከሚለው ጋር ተሳስሮ የሚሰሩ ነገሮች የአባይ ግድብ ከተገመገመ በኃላ ያሉ ሁኔታዎች በጣም የሚያበረታቱ ናቸው ።

ይሄ ጥንካሬ የመጣው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ፕሮጀክቶች ማቀድና ማስፈጸም ጋር የተያያዘ ክህሎት ያላቸው ሰዎች በመኖራቸው ነው። አንዱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቁ አቅም፣ ፍላጎትም፣ እልህም ያለው ፕሮጀክቶች በጊዜ ተጀምረው በጊዜ ማለቅ አለባቸው የሚል ነገር መኖሩ ነው። አባይ ደግሞ ከሌሎቹ ትንንሽ ፕሮጀክቶች የበለጠ ትልቁ ፕሮጀክት ነው። ትልቁም የጠቅላይ ሚኒስትር ትኩረት እርሱ ላይ ያደረገ ነው የሚመስለኝ። እኔ የግድብ ነገር በጣም ውስብስብና አስቸጋሪ ነገር መሆኑ ቢገባኝም ሌሎች እኛ የማናውቃቸው ከፕሮጀክት ማኔጅመንት ውጪ የሆኑ ችግሮች ካልገጠሙት በስተቀር ከዚህ በኋላ እንደሌላው ጊዜ ገንዘብ የሚበላበትና ጊዜው በጣም የሚጓተትበት አይሆንም።

ማህሌት አብዱል አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2013


Related posts:

ደብዳቤ ለኢትዮጵያ - ከቢልለኔ ስዩም
የዓለም ባንክ የ300 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ፈረመ
"እናቴ ፍጹም እስር ቤት እንድትገባ አልፈግም" ብሎ እግሩን ያጣው ወጣት ምስክርነት ለሮይተርስ
"አልዘምትም" ወይም "ከጠላት ጎን እሰለፋለሁ" ማለት ሲቻል ማውሰብሰብና ማድበስበስ አይገባም!
አብዱላሂ ፋርማጆ ለአዲሱን ፕሬዝዳንት «ሁሉም ወገኖቼ እንዲደግፉህና እንዲጸልዩልህም እጠይቃለሁ»
መንግስ የጸጥታ ሃይሎች ለየትኛውም ዓይነት ትንኮሳ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ማድረጉን አስታወቀ
በትግራይ 5.2 ሚሊዮን ሕዝብ ዕርዳታ እየደረሰ ነው፤ ከሺህ በላይ የጭነት መኪኖች ታግተዋል፤ 76 ቢሊዮን ብር ወደ ትግራይ ተልኳል
የደህንነት ጥናት አዲሱ ምዕራፍ - ጂኦስፓሻል ኢንተለጀንስ
ዳግም ጦርነት እንዳይጀመር ስጋት የገባው ኢሰመኮ የማስጠንቀቂያ ጥሪ አሰማ
"ህሊናን የሚፈታተን" የተባለ ሪፖርት ይፋ ሆነ - አማራ ክልል በተወረረበት ወቅት ግብረርሰዶም መፈጸሙ ተገለጸ
ፊንላንድ 3.6 ሚሊዮን ሕዝብ የሚይዙ ዋሻዎች አዘጋጀች - ለኢትዮጵያውያን ጠቃሚ የጥንቃቄ መረጃ
"አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድንና የጥፋት ኃይል ዳግም ከሞከረ የማያዳግም ቅጣት ይጠብቀዋልʺ
ሻዕቢያና ትህነግ - ሰሞኑን ይህ ሆነ
ትህነግ ጦርነት እንደሚከፍት ይፋ አደረገ፤ አማራ ክልል "ለክተት ተዘጋጁ"አለ፤ መከላከያ በተጠንቀቅ ላይ ነው
ወልቃይት "የወር ስንቅህን አዘጋጅተህ ለክትተ ጥሪ ተዘጋጅ”

Leave a Reply