በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች ተከስቶ የነበረውን ግጭት ተከትሎ በደረሱ ጉዳቶች ዙሪያ የፌደራል መንግሥትና የክልሉ መስተዳደር ምርመራ እያካሄዱ መሆኑን የዞኑ አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ገልፁ። በዞኖቹ ውስጥ ከሁለት ሳምንት በፊት ተከስቶ የነበረውን ግጭት ተከትሎ ከደረሱ ጉዳቶች መካከል ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከተለቀቀው ዘግናኝ ተንቀሳቃሽ ምስል ጋር ተያይዞ በሸዋሮቢት የተከሰተ ነው በተባለው ጥቃት ዙሪያም ምርመራ እየተደረገ መሆኑ ገልጸዋል።

በዚህ ጥቃት ዙሪያ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረ ጻዲቅ ከፌደራል እና ከክልል መንግሥታት የተውጣጡ ቡድኖች በአጠቃላይ በደረሱ ጉዳቶች ላይ ጥናት ምርመራ መሆኑ እና የምርመራው ውጤትም ይፋ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።

የፌደራል ፖሊስ፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲን ጨምሮ የሚገኙበት ቡድን በጥቃቱ ዙሪያ ምርመራ እያደረጉ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፣ እስካሁንም በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች አለመኖራቸውን እና፤ ሂደቱ ሲጠናቀቅ በድርጊቱ ውስጥ ተሳትፈው የሚገኙ ሰዎች ለሕግ እንደሚቀርቡም አረጋግጠዋል።

በአንቡላንሱ ላይ ተፈፀመ ስለተባለው ጥቃት ዝርዝሩ ክስተት የተጠየቁት አስተዳዳሪው፣ ምርመራው እየተካሄደ መሆኑን አስታውሰው ውጤቱ ሲጠናቀቅ እንደሚገለጽ አመልክተዋል።

እየተደረገ ስላለው ምርመራ ከፌደራል ፖሊስና ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።

ክስተቱ እንዴት ተፈጠረ?

በጅሌ ድሙጋ ሰምበቴ ጤና ጣብያ የድንገተኛ ሕክምና የጤና ባለሙያ የሆነው አህመድ አልይ ወደ ሸዋሮቢት ለሕክምና ከሄዱት ግለሰቦች ጋር አብሮ ከሄዱ ሰዎች መካከል አንዱ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

አንቡላንሱ ላይ ጥቃት ሲደርስም በስፍራው እንደነበር እና ከጥቃቱ አምልጦ መትረፉን ይናገራል።

አቶ አሕመድ እንደሚለው መጋቢት 11/2013 ዓ.ም በአጣዬና በአካበቢዋ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት በርካታ ሰዎች ወደ ሰምበቴ ጤና ጣብያ ለሕክምና እየመጡ ነበር።

ወደ ሕክምና ተቋሙ ከመጡ ሰዎች መካከል ሁለቱ ጉዳታቸው ከፍተኛ ስለነበር ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ሆስፒታል እንዲሄዱ መወሰኑን ያስታውሳል።

ስለዚህም እነዚህን ሰዎች ሸዋ ሮቢት በሚገኘው ይፋት ወደሚባል የግል ሆስፒታል ለተሻለ ሕክምና እንዲሄዱ ተደረገ።

የጅሌ ድሙጋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጀማል ሐሰን ደግሞ እነዚህ የተጎዱ ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸው “ወደ ሸዋ ሮቢት መላካቸው ላይ ስጋት እንደነበረ” ይገልጻሉ።

የነበረውን ሁኔታ ሲገልፁም “ወደ ሸዋ ሮቢት ሪፈር ከተጻፈላቸው በኋላ ሕዝቡ አደጋ ይደርስብናል የሚል ፍርሃት ነበረው። በመንግሥት አካላት ግፊት ማለትም በእኛ ግፊት ነው እንዲሄዱ ያደረግነው። ስለዚህ ከሁለት ምቡላንስ በተጨማሪ በአንድ መኪና ፖሊሶችን አብረን ላክን” ይላሉ ።

አህመድ እና በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች በሸዋ ሮቢት ይፋት ሆስፒታል ሲደርሱ የሕክምና ባለሙያዎች የሉም መባላቸውን ያስታውሳል።

“በሁለት አምቡላንስ እና በአንድ ፖሊስ መኪና ሆነን ይፋት ሆስፒታል ስንደርስ የተወሰኑ ነርሶች እንጂ ዶክተሮች አልነበሩም። ወደ ሌላ ሆስፒተል አድርሱ አሉን። ከሆስፒታሉ እየወጣን በነበረበት ወቅት መንገድ ተዘግቶብን ቆምን” ይላል።

አሽከርካሪዎች እና የጤና ባለሙያ ከመኪና ሲወርዱ ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች እና አብረው የመጡ ቤተሰቦቻቸው መኪና ውስጥ እንደነበሩ ይናገራል።

“ምን ማድረግ አለብን ብለን ቆመን እየተመካከርን ባለንበት ወቅት የፀጥታ ኃይል መጥቶ ከበበን። መሳሪያቸውንም ሲያቀባብሉ እኛ የሰላም ሰው ነን ብለን ነገርናቸው። በመካከል ኃላፊያቸው መጥቶ ዶክተሮቹን አስፈራርታችሁ ሕክምና ለማግኘት ጥረት እያደረጋችሁ ነው አለ” ይላል አህመድ።

የነበረው ሁኔታ እየተባባሰ ሄዶም ውጥረት በመንገሱ ለማሳከም ከመጡ ሰዎች መካከል አንዱ በፍርሃት ዘሎ ሲሮጥ ከየት እንደተተኮሰ በማይታወቅ ጥይት ተመትቶ ወደቀ።

ተኩስ ከተሰማ በኋላ ረብሻ ተፈጠረ ይላል የሕክምና ባለሙያው። ከብበው የነበሩ ወጣቶችም ወደ አምቡላንሱ ሮጠው በመሄድ ጥቃት አደረሱ ብሏል።

እስካሁን ድረስ የአማራ ክልል ፖሊስም ሆነ አስተዳደር ይህንን በሚመለከት የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።

በዚህ መካከል የጤና ባለሙያው እና ሁለቱ ሾፌሮች ወደ መንደር ውስጥ ሲሸሹ አንድ ወጣት ቤት ውስጥ በማስገባት እንደ ደበቃቸው ይናገራል።

አንደኛው አሽከርካሪ ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት ቀድሞ መሸሹን ጤና ባለሙያው ጨምሮ ያስረዳል።

በጥቃቱ በሁለት አንቡላንስ ውስጥ የነበሩ ሁለት ታካሚዎች እና አብረዋቸው የነበሩ ለሕክምና የመጡ ስድስት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን ጨምሮ አስረድቷል።

“ማታ ረብሻው ከተረጋጋ በኋላ ወደ ሁለት ሰዓት አካባቢ ከዚያች ክፍል ውስጥ አውጥተው ወደ ፖሊስ ጣብያ አደረሱን። ከዚያም ወደ ፌደራል ፖሊስ ካምፕ ወስደው እዚያ አደርን። እነርሱም ወደ ሰምበቴ አደረሱን” ሲል የነበረውን ሁኔታ ያስረዳል።

የጅሌ ድሙጋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጀማል ሐሰን ወደ ሕክምና እየሄዱ በነበሩ ሰዎች ላይ የተፈፀመውን ይህ ጥቃት ግጭቱን ይበልጡኑ እንዳባባሰው እና አሁንም ትልቅ ስጋት ጥሎ ማለፉን ያስረዳሉ።

“. . . የከፋ ግጭት ያገጣመው፤ ግጭቱ በሙሉ ወረዳችን እንዲስፋፋ ያደረገውም ይኸው ነው፤ የሕዝቡንም ሥነ ልቦና በጣም ጎድቷል።”

ከዚህ ጥቃት በኋላ የተለያዩ ጉዳቶች ደርሶባቸው ወደ ጤና ጣብያ የሚመጡ ግለሰቦች፣ ነፍሰ ጡር እናቶች ለተሻለ ሕክምና ወደ ሸዋ ሮቢት እንዲሄዱ ሲታዘዙ እምቢ እንደሚሉ ያስረዳሉ።

ከሁለት ሳምንት በፊት በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞኖች የተከስቶ ለቀናት በዘለቀው ግጭት ምን ያህል ሰው እንደሞተ በውል ባይታወቅም በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን በንብረትም ላይ ከፍተኛ ውድመት ማጋጠሙን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አካባቢዎቹ በአሁኑ ጊዜ የተረጋጉ ሲሆን በርካታ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው የእለት እርዳታና የመልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍን እንደሚፈልጉ ተገልጿል።

ዝግጅት ክፍሉ ፥ መረጃው ሙሉ ስእል ባያሳይም፣ የኦነግ ታጣቂዎች ምንጫቸውን ባያሳይም፣ ኣምቡላስ ውስጥ በነበሩ ንጹሃን ላይ የደረሰውን ክፉ ተግባር ያሳየና ሃላፊዎች ያረጋገጡት በመሆኑ ኣትመነዋል። BBC Amharic


Leave a Reply