ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከተመራው የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአውሮፓ ህብረት ልዑክ መሪ ሚስተር ፔካ ሀቪስቶ ጋር ውይይት አድርገዋል።በውይይታቸውም ለትግራይ ክልል የሚሰያስፈልገውን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የኢትዮጵያ መንግስት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሚሸፍን መሆኑን ጠቅሰው እስካሁን ለ4.5 ሚሊዮን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰው ለሁለተኛው ዙር የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትም ተገቢው የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ ወደ ስራ መገባቱንም አብራርተውላቸዋል።

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እያደረገ አለመሆኑን ጠቅሰዋል። አያይዘውም ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎች ተለይተው ከመከላከያ ጋር በመተባበር የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ ከአካባቢዎቹ የተፈናቀሉ ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው ስለመሆኑ ገልጸዋል።የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ ከማደረግ አንጻር የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቀደም ሲል በማይካድራ እንዲሁም በአክሱም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ምርመራ በማድረግ ያቀረበውን ሪፖርት አስታውሰው፣ በመንግስት በኩል በገለልተኛ አካላት አማካይነት ምርመራ እንዲደረግ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮምሽን ከተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ተቋም ጋር የጋራ ምርመራ ለማካሄድ ከስምምነት ላይ ተደርሶ በሂደት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል። መንግስት በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳተፉ አካላትን ለህግ ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነት የገለጽት ሚኒስትሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተሳተፉ አካላት በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና በጠቅላይ አቃበ ህግ በኩል አስፈላጊው ምርመራ በማድረግ በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸውላቸዋል።

ሚስተር ፔካ ሀቪስቶ በበኩላቸው ከሁለት ወራት በፊት ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ተደራሽነትና የሚዲያ አካላት በክልሉ በመገኘት እንዲዘግቡ ከማድረግ አንጻር በመንግስት የተከናወኑ ተግባራት በአዎንታዊነት ይጠቀሳል ብለዋል። በክልሉ ያደረጉት ጉብኝትም ይህንን የሚያረጋግጥ መሆኑን አንስተዋል። በተወሰኑ አካባቢዎች እርዳታ የሚያስፈለጋቸው ዜጎች ተገቢው እርዳታ እንዲደርሳቸው ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የአውሮፓ ህብረት የሰብዓዊ እርዳታ ኤጀንሲዎች በክልሉ ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለተደራሽ አካላት ተገቢው ድጋፍ ማቅረብ እንዲቻል የፍላጎት አጠቃላይ ዳሰሳ ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል። የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ አንዲሚወጣ ክቡር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መግለጻቸው በአዎንታዊነት እንደሚገነዘቡት ገልጸው፣ ሂደቱ እንዲፋጠን ጠይቀዋል። በወንጀል ከተሰማሩ የተለዩ ዋና የህወሓት ቅሬቶች ውጭ ሌሎች አካላት በፈቃደኝነት ለመንግስት እጅ እንዲሰጡ የምህረት ገደብ ማውጣቱ አስታውሰው፣ በዚሁ መሰረት እጃቸውን ለመንግስት ያልሰጡትን ወደ ህግ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

See also  ሲዳማ ወደ ግዳጅ ቀጠና ከተተ! አጫጭር ዜናዎች

በተያያዘም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ አካላት ምክክር በማድረግ ህዝቡ የመፍትሔው አካል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።ሚስተር ፔካ ሀቪስቶ ከተለያዩ የህበረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ አካላት ጋር ምክክር እንዲያደርጉ መታቀዱ በአዎንታዊነት እንደሚመለከቱት ገልጸዋል።የታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተም ኢትዮጵያ በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ድርድሩ በውጤት አንዲጠናቀቅረ ላደረጉት ጥረት ከበሬታ ያላት መሆኑን ክቡር አቶ ደመቀ ገልጸዋል። በቀጣይም በአፍሪካ ሕብረት አመቻችነት የሶስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸውላቸዋል። በተጨማሪም ድርድሩ በአውሮፓ ህብረት፣ በአሜሪካ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ታዛቢነት እንደሚካሄድ አብራርተውላቸዋል።

በኢትዮጵያ በኩል በውሃ ክፍፍል ስምምነት በሶስቱ አገራት መካከል ብቻ የሚካሄድ አለመሆኑን እንዲሁም ረጅም ጊዜ የሚወስድ መሆኑን ገልጸው፣ ድርድሩ በግድቡ የውሃ ሙሌት ላይ ማተኮር እንዳለበት ክቡር አቶ ደመቀ ገልጸዋል።

የህዳሴው ግድብ ድርድር ከመጪው ክረምት ከሚከናወነው የውሃ ሙሌት በፊት ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፣ በአውሮፓ ህብረት በኩልም የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ፍላጎት ገልጸዋል። የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብን ሁለቱ አገራት በድርድር መፍታት ያለባቸው መሆኑን ሚስተር ሀቬስቶ አንስተዋል።የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሱዳን የኢትዮጵያን ልዑላዊ መሬት በወረራ መያዟን ተከትሎ ማውገዝ የሚጠበቅበት ቢሆንም ይህንን አለማድረጉ አሳዛኝ መሆኑን ገልጸው፣ በኢትዮጵያ በኩል ችግሩ በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኝ ገልጸዋል።

ኢፕድ

Leave a Reply