“እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ መንግሥት ኮሮጆ አይሰርቅም” ጠ/ሚ/ር ዐቢይ

መንግሥት በምርጫ ዙሪያ በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ካድሬ እስካለፈው እሑድ ድረስ ማሠልጠኑን፣ ማክሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደው የአዲስ ወግ ውይይት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ተናግረው፣ ዘንድሮ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ ፓርቲያቸው ብልፅግና ከተሸነፈ ሥልጣን ለማስረከብ ዝግጁ መሆኑን አስታወቁ።

“እንደ ብልፅግና ፓርቲ ከተሸነፍን ሥልጣን ለማስረከብ ተዘጋጅተናል። ይህንን ካደረግን ደግሞ ከምርጫ በኋላ ሰላም የማይኖርበት ምክንያት አይኖርም። አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ካድሬ እስካለፈው ቅዳሜና እሑድ ድረስ ሥልጠና ላይ ነበር። ዋናው መልዕክት ኢትዮጵያ አሸናፊ መሆን አለባት ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያ አሸናፊ የምትሆነው ሽንፈት ሲኖር በማመሥገንና መልካም በመመኘት ሥልጣን መስጠት ከተቻለ መሆኑን ገልጸው፣ “በታሪካችን ሆኖ ስለማያውቅ ለእኛም ጥሩ ነው አገርም ይቀጥላል። ብናሸንፍ ደግሞ ሰላማዊ ሆኖ ሰዎች ተሸንፈው ከሆነ እንኳን፣ በሒደቱ ጥርጣሬ በልቦናቸው ያላደረ ከሆነ ጠቃሚ ነው የሚል ውይይት አድርገናል” ሲሉ በካድሬዎች ውይይት ላይ የነበረውን ሐሳብ ጠቁመዋል።

ከዚህ ባለፈ እንደ ምርጫ 97 የምርጫ ኮሮጆ በመስረቅ የሚፈጠር ቀውስ እንደማይኖር፣ እንዲያውም እሳቸውን የሚያስፈራቸው ቅጥረኞች ወይም የተገዙ ሰዎች ራሳቸውን ከሕዝብ ጋር አመሳስለው በአንዳንድ ቦታዎች መራጭንና አስመራጭን በማጥቃት ጥፋት እንዳያስከትሉ እንደሆነ ተናግረዋል።

“በምርጫ 97 የገጠመንን ችግር ከአሁኑ ጋር እንዳታመሳክሩት። በምርጫ 97 ኮሮጆ የሚሰርቅ መንግሥት፣ ኮሮጆ የሚሰርቅ ፖሊስ፣ ኮሮጆ የሚሰርቅ አስፈጻሚና ድምፄ አይሰረቅብኝ የሚል ሕዝብ ነው የተጋጨው። እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ መንግሥት ኮሮጆ አይሰርቅም” ሲሉ ቃል ገብተዋል።

አሁን ችግር የሚያጋጥመው ኮሮጆ በመሰረቁ ብቻ ሳይሆን፣ ወጥቶ ለመምረጥ ዜጎች የደኅንነት ስሜት እንዳይሰማቸው ለማድረግ የሚፈልጉ፣ የተገዙ፣ በሽፍትነት የሚሠሩ፣ ዘር እየመረጡ የሚገድሉ፣ የኢትዮጵያን አንድነትና ህልውና የማይፈልጉ ኃይሎች መኖራቸው እንደሆነ ጠቁመው፣ “ነገር ግን ታጥቀውና ዩኒፎርም ለብሰው ስለማናገኛቸው፣ ተመሳስለው ስለሆነ የሚገኙት ጥፋት ሊያደርሱ ይችላሉ። እነዚህን መከላከል የምንችለው እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ሲወስድ ብቻ ነው። እያንዳንዱ ዜጋ መረጃ ከሰጠ፣ ሁኔታዎችን ለሚመለከተው አካል ካሳወቀ ከወዲሁ እየገመትን፣ እየለየንና እያወቅን ከሄድን የጥፋት ኃይሎችና ቅጥረኞች ጥፋት እንዳያመጡ ማድረግ ይቻላል” ብለዋል።    

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫውን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ያወሱት፣ በጣም ብዙ ኃይሎች ቋምጠው የሚጠብቁት ይህንን ምርጫ እንደሆነ ነው። በዚህ ምርጫ አማካይነት ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር መፍጠር ይቻላል በማለት ብዙ ሀብት የሚያፈሱ አገሮች እንዳሉ፣ ይህንን ችግር የሚገነዘቡና የሚያዩ ብዙ ሰዎች ምርጫው አያስፈልግም እንደሚሉ፣ ምርጫው ቅንጦት ነው የሚሉ ሰዎች ዝም ብለው ሳይሆን መከራከሪያቸው ችግሩን በማየት፣ የኢትዮጵያን ቀጣይነትና ህልውና ቅድሚያ በመስጠት ስለሆነ እንደሚጨነቁ አስረድተዋል።

ከዚህ ምርጫ ምንድነው የምናገኘው? ብዙ ተዋንያን ሊያጠፏት የሚፈልጓትን አገር በውስጥ ሳንግባባ ምርጫ ብለን ከነበረው ሁኔታ የዘቀጠ ነገር እንዳይፈጠር በማለት የሚሠጉ አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሥጋቱን አጉልተው ምርጫው ባይኖር እንደሚፈልጉ እንደሚናገሩ አስታውቀዋል። “በሌላ በኩል ደግሞ ምርጫው ባለመደረጉ ለረብሻና ለብጥብጥ እንደ ነጥብ ለመጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች ስላሉ፣ የመንግሥትን ቅቡልነት የሚያሳጡና ሰብሰብ ብለን ወደ ልማት ወደ ብልፅግና እንዳናተኩር የሚያደርጉ  ስላሉ ምርጫ ማድረግ አስፈላጊ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች አሉ” ብለዋል።

ምርጫው መካሄድ አለበት ወይም የለበትም ብሎ የሚወስነው አካል ለሚመጣው ውጤት ኃላፊነት የሚወስድ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ምርጫ አማራጭ መሆኑ አያጠራጥርም። አሁን በመድረኩ ወንድሞቼና እህቴ እንዳነሳችሁት እያንዳንዱ ዜጋ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን አውቆ፣ ጊዜ ስላለም ማንን እንደሚመርጥ እያሰበ ቆይቶ ከመረጠ በኋላ ድንጋይ የሚወረወር ከሆነ ግን በጋራ መቆም አለበት። በዚህ በሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ በከተማ ውስጥ ድንጋይ የሚወረውርና ውጤቱን ባለመቀበል የሚደረግ ተቃውሞ ይኖራል ብዬ አልጠብቅም። ሥጋቱ ግን የተገዙ አካላት ቀውስ እንዳይፈጥሩ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል።

“መጪው ምርጫ ዕድልና ችግሮችን ይዟል፤” በማለት ሁለቱንም ተገንዝቦ ለመምረጥ የሚነሳና የሚመርጠውን አካል ሕጋዊነት ያረጋገጠ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር፣ ይህን መሰል ውይይቶች እንደሚያስፈልጉ አሳስበዋል።

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊዎችና ልሂቃን የተሳተፉበት የአዲስ ወግ ውይይት “ሰላምና ደኅንነት በምርጫ ወቅት” በሚል ርዕስ በወቅታዊ ጭብጥ የተመረጠ ሲሆን፣ በሦስት ክፍለ ጊዜያት በተለያዩ ርዕሶች የሚካሄድ ነው።

ማክሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ማለዳ የተካሄደው የመጀመርያው ክፍል የአዲስ ወግ ውይይት በሰላማዊ ምርጫ መገለጫዎችና መሥፈርቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ከቀትር በኋላ የተካሄደው ክፍል በምርጫ ወቅት ሰላምን ለማስፈን ሰላምን የሚያንፁ አገር በቀልና ዘመናዊ ተቋማት ሚና ተዳሰዋል። ባለ ሦስት ክፍሉ የአዲስ ወግ ፍፃሜ ረቡዕ መጋቢት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ሐሰተኛ መረጃ በሰላማዊ ምርጫ ላይ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ መግታት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ እንደሚካሄድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያስረዳል። (ሪፖርተር)

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ


 • ጃል መሮ በትግርኛ – ከትህነግ ጋር ሲመክር ተጠለፈ ” 70 ከመቶ ጨርሰናል አዲስ አበባ ነው የቀረን”
  የአሜሪካ ድምጽ ማንነቱን ሳይጠይቀውና ሳያውቅ ሰፊ ቃለ ምልልስ በተደጋጋሚ ሲያደርገልት የነበረው ጃል መሮ በትግርኛ ከትግራይ ስሙ ካልተገለጸ ባለስልጣን ጋር ስለሚያካሂዱት ኦፕሬሽን ሲመክሩና መረጃ ሲቀባበሉ የሚያስረዳ ድምጽ ሆነ። ሌላው ቢረሳ በኢሬቻ ብቻ ከስምንት መቶ ሰዎች በላይ ሰዎችን የጨረሰ ትህነግ ከመላው ኦሮሞ ጋር ህብረት እንደሌለው በማስረዳት በተዘጋጀው ዶክመንታሪ ዝርዝሩን ይመልከቱ። ኦሮሞ በሃዘንናContinue Reading
 • “ወታደራዊውን ጉዳይ ለእኛ ተውልን” ሌ/ጄ አበባው ታደሰ
  “እናንተ ደጀን በመሆን ከጀርባችን ሁኑልን እንጂ ወታደራዊ ጥበቡን ለእኛ ተውልን” የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታምዦር ሹም ሌ/ጄ አበባው ታደሰ ማስታወቃቸው ተሰምቷል። መከላከያ ሰራዊትንም ሆነ ደጀኑንን ሕዝብ በወሬ ለማተራመስ ተከፍሏቸው የሚሰሩ፣ አገር ወዳድ መስለው የሚቀስቀሱና በባንዳነት አገር እያስመቱ ያሉ ላይ ሕዝብ እርምጃ እየወሰደ መሆኑም ተሰምቷል። ጠላትንም ለመመከት ህዝብ እየጎረፈ ነው። “ኢትዮዽያ እየሞትንContinue Reading
 • አሜሪካ የባድመ ጉዳይ በውሳኔው መሰረት ተግባራዊ እንዲሆን ጥሪ ማቅረቧን አስታወቀች
  አሜሪካ የባድመ ጉዳይ ሁለቱ አገሮች ቀደም ሲል በ2008 የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ በደረሱበት ስምምነት መሰረት ተግባራዊ እንዲሆን ስታሳስብ መቆየቷንና ሁለቱ አገሮች ይህንኑ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ ማሰማቷን አስታወቀች። “ባለፉት ጥቂት ሳምንታት አብዛኞቻችሁ ባድሜን አመልክቶ አሜሪካ (ያላት ወይም የያዘችው አቋም ለማለት ነው) ፖሊሲ ምን እንደሆነ ስትጠይቁን ነበር” ይላል የአሜሪካ መንግስት አስመራ በሚገኘው ኤምባሲውContinue Reading
 • የሽብርተኛው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የሠራዊታችንን የድል ግስጋሴ አይገታውም !
  ሽብርተኛው ከሚታወቅባቸው ስልቶቹ መሀል አንዱ ቅጥፈቱ ነው ፡፡ ጉልበት ሲያንሰው ምላሱ ይረዝማል ፤ ያልሆነውን ሆንኩ ፣ ያላደረገውንም አደረኩ…ይላል ፡፡ ይህ ደግሞ ጥርሱን የነቀለበት እና ተወልዶ ያረጀበት ባህሪው ነው ፡፡ አንድም ቀን ከአፉ እውነት ተገኝታ የማታውቀው ይህ ሽብርተኛ ፣ ሽንፈቱን የሚሸፍነው የሠራዊታችንን ስም በማጠልሸት ነው ፡፡ ደጋፊዎቹ ኪሳራውን እንዳያወቁ ፣ ሰላማዊውContinue Reading

Leave a Reply