May be an image of Belay Bayisa, beard, suit and outerwear
በላይ ባይሳ

ሃገርን የመምራት ተግባር በተወሰኑ አመራሮች ብቻም የሚፈፀም ተግባር አይደለም። ይልቁንም በትውልድ ቅብብሎሽ በተተኪዎች የሚፈፀም ረጅም ጉዞ ነውና።ካልሆነ ግን በየጊዜው ድንገት ሳያስበው ወደ አመራርነት የሚመጣ ድንገቴ “አመራር” ልክ እንዳልተሟሸ ጀበና ይሆንና ሃገር ስትገነፍል ትቀጥላለች።


ምጣድም ሆነ ጀበና በደንብ ከተሟሸ እንጀራውም ያምራል ቡናው ይጣፍጣል። ነገር ግን ያልተሟሸ ምጣድ እንጀራ እና ያልተሟሸ ጀበና ቡና አይጣፍጥም። እንጀራውንም ይበጣጥሰዋል/ያቀልጠዋል፤ ቡናውንም ያገነፍለዋል! በተመሳሳይ በሃሳብ ልዕልና ያልበለፀገና በመሠረታዊ ሃገራዊ አጀንዳዎች ላይ ውህደት የሌለው ፖርቲም እንደዚሁ ነው።

በተመሳሳይ ሃገር ስትመራ አሻግሮ በሚያሳይ የሃሳብ ልዕልና የተቃኘ ውህደት ባለው አመራር ካልተዋቀረ ከፋይዳው ይልቅ ሃገራዊ ጉዳቱና ስብራቱ ከፍተኛ ነው። አንዳንዱ ልዩነትን ብቻ በማጉላት እና አንድነትን በማኮሰስ ተጠምዶ ግራ ገብቶት ግራ እያጋባ ይውላል። ሌላው ደግሞ ልዩነትን ጨፍልቆ አሃዳዊነትን ያቀነቅናል። ሁለቱም ሚዛኑን ስቷል።

በመሰረቱ ተተኪ እና የተሟላ የፓለቲካ ስብእና የተላበሰ አመራር የመፍጠር ስራ በአንድ ጀምበር የሚሰራ ስራ ሳይሆን ረጅም ሂደት የሚጠይቅ በእቅድ የሚመራ፣ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ግብ ያለው ተግባር ነው።

በኢትዮጵያ ታሪክ፣ በፓለቲካና ኢኮኖሚ፣ ባህል፣ በማህበራዊ ጉዳዮችና፣ በማህበረሰቦች ስነ-ልቦናዊ አወቃቀር፣ በንፅረተ-ዓለሙና ፍልስፍና እንዲሁም ሞራላዊ እምነቱ ላይ የጠራ አረዳድ እና ወጥነት ያለው አቋምና ግንዛቤ ስለሌለው እንዴት ሃገር መምራት ላይ ልበ-ሙሉ የጠራ ግንዛቤ ሊኖረው ይችላል?

ለዚህም አይደል ህዝቡን ዥዋዥዌ እና ጉተታ ሲያጫውት የሚውለው?ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር ብልፅግናም ሆነ ሌሎች ፖርቲዎች በድርጅታዊ ዲሲኘሊን የታነፀ እና የተቃኘ አመራርን የማፍራት እና የማብቃት ስራ በመስራት የተሟላ የፖለቲካ ስብዕናና ብቃት የተላበሰ እንዲሁም ስለሃገሪቱ የተሟላ ሁል-አቀፍ አተያይ እና አረዳድ ያለውን ሰው የመፍጠር ከፍተኛ ሃላፊነት አለባቸው።

ሁሉም ነገር የሚሰራው ብቃት እና ፅናት ባለው አመራር ሲሆን ውጤታማ ይሆናል። እድገትም ይመዘገባል።ሃገርን የመምራት ተግባር በተወሰኑ አመራሮች ብቻም የሚፈፀም ተግባር አይደለም። ይልቁንም በትውልድ ቅብብሎሽ በተተኪዎች የሚፈፀም ረጅም ጉዞ ነውና።ካልሆነ ግን በየጊዜው ድንገት ሳያስበው ወደ አመራርነት የሚመጣ ድንገቴ “አመራር” ልክ እንዳልተሟሸ ጀበና ይሆንና ሃገር ስትገነፍል ትቀጥላለች።

ይህን ስል ግን ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆኑም ከፍተኛ የአመራር ክህሎት፣ ችሎታና ብቃት ያላቸውን በታማኝነት እና በትጋት ሃገራቸውን እያገለገሉ ያሉትን ውድ የሃገሬ ልጆች ከነጉድለታቸው አለማድነቅና አለማክበር እንዲሁም እውቅና አለመስጠት ግን ንፉግነት ይሆናል። በዚህ ፈተና ውስጥ በችግር የተተበተበችውን ሃገር መምራት ፈተናው ምን ያህል እንደሚከብድ ያላወቁ ሰማይ ቅርቡዎች ግን ብዙ ሊሉ ይችላሉ።

ሲጠቃለል እንደ ሃገር ከፍተኛ የአመራር ብቃትና ችሎታ ክፍተት በእጅጉ ስለሚስተዋል ጠንካራ ሰው በመለየት ወደ አመራር የማምጣት ስራ ላይ ከላይ እስከ ታችኛው መዋቅር ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል። ምን ለማለት ነው “… መርጦ ለታቦት” እንደሚባለው ሰዎችንም መርጦ ለፓለቲካ ማሟሸት እና ማዘጋጀት ቁልፍ ተግባር ሊሆን ይገባል።

በላይ ባይሳ መጋቢት 23/2013 ዓ.ም

ማስታወሻ – ለመግቢያ የተጠቀምነው ምስል የጸሃፊው ምርጫ አይደለም። ዝግጅት ክፍሉ ሃሳቡን ይወክላል በሚል አምኖ የተጠቀመው ነው። ሃሳቡ ግን የጸሃፊው እምነትና ሃሳብ ብቻ ነው


Leave a Reply