የተከዜ የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች ምንም ዓይነት ጥገና ሳይፈልጉ ወደሥራ መግባታቸው ተገለጸ

የተከዜ ኃይል ማመንጫ ሁለቱ ዩኒቶች ምንም ዓይነት ጥገና ሳይፈልጉ ወደ ሥራ መግባታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን አስታወቁ። ከዚህ በፊትም ግድቡ ተመቷል ፣ ከዚህ በኋላ አገልግሎት አይሰጥም ሲባል የነበረው ሐሰት መሆኑንም አመለከቱ።

አቶ ሞገስ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንዳስ ታወቁት፣ የተከዜ ኃይል ማመንጫ ከዚህ ቀደም ኃይል ማመንጨት ቢችል ማስተላለፍ የሚያስችል መስመር ስላልተዘረጋለት ኃይልን ማመንጨት አቁሞና ለወራትም ያለ ሥራ ተቀምጦ ነበር ፤ አሁን ላይ ግን ካሉት አራት ዩኒቶች ሁለቱ በሙሉ አቅማቸው አገልግሎትን እየሰጡ ነው።ሁለት ዩኒቶች በሳምንቱ መጀመሪያ ተንቀሳቅሰዋል፤ በእነሱም እስከ 108 ሜጋዋት የሚደርስ ኃይል ይዞ ሠርቷል። ሁለቱ ዩኒቶችም ወደ ሥራ ያልገቡት የኃይል ፍላጎቱን ታሳቢ በማድረግ እንጂ ሌላ ችግር ኖሮባቸው አይደለም።

ዩኒቶቹ ስለሚሠሩ ብቻ ወደ ተግባር አይገቡም። ከትላንት በስቲያ ሁለቱን ዩኒቶች ሥራ ስናስጀምር የተጠቀምነው 7 ሰዓት ከ 18 ደቂቃ ሲሆን፤ እስከ 12 ሰዓትም አንዱ ዩኒት ብቻ እንዲሠራ የሆነው፤ ከ 12 ሰዓት ጀምሮ ደግሞ ሁለተኛው ዩኒት እንዲሠራ ሆኗል፤ በመሆኑም የኃይል ፍላጎቱ እየታየ ሁሉም ወደሥራ የሚገቡበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል።የኃይል ማመንጫዎቻችን ልክ እንደ ማሰራጫ መስመር አካባቢን ሳይሆን ሁሉንም የአገሪቱን ክፍል ነው የሚያገለግሉት፤ አሁን ለጊዜው የተከዜ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያልፍበት መስመር ጉዳት ደርሶበት ስለነበርና መጠገን ያለባቸውም መስመሮች ተጠግነው እስከሚጠናቀቁ ትግራይ ላይ ብቻ አገልግሎቱን እየሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል።

የተከዜ የኃይል ማመንጫ ምንም ዓይነት የተለየ ሥራ አልተሠራበትም ከዚህ በፊትም ግድቡ ተመቷል፣ ከዚህ በኋላ አገልግሎት አይሰጥም ሲባል የነበረው ሐሰት መሆኑን መለከቱት አቶ ሞገስ ፤ እንደውም በወቅቱ የክረምቱ ዝናብ ጥሩ ስለነበር ኃይል ማመንጫው በውሃ ተሞልቶ ነበረ ፤በዚያ ላይ ደግሞ ካሉት አራት ዩኒቶች መካከል አንዱ የጥገና ሥራ ላይ ስለነበር ሙሉ ኃይሉን እንኳን ቢጠቀም አቅሙ የሚቀንስበት ደረጃ ላይ አልነበረም ብለዋል።

እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ፣ ኃይል ማመንጫው ላይ ምንም የተከሰተ ጉዳት ባለመኖሩ ከወራት ቆይታ በኋላ ወደ ስር ሲገባ ያስወጣው ወጪም የለም፤ ከዚያ ይልቅ ትግራይ ክልል ላይ የህግ ማስከበር ሥራው በሚከናወንበት ወቅት በደረሰ ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ውድመት ተቋሙ 240 ሚሊየን ብር ኪሳራ አጋጥሞታል።

See also  ጦርነቱ አይቀሬ ሊሆን? በአፋር መከላከያ ምላሽ ሰጠ

ትግራይ ላይ አሁን ለሦስተኛ ጊዜ ሰሞኑን የኃይል መቋረጥ ተከስቷል ያሉት አቶ ሞገስ የዚህን የኃይል መቋረጥ ትክክልኛ ምክንያት ለማወቅ ባለሙያዎች እየሠሩ እንደሆነ አስታውቀዋል።ከተከዜ ወደመቀሌ የሚሄደውን መስመር በመጠገን ኃይል እንዲያመነጭ ማድረግ ተችሏል ፤ ይህ መስመር ባይጠገን ኖሮ የኃይል ማመንጫው መሥራት የሚችል ቢሆንም እንኳን ወደመስመር ማስገባት ወይም ኤሌክትሪክ እንዲያመነጭ ማድረግ አይቻልም ነበር።አሁን ባለው ሁኔታ የኃይል ማመንጫው ራሱን በራሱ እንዲቆጣጠር ሆኖ ለመቀሌና አካባቢው ከተሞች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህንን ለማድረግም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለሙያዎች ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ከፍለዋል ያሉት አቶ ሞገስ፣አንዳንድ ቦታዎች ላይ አሁንም ጭምር የሰላም ስጋት ከመኖሩም በላይ በአነስተኛ ቡድን እየተደራጁ ጥቃት ለመሰንዘር የሚሞክሩ አካላት አሉ፣ ባለሞያዎቻቸው ከእነሱም ጋር ጭምር እየተጋፈጡ ሥራቸውን መሥራታቸውን ጠቁመዋል።የትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ መቋረጥን መንግሥት ሆን ብሎ እንዳደረገው አድርጎ የሚናፈሰው ነገር ፍጹም ሐሰት ነው ያሉት አቶ ሞገስ ፣ እንደዚህ ዓይነት ሃሳብ ቢኖር ኖሮ ልክ አንደኛው መስመር እንደተቋረጠ አማራጭ በሚባል ሌላ መስመር ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኝ አይሠራም ነበር ብለዋል።ክልሉ ቀደም ሲል ኃይልን ያገኝ የነበረው አላማጣ።

መሆኒ መቀሌ በሚሄድ መስመር ነበር፤ እሱን መጠገን እስከሚቻል ድረስ የኃይል መቋረጡ ይቆይ ነበር፤ ነገር ግን በሌላ መስመር ቀይሮ ለመሥራት የተደረገው ጥረት ተከዜም ወደ ሥራ እንዲገባ አደርጎታል። ህብረተሰቡም ይህንን በአግባቡ ሊረዳ እንደሚገባም አመልክተዋል።በመሰረተ ልማት ላይ የሚደርስ ጉዳት ማንንም ተጠቃሚ አያደርገም፣ እንደ አገር ሁሉንም የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ በአካባቢው ላለ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖን የሚያሳድር ነው፤ በመሆኑም ህብረተሰቡ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ የሚደርስን ጉዳት ለሚመለከተው የጸጥታ አካል በማሳወቅ አጥፊዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋ።

እፀገነት አክሊሉ

Leave a Reply