SOCIETY

ጭው ባለ በርሀ፤ እንደ እሳት በሚፋጅ ሙቀት ውስጥ ፤ አንዲት ትንሽ መንደር….

መጋቢት 25 ቀን 2013 "ድንበር ተሻጋሪው ህዝባዊነት"

ጭው ባለ በርሀ፤ እንደ እሳት በሚፋጅ ሙቀት ውስጥ ፤ አንዲት ትንሽ መንደር….

የሁለቱ ሱዳኖች የግጭት ቦታ በነበረችው ፣ በአብዬ ደቡባዊ ሴክተር በ24ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ የግዳጅ ቀጠና ውስጥ የምትገኝ ‘አንቶኒ መንደር ‘….

በመንደሯ ውስጥ ትንንሽ የሳር ጎጆዎች አለፍ አለፍ ብለው ይታያሉ።
በእነዚህ ጎጆዎች ውስጥ የሚኖሩ የመንደሯ ነዋሪዎች በጦርነት የተጎዱና በመሠረተ ልማት እጦት ከባድ ስቃዮችን ያሳለፉ መሆናቸውን ከፊታቸው ላይ በቀላሉ ለመረዳት የስነልቦና ባለሞያ መሆን አይጠበቅም።

በተለይ ፤ በሰላም እጦትና በእርስ በእርስ ግጭት ምክንያት ትልቅ ዋጋ መክፈላቸውን በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል።

የ24ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ የሠራዊት አባላት ፤ ለነዚህ ሠላም እንደ ውሀ ለጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በፀጥታና ደህንነት ጉዳይ ዙሪያ ወትሮውንም እንደሚያደርጉት ለመወያየት ከጎሳ መሪዎች ፣ ከፓሊስ ኮሚኒቲዎች፣ እንዲሁም ከሴቶችና ወጣት ተወካዩች ጋር ከረፋዱ 3 ሰዓት ጀምሮ ለውይይት ተቀምጠዋል።

ውይይቱ ከተጀመረ ጀምሮ ስለ ኢትዩጵያ መከላከያ ሰራዊት ጀግንነቱ ፣ ህዝባዊ ወገተኝተቱና ቁርጠኝነቱ እንዲሁም በአካባቢው ስላበረከተው ሠላም በስፋት ተነገረ ፤ ሰራዊታችን ተወደሰ ፤ ተሞካሸ።

በሌላ በኩል ደግሞ ህብረተሰቡ ፤ ሰራዊቱ ካበረከተልን የሰላምና ፀጥታ ቱርፋቶች ባሻገር ቢደግፈን በማለት አሉብኝ ያሏቸውን ችገሮች አቀረቡ ። በተለይ…ትኩረቴን ከሳቡት ሀሳቦች መካከል፤

” ከብቶቻችንን ወደ ግጦሽ ለማሰማራት በሚወጡ ልጆቻችን ላይ የሚከሰቱ እንደ በእባብ መነደፍ፣ በድንገተኛ የተሽከርካሪ አደጋ መጎዳትና የወላድ ሴቶች በህክምና እጦት የሚደርስባቸው የሞት አደጋ ይገኙበታል።

…..ጉዳታቸውን አሰብኩት ችግራቸው ውስጤ ድረስ ዘልቆ ተሠማኝ
በውይይቱም እነዚህንና ሌሎች ጉዳዩችን በማንሳት ምክክሮች ተደረጉ በስተመጨረሻም ፣ የሻለቃው ዋና አዛዥ ማጠቃለያና የመፍትሄ ሀሣብ ያሉትን ተራ በተራ ማስደመጥ ጀመሩ

” ….ሀገራችን ኢትዩጵያ የአምባሳደርነት ማዕረግ አልብሳ ወደዚህ ቀጠና ስትልከን የእናተን ችግር ለመቅረፍና የሠላምና የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት ስለሆነ ባሳለፍናቸው ወራቶች አንድም የሰው ህይወት እንዳይጠፋና ከብቶቻችሁ እንዳይዘረፉ ጥበቃ እንዳደረግነው ሁሉ ወደፊትም አጠናክረን እንቀጥልበታለን” በማለት ማብራሪያቸውን ቀጠሉ….

” ድንገተኛ አደጋ የሚገጥማቸው ዜጎችንም እንደ ሠላም አስከባሪ ብቻ ሳይሆን እንደ ወንድምም ጭምር ሆነን በምትሰጡን መረጃ መሰረት ድጋፋችንን እናደርጋለን” በማለት ቃላቸውን ሰጡ።

በዚህ መሀል ድንገት አንዲት ነፍሰጡር እናት በመንገድ ላይ ሳለች ከፊት ለፊቷ የመጣ ሞተር ሳይክ ይገጫትና ትወድቃለች ።

የአካባቢው ነዋሪዎችም በሁኔታው ተደናግጠው ተጎጂዋን ከወደቀችበት አፋፍሰው ያነሷታል ።ያቺ ምስኪን ነፍሰጡር እናት በአፍና በአፍንጫዋ ደም መፍሰስ ይጀምራል። ያኔ በቦታው የነበሩ የመንደሯ ነዋሪዎች በአካባቢው ምንም አይነት የህክምና አገልግሎት መስጪያ ተቋም እንደሌለና ወደሌላ ቦታ ደግሞ እንደይወስዷት ምንም የትራንስፓርት አማራጭ አለመኖሩን ሢያውቁ ተስፋ በቆረጠ ስሜት ውስጥ በመሆን ማልቀስ ጀመሩ።

በዚህ ግዜ አንድ ተለቅ ያሉ አባት በመጡበት አቅጣጫ በግምት 1ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከዋናው መንገድ ገባ ባለ ዛፍ ስር በውይይት ላይ የነበሩ የሠላም አስከባሪ አባላትን መመልከታቸው ትዝ አላቸው ። ወዲያው ነፍሰጡሯን ተጎጂ በመሸከም ከተሰብሳቢው መሀል በማምጣት እርዳታ እንዲደረግላቸው ተማፀኑ።

በውይይቱ ላይ የነበሩ የሰላም አስከባሪው አመራሮችና የህብረተሰቡ ተወካዩች ተደናገጡ ።

ውይይቱ ተቋረጠ…..

የሻለቃው ዋና አዛዥም የእጅ ሬዲዩናቸውን በማንሳት ወደ ሻለቃው ማዘዣ ጣቢያ በመደወል በፍጥነት አምፑላንስና የህክምና ባለሙያዎች እንዲመጡ አዘዙ።

በደቂቃዎች ፍጥነት በቦታው የደረሰው የህክምና ቡድኑ ጉዳት የደረሰባትን ነፍሰጡር እናት ከሞት ለመታደግ የሚያስችላቸውን ስራ መስራት ቻሉ።በስብሰባው ላይ ታዳሚ የነበሩት የህብረተሠብ ክፍሎችና ጎሳ መሪዎች በአድናቆት እንደተደመሙ የተቋረጠው ስብሰባ ቀጠለ ።

የሻለቃው የሠራዊት አመራርና አባላት ነጋሪም መስካሪም ሳያስፈልጋቸው ህዝባዊነታቸውን በተግባር ለተሰብሳቢው ለማሳየት በቁ። .....እውነትም ድንበር ተሻጋሪው ህዝባዊነት.....

መቶ አለቃ ልደት አስረስ – ከአብዬ via FEDE Defence Force


Categories: SOCIETY

Tagged as:

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s