ዛሬ የመንግስት ሚዲያዎች የአማራና ኦሮሚያ አመራሮች በዝግ እየመከሩ እንደሆነ ዘግበዋል። ስብሰባው በጸጥታ ጉዳይ፣ በሚፈናቀሉ፣ በሚገደሉ፣ መብታቸው በሚጣስ ዜጎች ጉዳይ ሲሆን አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላቸው እንደሆነ ከሌሎች ወገኖችም እየተሰማ ነው።

መሰብሰባቸውን ተከትሎ አንድ ባለሃብት ” በስብሰባ አብረው ወስነው ሲያበቁ፣ አብረው ተሳምምተው ሲያበቁና አብረው እጃቸውን አንስተው ካጸደቁ በሁዋላ በፌስ ቡክ እየወጡ አሽሙር የሚያሰራጩ የሁለቱም አመራሮች ከዚህ ተግባራቸው ካልተቆጠቡ ስብሰባ ዋጋ የለውም ” ሲል አስተያየት ሰጥተዋል።

የአንድ ገዢ ፓርቲ አባል ሆነው ሚና ለይተው በማህበራዊ ሚዲያ የሚታኮሱት የአማራና ኦሮሞ ካድሬዎች ሕዝቡን ግራ እያጋቡ እንደሆነ በብዛት ይሰማል። አንዱ ነዳፊ፣ አንዱ ተነዳፊ፣ አንዱ ተንኳሽ ሌላው መልስ ሰጪ እየሆኑ እንደ ውርጋጥ በማህበራዊ ሚዲያ የሚመላለሱት ካድሬዎች አንዳንዴ የሚያነሷቸው ሃሳቦች ” በነዚህ ከመመራትስ ” የሚያሰኝ ነው።

በረባ ባልረባው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ እየወጡ የሚንተከተኩ፣ እነሱን ተከትለው የሚያጫፍሩና አጋጣሚውን እየጠበቁ የቅዠት “የተራራ ስብከት” የሚያሰሙ ተዳምረው ህዝቡን ለመከራ፣ ለርስ በርስ ግጭት፣ ለመፍናቀልና ለዘግናኝ ሞት ከመዳረግ የዘለለ ፋይዳ ስለማያመጣ ሁሉም ወገን ጋብ ሊል እንደሚገባ መሃል ሰፈር የሆኑ በብዛት እየመከሩ ነው።

ዛሬ የተጀመረው የሁለቱ ክልሎች ስብሰባ መሰረታዊ ውሳኔ የሚጠበቅበት እንደሚሆን ለጉዳይ ቅርብ የሆኑ እየገለጹ ነው። የሁለቱ አቋም የመንግስት አቋም ስለሚሆን በጉጉትም የሚጠበቅ ነው። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሚከተለውን ዘግቧል።

የኦሮሚያ እና የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች በጋራ ልማት እና ሰላም ጉዳዮች ላይ እየመከሩ ነዉ፡፡በምክክር መድረኩ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የሰላም እና የጸጥታ ችግሮችን ተቀናጅቶ ለመከላከል በትብብር መስራት የሚቻልበት ሁኔታ ልዩ ትኩረት መሰጠቱም ነው የተገለጸው፡፡

በሁለቱም ክልሎች የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ተከትሎ በንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለዉን ሞትና መፈናቀል በፍጥነት ማስቆም፣ የግጭቱ ጠንሳሾች እና ተዋናዮች ላይ አስፈላጊዉን እርምጃ መዉሰድ፣ በተከሰቱ ግጭቶች ጉዳት የደረሰባቸዉ ወገኖች ፍትሕ እንዲያገኙ እና ወንጀለኞች ለሕግ እንዲቀረቡ ማድረግ፣ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው በፍጥነት መመለስና ማቋቋም እንዲሁም በክልሎቹ ዘላቂ ሰላም ከማስፈን አኳያ በትብብር ለመሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች በመወያየት ላይ ይገኛሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የኦሮሞ እና የአማራ ወንድማማች ሕዝቦች ዘመን ተሻጋሪ ትስስርና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከር፣ አጎራባች ዞኖች ላይ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችን በተቀናጀ ሁኔታ መከላከል፣ በሁለቱ ክልሎች መካከል እየተሠሩ ያሉ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የዉይይቱ አንኳር ጉዳዮች ናቸው።

በመድረኩ የሁለቱም ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ሲሆን፤ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር እና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ምክክሩን በጋራ እየመሩት መሆኑን አብመድ ዘግቧል።


Leave a Reply