“የምናስተውላቸው ሀገራዊ ፈተናዎች እንደ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን እንደ ማኅበረሰብም መውረዳችንን አመላካቾች ናቸው፡፡” ረ/ፕ ሽመልስ ኃይሉ

በታሪክ አጋጣሚ ጠንካራ እና ታላቅ ሀገረ-መንግሥት የገነቡ ሀገሮች ለታላቅነት የበቁበት ታላቅ ሚስጥር ሀገራዊ እሳቤዎችን ከውስጣቸው ስለገነቡ ነበር፡፡ ከፈረንሳይ እስከ እንግሊዝ፣ ከጀርመን እስከ ጣሊያን፣ ከአሜሪካ እስከ ጃፓን፣ ከቱርክ እስከ ደቡብ ኮሪያ፣ ከሩሲያ እስከ ቻይና የምናያቸው የዓለም ታላላቅ ሀገራት እና መንግሥቶቻቸው የተፈጠሩት ከፍ ካለ ሀገራዊ ሃሳብ እንጂ ከልዩነቶቻቸውማ ለተደጋጋሚ ጊዜ ሞክረውት አላዋጣ ሲላቸው ተምረውበት አልፈዋል፡፡

በዓለማችን በየአካባቢው የሚፈጠሩ ጥቃቅን አንጃዎች እና የጎበዝ አለቆች የሀገር እና ሕዝብ ማሳያ ሆነው መታየታቸው የትኛውንም ሀገር በየትኛውም ጊዜ የትም አላደረሱም፡፡ ኢትዮጵያ የራሴ የምትለው ሕዝብ ስብጥር ውጤት እንጂ የሄደው ነቅሎ የመጣው ተክሎ እንዳሻው የሚሠራት የነገስታት እና መንግሥታት ድንኳን አይደለችም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለልዩነት፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፍላጎት እና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ ግለሰባዊ እና የቡድን መብቶቹን እኩል የሚያስከብር መንግሥት እና መንግሥታዊ ስርዓት መፍጠር ካልተቻለ ትልቅ ሀገር በትንሽ አስተሳሰብ መገንባት እንዴት ይቻላል?

በወቅታዊ የሀገሪቱ ፈተናዎች ዙሪያ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ከሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልሽ ኃይሉ ጋር የስልክ ቆይታ አድርገናል፡፡

ፖለቲካ እና ፖለቲከኛ በሕዝቦች መካከል የነበረን የቀደመ ልዩነት አክስሞ ሀገር የሚያፀና እንጂ ባለፈ ልዩነት መካከል ሽብልቅ እያስገባ ስንጥር የሚፈጥር ከሆነ የታላቅ ሀገረ-መንግሥታዊ እሳቤ መጨንገፍ ካልሆነ ትንሳዔን ማብሰር ይከብደዋል፡፡ በቀበሌ መታወቂያ የሚኖር እንጂ በቀበሌ እሳቤ የሚያኖር ፖለቲከኛ ሀገር ከመገንባት ይልቅ ሀገርን መለያየት ይቀናዋል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ሀገራዊ ፈተና ምክንያቶቹ የበዙ ቢሆኑም ምንጩ ግን የፖለቲካ እና ማኅበረሰባዊ ስሪቶቻችን ከትናንቱ ይልቅ ዛሬ መቀንጨር እየተስተዋለባቸው መሆኑን የሚያመለካክት ነው ባይ ናቸው፡፡

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ እይታ ኢትዮጵያዊያን በአንድ እንዲኖሩ የሚያስችላቸው ፍቅር ስላላቸው ብቻ አይደለም፤ እጣ ፋንታቸው በአንድ የተገመደ ስለሆነ ጭምር እንጂ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ትግሬ ያለ አማራ፣ አማራ ያለ ኦሮሞ፣ ኦሮሞ ያለ ሱማሌ፣ ሱማሌ ያለ አፋር ተነጣጥለው መኖር እንዳይችሉ ሆነው ተገምደዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያንን ጋብቻ፣ መልካ ምድር፣ ማኅበረሰባዊ ስሪት፣ ምጣኔ ሃብታዊ እጣ ፋንታ እና ከምንም በላይ ኢትዮጵያን እንደ ኢትዮጵያ በጋራ ለማቆም የከፈሉት ታሪካዊ መስዋዕትነት መቼም እንዳይለያዩ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል፡፡

See also  ማን ነው ቀውስ የሚጠምቅልን? ከቀውሱ ብሁዋላስ? አዲስ አበባ መርዝ ታቅፋለች

ኢትዮጵያዊያን ይህን ያክል ለመለያየት እና ለመገፋፋት የማይመች ማኅበረሰባዊ ትስስር ካላቸው አሁናዊው ሀገራዊ ፈተና እንዴት ተፈጠረ? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ ሲመልሱ “የምናስተውላቸው ሀገራዊ ፈተናዎች እንደ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን እንደ ማኅበረሰብም መውረዳችንን አመላካቾች ናቸው” ይላሉ፡፡

ላለፉት ዘመናት የትምህርት ስርዓታችን ሰው መስራት አልቻለም፡፡ ለዚህም ሳይንሳዊ እውቀት፣ የሕይዎት ፍልስፍ እና ምርምሮች የሚከናወንባቸው የትምህርት ተቋማት ይህ ነው የሚባል ሀገራዊ ፋይዳ ሳይስተናገድባቸው እና የሀገር ፍቅር ሳይሰበክባቸው አልፈዋል፡፡ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ አማኝ ሕዝብ ባለባት ሀገር፣ የበዛ መስጂድ፣ እልፍ ቤተ ክርስቲያን እና በርካታ ቤተ አስተምሕሮዎች በከተሙባት ሀገር ከሰውነት በታች የወረዱ ተግባራት ሲፈፀሙ መመልከት ከእነዚህ ቤተ እምነቶች አስተምሕሮ ይልቅ የፅንፈኞች ስብከት ቦታ እያገኘ ለመምጣቱ ግልፅ ይሆናል፡፡

እነዚህ ሁሉ ችግሮች ቢኖሩም ፖለቲካችን እና ፖለቲከኞቻችን አሁንም የልዩነቶቻችን ሽብልቅ እየሆኑ መጥተዋል የሚሉት የፖለቲካ ምሁሩ በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ከዚህ ቀደም ያበላሸናቸውን እድሎች ዳግም ላለማበላሸት ቁጭ ብሎ መምከር እና የሚያዋጣውን መንገድ መምረጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ሀገር እየመሩ ያሉ ፖለቲከኖች የዛሬ ሥራዎቻቸው የነገ ታሪክ አንድ አካል ስለሚሆን ካለፈ ታሪካችን መማር የዚህ ዘመን ፖለቲከኞች እና መሪዎች የሥራ ጅማሮ መርህ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ ምክረ ሐሳብ መሪ እና ፖለቲከኛ ሰፊ ሀገራዊ ራዕይ ሊኖረው ይገባል፡፡ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን ብርቱ ፖለቲከኛ እና መሪ ስለማንነቱ የሚናገረው ከኢትዮጵያዊነቱ ሚዛን ተመስርቶ ነው፡፡ ፖለቲከኞቻችን በውስጣቸው ያለው ምዕናብ ካልተሰለበ በቀር ሰፊነትን ያልማል ያሉት የፖለቲካ ምሁሩ በትንንሽ ቡድኖች ታጥረው የጎጥ ሀገር የመመስረት እሳቤ ያላቸው ልሂቃን ፈሪ፣ አልጠግብ ባይ ውይም ሰነፎች ናቸው ነው ያሉት፡፡

አሌክሳንድር ከግብፅ እስከ አፍጋኒስታን የሰፋው በውስጡ ሰፊ ራዕይ ስለነበረው ነው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ እስከ እየሩሳሌም ያለመው በውስጡ ሰፊ እና ጠንካራ ሀገር የመመስረት ፅኑ ፍላጎት ስለነበረው ነው፡፡ አፄ ምኒልክ እስከ ናንዚያ ባህር የሚሻው ለራሱ ጠቦት ሳይሆን ለሰፊ ሀገር የመኖር ህልም ስለነበረው ነው፡፡ አሉላ አባነጋ “ፈረሴ የቀይ ባሕር ውሃን ሳትጠጣ አልመለስም” ያለው ሰፊ ሀገራዊ ራዕይ በውስጡ ስለነበረ ነው፡፡

See also  Watch IndieBio Accelerator's Demo Day Today

በአራቱም ማዕዘን በዱር በገደል የወደቁ ቀደምት ጀግኖቻችን ዛሬም በዚህ ትውልድ ልብ ውስጥ የማይጠፉት ሰፊ ሀገራዊ ራዕይ ስለነበራቸው እና ለራዕያቸው ሲሉ ራሳቸውን መስዋዕት ስላደረጉ እንደሆነም ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ ኃይሉ አስገንዝበዋል፡፡ እናም ፖለቲከኞች ከኋላቸው የሚከተል ሰፊ ሕዝብ አለና ከመጥበብ ይልቅ መስፋት፣ ከሰፈር ይልቅ ሀገር እና ከስሜት ይልቅ ስሌትን ሊያስቀድሙ ይገባል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው. (አሚኮ)

Leave a Reply