በዓለም ላይ ሰዎች በተደራጀ መንግሥት መተዳደር ከጀመሩበት ጊዜ አንሥቶ፣ መንግሥታት በሆነዉም ባልሆነዉም ሲፋለሙ መኖራቸዉን ታሪክ ይነግረናል። እንዲያዉም ታሪክ ራሱ የጦርነት ማስታወሻ ነው። ጦርነት በዉስጡ ያልያዘ የታሪክ መጽሐፍ እንደ አልጫ ወጥ ነው እሚቆጠረዉ፤በዓለም ዘንድ። የሃያኛዉ ክፍለ ዘመን ታሪክ በሦስት ወይም አራት አበይት ክስተቶች ሊጠቃለል ይችላል፦ አንደኛዉና ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነቶች፣ቀዝቃዛው ጦርነትና የምስራቁ ጎራ መሸነፍ:: ያለፈው ክፍለ ዘመን ዉስጥ ጎልተዉ የሚታዩ የታሪክ አዕማድ እኒህ ናቸው።
በያንዳንዱ አገር ዉስጥም ቢሆን ታሪክ፦ ስልጣን ለመቆናጠጥ የሚደረግን ሴራ፣ ግብግብና ፍልሚያ ከመከተብ የዘለለ አይደለም፡፡ የተራው ህዝብ ደስታም ሆነ ስቃይ ባብዛኛዉ ተመሳሳይ ስለሆነ እምብዛም አይጻፍም፡፡ ለቲያትር ተመልካቹ እንዳያሰለች፡፡ ጀግንነት ባብዛኛው ከጦርነት ጀብድ ጋር የታያዘው ታሪክ የጦርነት ፊልም ስለሆነና ዋና ተዋናዮቹ ጦረኞች ስለሆኑ ነው፡፡
ታላቁ እስክንድር የሚባለው የመቄዶንያ ጎረምሳ ግሪክን አስገብሮ፣ ፋርስን አንበርክኮ እስከ ህንድ ደረስ ዘልቆ፣ ግብፅን ቅምጡ አድርጎ፣ በጦር ከመግዛት የዘለለ ሥራ የለውም። ታሪክ የጦረኞች ስለሆነ ግን “ታላቅ” የሚል ቅፅል ተጨመረለት፡፡
ዓለም እስካሁን እንደ ሮማ፣ ኦቶማን ቱርክ፣ ብሪታኒያ፣ የሶቪየት ህብረት…የመሳሰሉ ሰፋፊ ግዛታዊ አስተዳደሮች (Empires) አይታለች። ባለፈዉ አንድ መቶ ዓመት የገነነችዉ ግን አማሪካ ናት። በምጣኔሀብት ድልበት፣ በጦር ሃይል ፈርጣማነት፣ በቴክኖሎጂ ልህቀት ከፊት ተሰልፋለች። ጭራሽ የቀዝቃዛው ጦርነት ካለቀ በኋላ ያለማንም ሃይ ባይነት እንዳፈነናት ስትሆን ከርማለች።
የቻይና ደረት ማበጥ፦
ቻይና ትልቅ አገር ናት፦ በታሪኳ ርዝመትም፣ በስነ ጽሑፍና ፍልስፍናዋ፣ በሌላዉም ስልጣኔዋ፣ እንዲሁም በሰፊው ግዛተ ምድሯ። እነ “ኮንፊሺዬስ” የስነ ምግባር ሥርዓት ሲዘረጉ፣ እነ “ሰን ዙ” ደሞ “ የጦርነት መላ/The Art of War” የመሰለ የውጊያና የአጠቃላይ ጦርነት ስትራቴጂ የነደፉት ገና ጠዋት ነበር፤ ከሁለት ሺ ዓመታት በፊት፡፡
ባለፉት አርባ ያህል ዓመታት ኢኮኖሚያቸዉን በነፃ ገበያ መንገድ ስላዋቀሩት ሀብታቸዉ በብዙ እጥፍ፣ እዉቀታቸዉ ባያሌዉ ጨምሯል። በተለይ በዘጠናዎቹ የዓለም የንግድ ድርጅትን (WTO) ቻይና ከተቀላቀለች በኋላ፣ ግዙፍ ግዙፍ የምእራባዉያኑ አምራች ድርጅቶች ወደ ቻይና ጎራ ብለዋል። ለምን?
1) ዓ. ን. ድ . ን የተቀላቀለ አገር ወደ ዉጪ በሚልካቸዉም ሆን በሚያስገባቸው ምርትና አገልግሎቶች ላይ አነስ ያለ ቀረጥ ብቻ ይጣልበታል/ይጥላል። በአባል አገራት መሐከልም አድሎ መፈፀም አይቻልም። ለማምረት የማይመቹ አገራት ግን ይህን ድርጅት በተቀላቀሉ ጊዜ፣ የሚያስገቡት እንጂ የሚልኩት ስለማይኖራቸዉ ለተዛባ ይንግድ ሚዛን ይጋለጣሉ።
2) በዚህ የተነሣ አንድን ምርት አሜሪካ ዉስጥ ሲያመርቱ ላንድ ግለሰብ በሚከፍሉት ደመወዝ አርባ ሰባት ያህል ቻይናዎች መቅጠር በመቻሉ ነጋዴዎች አትራፊ ሆኑ። እናም ወደ ቻይና  ጎረፉ፡፡
3) ሰፊ ገበያ ፍለጋ፡፡ ቻይና የህዝብ ቢሊየነር ናት፡፡ እዚያዉ አምርቶ  ያለብዙ ዉጣ ውረድ  ላገሬዉ ሰዉ መሸጥ ይችላሉ። የተረፈዉን መልሰው አነስ ባለ ቀረጥ ወደ ምዕራቡ ዓለም ይልካሉ።
ይህ ሁሉ ተደማምሮ አሁን የዓለምን ሁለተኛ ኢኮኖሚ፣ ከፍተኛ የጦር መሳሪያና የዲጂታል ቴክኖሎጂ (ለምሳሌ አምስተኛ ትዉልድ ወይም 5G ን በማስተዋወቅ ሁዋዌ የሚባለው የቻይና ኩባንያ ተጠቃሽ ነው) አሜሪካን መገዳደር ጀምራለች፡፡
በተጨማሪም አሜሪካ በአፍጋኒስታን፣ በኢራቅ፣ በሶርያ ብዙ ትሪሊየን ዶላር የፈጀ ጦርነት ስታካሂድ ( ላለፉት 20 ዓመታት)፣ ቻይና አድፍጣ የቤት ሥራዋን ስት ሠራ ነበር ይባላል፡፡
የሽኩቻ ሜዳዎች
1. የቀድሞ ያሜሪካ ሊቀ መንበር ዶናልድ ትራምፕ በቻይና ምርቶች ላይ ቀረጥ በመጣል የምጣኔ ሀብት ጦርነቱን ጀምሮታል። ዶናልድ ትራምፕ ባይጀምረው እንኳን የሚቀር ጉዳይ አልነበረም። የጊዜ ጉዳይ ነው። በዚህ የተነሣ በሁለቱ አገሮች ብቻ ሳይሆን ሦስተኛ ወገንም ብዙ ተጎድቷል (ለምሳሌ  ወድ ቻይና ጥሬ እቃ የሚልኩ አገሮች)፡፡
የአሜሪካ ክስ “ቻይና የዉጭ ኢንቨስተሮችን የፈጠራ መብት ትጋፋለች፣ የገንዘብ ምንዛሪ ታምታታለች፣ እንዲሁም እኛ በራችንን ከፍተንላት እሷ ግን የኛን ነጋዴዎች ታንገላታለች” የሚል አለበት፣ በክሱ፡፡
ከላይ እንደገለጥሁላችሁ ብዙ የአሜሪካ ድርጅቶች ለሠራተኞች የሚከፍሉትን ደሞዝ ለመቀነስ ወደ ቻይና በመኮብለላቸዉ ሥራ የፈታ ብዙ አሜሪካዊ አለ። በተለይ Mid West በሚባሉት የአሜሪካ ግዛቶች (ሚቺጋን፣ ዊስኮንሰን፣ ዒንዲአና…) ጉዳቱ በደንብ ታየ።
መድሃኒትን ጨምሮ ወሳኝ ምርቶችን ከቻይና ስለሚገዙ እንደ ብሄራዊ አደጋ ማየትም ጀምረዋል።
2. የደቡብ ቻይና ባህር፡፡ ቻይና በዚህ ባህር ላይ ሰባት ሠዉ ሰራሽ ደሴቶችን በገመንባቷ እና በደሴቶቹ ዙሪያ ያለው ባህር የግሌ ነው በማለቷ” Free and open Indo- pacific” ን አደጋ ላይ ጥላለች፡፡ ስለዚህ መርከቦቻችን እንደልብ እንዳይቀዝፉ አስቸግራለች ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ለፊሊፒንስ፣ ለቬትናም፣ እና እዛ አካባቢ ላሉ አገሮች የድንበር ጉዳይ ጭምር ነው፡፡ ከጃፓን ጋርም “ሲንካኩ” በሚባሉት ጃፓን ዉስጥ ባሉ ደሴቶች የይገባኛል ቁርሾ አለ።
3. ቴክኖሎጂ (ረቂቅ ዕደ ጥበብ) ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት የፈጠራ መብት እየጣሰች ብዙ ቴኖሎጂ ወስዳብናልች ባይ ናቸው። 5G የሚባለው ቀጣዩ የመረጃ ማቆሪያ፣ ማስተላለፊያና፣ ማቀናበሪያ ጥበብ ቻይና ዉስጥ ከአሜሪካ ቀድሞ በስፋት ሥራ ላይ ዉሏል፡፡
በ21 ኛው ክፍለ ዘመን ደሞ “መረጃን የያዘ፣ ሁሉንም አዘዘ” ሊባል ይችላል። የዲጂታል መረጃ አዲሱ የነዳጅ ሀብት ነው። ይሸጣል ይለወጣል። ለምርምር ይዉላል። ለጦርነት ይዉላል። ለንግድማ ባያሌው እየተጠቀምንበት ነው።
4. የአስተዳደራዊ ሥርዓት ተቃርኖ። የቀዝቃዛዉ ጦርነትን ማክተም ተከትሎ አሜሪካ ሁሉንም አገር “በኔ ዴሞክራሲ ተጠመቅ” እያለች አድራጊ ፈጣሪ ሁና ቆይታለች ቻይና ደሞ “ሕብረተ ሰባዊ” መንግስት ነው ያላት። የአሜሪካ አይነት ምርጫ፣ ነፃ ሚዲያ፣ ህግ መምሪያ፣ ህግ መወሰኛብሎ ነገር የላትም። የፓርቲው ተወካዮች ይሰብሰባሉ። ይወስናሉ።
በኢኮኖሚ የዳበረች፣ በወታደር የፈረጠመች፣ በቴክኖልጂ የተራቀቀች፣ ኮምዩኒስታዊ መንግስት ያላት ቻይና ለአሜሪካ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የራስ ምታት ሁና ትቀጥላለች። ብዙዎች እንደሚሉትም  ፓሲፊክ ዉቅያኖስ  የ21ኛ ክፍለ ዘመን አትላንቲክ ዉቅያኖስ መሆኑ አይቀሬ ነው( አትላንቲክ የ20ኛ ክፍለ ዘመን የታሪክ መድረክ ነብ። በምጣኔ ሀብትም፣ በጦርነትም)
ይዋጉ ይሆን?

via addisadmass


Leave a Reply