በሀገሪቱ የሚገኙ ጥቂት የዶሮ እርባታ ማዕከላት በገጠማቸው የመኖ እጥረት ሊዘጉ ጫፍ መድረሳቸውን የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎች ማህበር ፕሬዚዳንትና የሀዋሳ ዶሮ እርባታ ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገነነ ተስፋዬ አስታወቁ።

ፕሬዚዳንቱ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ በሀገሪቱ አሁን እየታየ ያለው የዶሮ በተለይም የእንቁላል እጥረት የተከሰተው ማባዣ ማዕከላቱ በገጠማቸው የመኖ እጥረት መሆኑን አመልክተዋል።

ማዕከላቱ የተቀነባበረ መኖ በተወሰነ መጠን ከውጭ የሚያስገቡ፣ ከሀገር ውስጥ የኑግ ፋጉሎ፣ አኩሪ አተርና በቆሎን በስፋት ይጠቀሙ እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፤ በአሁን ወቅት ከዘይት አምራቾች ግብዓቶቹን ማግኘት እንዳልቻሉ ጠቁመዋል።ዋጋውም 1800 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኩንታል የኑግ ፋጉሎ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በእጥፍ ጨምሮ 3400 ብር መግባቱን አመልክተዋል።

ዘርፉ የዓለም ሥጋት በሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተጎዳ ቢሆንም ከመስከረም 2013 ዓ.ም ጀምሮ መነቃቃት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም የመኖ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ ተመልሶ ችግር ውስጥ መግባቱን አስታውቀዋል።

ከዋጋው መናር ባለፈም ምርቱን ማግኘት እንዳልተቻለ የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፤ ለዚህም ዘይት አምራቾች ጥሬ ዕቃውን ወደ ውጭ ገበያ መላክ እንዲችሉ ፈቃድ ማግኘታቸውና በመኖ ላይ ከዚህ ቀደም ያልነበረ ቫት መጣሉ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም በዘርፉ ከተሰማሩ 22 የዶሮ አርቢዎች ማዕከል ውስጥ እርሳቸውን ጨምሮ ስድስት ብቻ የቀሩ ቢሆንም እነሱንም ለመዘጋት ጫፍ መድረሳቸውን ጠቁመዋል

(ኢ ፕ ድ)

Leave a Reply