የአባይ ግድብ ሁለተኛ ሙሊት እንዳይከናወን ግብጽ ከሰማይ በታች ማንኛውንም አማራጭ እንድትጠቀም…

ከሁለት ወራት በፊት ግብጻዊው ምሁር ያሰራጩት መልዕክት የግብጽን ቀጣይ አካሄድ የሚጠቁም ነበር። የአባይ ግድብ ሁለተኛ ሙሊት እንዳይከናወን ግብጽ ከሰማይ በታች ማንኛውንም አማራጭ እንድትጠቀም የሚገፋፋ፡ የሚያበረታታ ነው። ይህ ጽሁፍ በአንድ ምሁር ቀረበ እንጂ የግብጽ መንግስትን እቅድ በጎን እንድናውቀው ሆን ተብሎ የተደረገ ለመሆኑ አሁን ላይ ከሚሆኑት ክስተቶች ተነስቶ መግለጽ ይቻላል። ጽሁፉ በግልጽ የሚለው ሁለተኛው ዙር ሙሊት እንዳይከናወን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ውስጣዊ ቀውስ ማጦዝ፡ ማዕከላዊ መንግስቱን የሚያዳክሙ በተለይም ደግሞ በቁጥር ትልቅ የሆኑትን ሁለቱን የኢትዮጵያ ብሄረሰቦችን ወደለየለት ግጭት ውስጥ ማስገባት የሚል ያልተሸፋፈነ በግልጽ ቋንቋ የተላለፈ መልዕክት ነበር የተሰራጨው።

ግድቡ የሚገኝበትንም አከባቢ ማተራመስ የግብጽ ስውር አጀንዳ መሆኑ በጽሁፉ ላይ ተንጸባርቋል። በአማራው ላይ ዘግናኝ ግድያዎች እንዲፈጸሙ ማድረግ የተልዕኮው መሰረታዊና ቁልፉ እርምጃ እንዲሆን ታቅዷል። ንጹሃንን በብዙ ቁጥር በአሰቃቂ ሁኔታ መግደል ጉዳዩን የበለጠ ያከረዋል፣ በዚህና በዚያ በብሄር አጥር ውስጥ የተሰለፉ ሃይሎችን በቀላሉ ወደ ግጭት ውስጥ ያስገባል ብሎ የታመነበት እንደሆነ በግብጻዊው ምሁር መጣጥፍ (የግብጽ ስውር ፕሮጄክት) ውስጥ ሳይድበሰበስ በግልጽ የተቀመጠ መልዕክት ነው።

የሚሰማው ሳያሳዝን ቀርቶ አይደለም። ወለጋ ላይ የሚቀነጠሰው የሰላማዊ ዜጎች አንገት ልብን በሀዘን ሳያኮማትረውም አይደለም። የአማራ ተወላጆች በማንነታቸው ምክንያት ታላቁን ግፍ እየተቀበሉት መሆኑን ለመካድ አይደለም። ዛሬ ያየነውና የኦሮሞ ተወላጆችን በደቦ ፍርድ ሰቅጣጭ ሞት የተፈጸመባቸው ወገኖቻችን ሁኔታ ውስጥን ሳይረብሽ በመቅረቱም አይደለም። ከዚህ የከፋ እንዳይመጣ ምን እያደረግን ነው? የጀመርነው የፈንግጪውና ፈንክቺው ብሶት የወለደው ቅስቀሳ ከየት ያደርሰናል? መፍትሄ የሌለው፣ በብሶት ጀምሮ በቁጭት የሚጠናቀቀው የሰሞኑ ፍጥጫ መፍትሄ ከሌለው ነገ ሌላ ዙር የከፋና የበለጠ እልቂት እንደማይፈጸም ምን ዋስትና አለን? ይህ አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለመከላከል አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ቅዱስ አድርጎ ሃጢያትን የመሸፋፈን ጉዳይ አይደለም።

ከኢትዮጵያ የሚበልጥ ምንም ነገር የለም። ከኢትዮጵያውያን ህልውና በላይ የሚያስጨንቅ ምንም ምክንያት አይኖርም። የተያያዝነው የመጠነቋቆልና ጣት የመቀሳሰር አዝማሚያ መጨረሻው ማንን ተጠቃሚ፣ የትኛውን ወገን ተጎጂ እንደሚያደርግ ተረድተናል ብዬ አላምንም። ሁሉም ከሳሽ፣ ሁሉም ብሶተኛ በሆነበት በዚህን ወቅት ስሜትን ያዝ አድርጎ ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና እንድትወጣ፣ ይህቺን የጭንቅ ጊዜ እንድትሻገር በአስተዋይነት የሚንቀሳቀስ ጠፍቶ ባየሁ ጊዜ ነገ አስፈርቶኝ እንደአንድ ትንሽዬ ፍጡር ስጋቴን ለመግለጽ የሞነጫጨርኩት ስሜቴ ነው።

See also  ትህነግ ሲዘጋ፤ ኢትዮጵያ ትወቀሳለች- እስከመቼ በዚህ ይቀጥላል?

በመጨረሻ አሸናፊው ማን ነው? በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ጸንቶ የሚቆም የኦሮሚያ መንግስት ይኖራልን? የአማራን ቤተመንግስት ባህርዳር ላይ ማቆም ይቻላልን? የትግራይ ልዑላዊ መንግስት ከመቀሌ ይመጣልን? ቆም ብለን ማስብ የሚገባን ወቅት ላይ ነን። ኢትዮጵያ ፈርሳ የሚመሰርት የብሄር መንግስት ፈጽሞ አይኖርም። እንደዩጎዝላቪያ ውድ ስድስት መንግስትነት የምንሸነሸንበት እድል እንኳን የለንም።በዚሁ ከቀጠልን በዩጊዝላቪያ መበጣጠስ የምንቀናበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ካራና ስለት ይዘን እርስ በእርስ የምንተላለቅበት እንጂ በሰላም አጥራችንን አጥረን የምንኖርበት ቀጠና ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም።

ኢትዮጵያዊነት ስለፈለግነው ሳይሆን ምርጫ ስለሌለን የምንሞትለት እውነት ነው። የትኛውም ብሄርተኛ ዛሬ ስለጮኸ ኢትዮጵያዊነት የማያስፈልግ ተራ ማንነት ሆኖ ሊታይ አይገባውም። ፖለቲካዊ እንቅስቃሴአችንና አቋማችን ስሜት የሚጋልበው፣ ብሶት የሚነዳው ስለሆነ እንጂ ኢትዮጵያዊነት ለሁላችንም ፈውስ መድሃኒታችን መሆኑ ድምቅ ብሎ የሚታይ ሀቅ ነው። አይደለም ለእኛ ለምስራቅ አፍሪካ ብሎም ለአፍሪካ፣ ከፍ ካለም ለመላው ዓለም የሚበጀው የኢትዮጵያ መጠንከር ነው። ምርጫ የሌለው የምንጊዜም እውነት ነው። አዋራው ሲሰክን፣ ደመናው ሲጠራ ለተሰወረብን ያኔ ይገለጥልን ይሆናል።

አሁን የምንሰቃየው በበሽታችን ምልክቶች ነው። የእርስ በእርስ ፍጥጫችን በራሱ በሽታችን አይደለም። ምልክት ነው። እየተናጨን ያለነው በበሽታችን ምልክቶች እንጂ በዋናው ደዌ ሆኖ እያሰቃየን ባለው ጉዳይ እንዳልሆነ የተገለጠልን አይመስለኝም። የእኛ በሽታ የውጭ ሃይል ነው። የእኛ የዘመናት ሰንኮፍና ህመማችን ታሪካዊ ጠላቶቻችን ናቸው። በስልጣን ላይ ያለው መንግስትም የዚሁ ሰለባ መሆኑን መረዳት አለብን። ከምልክቶቹ የተሻገረ ለበሽታችን መድሃኒት መፈለግ ግድ ይላል። አብይ ይውረድ ብሎ ጩኸት ባዶ ድንቁርና ነው። መድሃኒት የሌለው ህክምና ትርጉም የለውም። መፍትሄ የሌለው ብሶትና ቁጭት የትም አያደርሰንም። ፈጣሪ ይታረቀን!

Via Mesay Mekonene Fb

Leave a Reply