‹‹ሀብት ለማፍራት ብቻ ሳይሆን ያለውንም ለመጠበቅና ህይወትን ለመታደግ የሰላም መኖር ወሳኝ ነው›› አቶ ደስታ ሌዳሞ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር


የጸጥታ መደፍረስ ክስረት በመሆኑ ሀብት ለማምጣት ብቻ ሳይሆን ያለውንም ለማስጠበቅና ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ ህይወት ለመታደግ የሰላም መኖር ወሳኝ መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ። በክልሉ 12 ተፎካካሪ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን ማስመዝገባቸውን ጠቁመዋል።

አቶ ደስታ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፤ የጸጥታ እጦት የሀብት ክስረትን ከማስከተሉም በላይ ሕይወት ቀጣፊ ነው። ስለዚህ ተጨማሪ ሀብት ለማምጣት ብቻ ሳይሆን ያለውንም ለማስጠበቅና ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ ህይወት ለመታደግ የሰላም መኖር ወሳኝ ነው።

ሰላም የማይኖር ከሆነ ብዙ ዓመታት ለፍተን የገነባናቸውን አንጡራ ሀብቶቻችንን ወድመው እንደገና የኋሊት ያስጉዘናል ያሉት አቶ ደስታ፣ በእስካሁንም ሂደት የሰው ሕይወትን የቀጠፈና ሀብትን ያወደመ ነገር ቢኖር ዴሞክራሲ እጦት ያመጣው ሳንካ ነው ብለዋል።

“ለኢትዮጵያውያን የሚጎድለን ነገር ቢኖር ዴሞክራሲ ነው። ዴሞክራሲ ነገሮች በቀላል መንገድ እንዲሳኩ የሚያደርግ ነው። ነገር ግን የዴሞክራሲ ባህል ስላልሰረጸ የሚፈለገውን ነገር ለማግኘት ብዙ ዋጋ እያስከፈለ ነው። በዴሞክራሲ እጦት ምክንያት የሰው ሕይወት ተቀጥፏል፤ ሀብት ንብረት ወድሟል “ብለዋል ።

መንገድ መዝጋት፣ ድልድይና ንብረት ማውደም ያስፈለገው አንድን ነገር ለመቀየር ወይም መንግሥትን ከሥልጣኑ ለማስነሳት ሲባል ነው ያሉት ርዕሰመስተዳድሩ፣ መንግሥትን ለመቀየር ግን አሁን እየሄድን ባለው አካሄድ ሳይሆን ትንሽ ደቂቃ ተሰልፈን በካርዳችን መሆን አለበት ብለዋል።

በካርድ ከሆነ ውድመት፣ ጥፋትና መገዳደል ሳይኖር ባለው አማራጭ ፍላጎታችንን ማሳካት እንችላለን ያሉት ርዕሰመስተዳድሩ፣ በዚህም ዴሞክራሲን መለማመድ፤ ባህሉን ማሳደግ ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።

የዴሞክራሲ መገለጫ ከሆኑት መካከል አንዱ ምርጫ ነውና ሰላማዊ፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ ይኖርብናል ያሉት ርዕሰመስተዳድሩ፣ በምርጫው ውጤትም አብዛኛው ሰው የተስማማበትን ማክበር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ብጥብጥና ሁከት አሁን ላለንበት ድህነት ውስጥ አስገብቶናል ያሉት አቶ ደስታ፣ ይህ መንገድ ስለማያዋጣ ዝግ አድርገን ማንም አማራጭ አለኝ የሚል ኃይል አማራጩን በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀርብ የኢትዮጵያ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል ። አማራጮች ሁሉ መደመጥ እንዳለባቸውን አመልክተዋል።

ህዝቡ የፈለገውን ለመወሰን ያስችለው ዘንድ በነቂስ ወጥቶ መመዝገብ እንዳለበት አመልክተው፤ የመራጭነትን መብት ሊያጎናጽፈው የሚችለውን ካርድ በእጁ መያዝ አለበት ብለዋል። ለአመጽ የሚውሉ ግብዓቶችን፣ ቅስቀሳዎችን ብሎም የሚያሳስቱ የጥላቻ ንግግሮችን ማውገዝና መከልከል ይኖርብናልም ብለዋል ።

በአሁኑ ጊዜ በሲዳማ ክልል እየተካሄደ ያለው የምርጫ ዝግጅት እንቅስቃሴ ሰላማዊ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ደስታ፣ በክልሉም 12 ተፎካካሪ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን አቅርበው አስመዝግበዋል ብለዋል። ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ሳንካ እንዳይገጥመው እየተሰራ እንደሆነም አስታውቀዋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫ ሄደት ውስጥ ችግር ከገጠማቸው ወዲያው መፍትሄ ማግኘት እንዲችሉ የጋራ ምክር ቤት መስርተናል ። የጋራ ምክር ቤቱ የገዢው ፓርቲ ሐሳብ በበላይነት የሚንጸባረቅበት ሳይሆን ሁሉም ድምጹ እኩል የሚያሰማበትና ችግሩ በእኩል ተፈትሾ በእኩል ደረጃ ፍትህ የሚያገኝበት መሆኑንም አመልክተዋል።

አቶ ደስታ እንዳሉት፤ እንደ ሲዳማ ክልል ምርጫ ጣቢያዎቹ ከሁለት ሺህ በላይ ናቸው። ለእነዚህ ሁሉ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ተሰናድተዋል። የጸጥታ ጉዳዩን አስተማማኝ የማድረግ ሥራ በተለየ ትኩረትና ከህዝቡ ጋር በመወያየት ጭምር እየተሰራ ነው። ይህም በመሆኑ እስካሁን በምርጫ ጉዳይ በክልሉ ያጋጠመ ችግር የለም ። ሂደቱም መልካም የሚባል እንደሆነም አስታውቀዋል።

እስከመጨረሻው ይህንን በማስጠበቅ ምርጫው ሰላማዊ፣ ነጻና ገለልተኛ ብሎም ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ተግተን እየሰራን ነው። የመንግሥት ሥልጣን ከምርጫ ኮሮጆ የሚወጣ እንዲሆን፣ ዴሞክራሲው ጥልቀቱ እንዲጨምር ፣ ባህልም እንዲሆን በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል።
በአስቴር ኤልያስ

(ኢ ፕ ድ)

Leave a Reply