– ዳቦ በሰዓቱ ባለመድረሱ በሥራቸው ላይ ጫና እንደፈጠረባቸው በሸገር ዳቦ አከፋፋይነት የተደራጁ ወጣቶች አመለከቱ
– ያሉት ተሽከርካሪዎች ውስን በመሆናቸው ዳቦውን በሰዓቱ ማድረስ እንዳልቻለ ሸገር ዳቦ አስታውቋል


ዳቦ በሰዓቱ ባለመድረሱ በሥራቸው ላይ ጫና እያደረሰባቸው እንደሆነ በሸገር ዳቦ አከፋፋይነት የተደራጁ ወጣቶች አመለከቱ ። ያሉት ተሽከርካሪዎች ውስን በመሆናቸው ለ384 ሱቆች በሰዓቱ ማድረስ እንዳልቻለ የሸገር ዳቦ ፋብሪካ አስታወቀ።

በከተማ አስተዳደሩ የሥራ እድል ፈጠራ አማካኝነት የሸገር ዳቦ ሽያጭ ላይ አምሥት ሆነው ተደራጅተው እየሰሩ ከሚገኙት መካከል አቶ ሰይፉ አቦምሳ ለአዲስ ዘመን እንደገለጸው፣ ዳቦ ብዙ ጊዜ በሰዓቱ መድረስ ባለመቻሉ በስራቸው ላይ እንቅፋት ፈጥሮባቸዋል።

ዳቦ በጠዋት የሚፈልገው ኅብረተሰብ በርካታ በመሆኑ በሌሊት ዳቦውን ለማግኘት ተሰልፎ ሲጠብቅ በሰዓቱ ስለማይደርስ ከፍተኛ ቅሬታ እያቀረበ መሆኑን አመልክቶ ፣ችግሩ በገበያው እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረባቸው መሆኑን አስታውቋል።

ሌላዋ በሸገር ዳቦ አከፋፋይነት ንግድ የተሰማራችው ወይዘሮ አለምበዛ ጌታቸው በበኩሏ ፣ የሸገር ዳቦን ተደራጅተው እንዲያከፋፍሉ ዕድል መፍጠሩ መልካም ቢሆንም ዳቦው በሚፈለግበት ሰዓት አለመድረሱ በአግባቡ ለመስራት ተቸግረዋል።

ዳቦው አንዳንዴ በጠዋት፣ ሌላ ጊዜ ከሰዓት የሚቀርብበት ሁኔታ መኖሩን ያመለከተችው ወይዘሮ አለምበዛ ፣ ኅብረተሰቡ ዳቦውን በጠዋት ስለሚፈልገው በተገቢው መንገድ ልናስተናግደው አልቻልንም ብላለች።
ዳቦው በጠዋት ቢደርስላቸው ከሦስት ሺ 500 በላይ ዳቦ መሸጥ እንደሚችሉ ጠቁማ፣ ይህ ባለመሆኑ በሚፈልጉት ልክ መስራት እንዳይችሉ አመልክታለች።

ማህበረሰቡ ዳቦ ለመግዛት በሌሊት ተሰልፎ ብርድ ሲጠጣ አርፍዶ ዳቦ አጥቶ ሲመለስ ማየት ከባድ ነው የሚሉት ወይዘሮ አለምበዛ፤ ‹‹ዳቦ በሰዓቱ ቢቀርብ ማኅበረሰቡ በወቅቱ ማግኘት ከመቻሉም ባሻገር እነሱም በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።

በአስኮ የብርጭቆ ፋብሪካ ሰፈር ነዋሪዋ ወይዘሮ ስንቅነሽ አሻግሬ፣ ሸገር ዳቦ መሸጥ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ተጠቃሚ እንደሆኑ ገልጸው፣ ዳቦው አልፎ አልፎ በጠዋት ስለማይደርስ ወረፋ የያዘ ሰው ምንም ሳይገዛ የሚመለስበት ሁኔታ እንዳለ አስታውቀዋል።

ዳቦው ተጠቃሚው በሚፈልግበት ሰዓት መድረስ ቢችል አንድ ዳቦ በአንድ ብር ከአስር ሳንቲም ስለሚሸጥ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላለው የኅብረተሰብ ክፍል ጠቀሜታው ከፍ ያለ እንደሚሆን አመልክተዋል ።

በችግሩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቶ አካለወልድ አድማሱ፣ የመሸጫ ሱቆች የሚገኙበት ቦታ ምቹ አለመሆንና ያሉት ተሽከርካሪዎች ውስን መሆናቸው ለሁሉም ሱቆች ዳቦ በሰዓቱ ማድረስ እንዳልተቻለ ገልጸዋል ።

ፋብሪካው ዳቦ ከማምረት ባለፈ ለ384 የዳቦ ቸርቻሪ ሱቆች ባሉት 20 ተሽከርካሪዎች ዳቦውን ለማዳረስ እየሰራ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ ባሉት ተሽከርካሪዎች በሰዓቱ ማድረስ የሚችልበት አቅም እንደሌለው አስታውቀዋል።

ቸርቻሪዎች ምርቱ በሰዓቱ አይደርሰንም ቢሉ የሚገርም አይደለም ። በአንድ ክፍለ ከተማ ከ20 እስከ 30 ሱቆች የሚገኙ ሲሆን ሱቆቹ የተቀመጡበት ሁኔታ መንደር ውስጥ በመሆኑ ባሉት ውስን ተሽከርካሪዎች በፍጥነት ለማዳረስ ፈታኝ ነው ፤ መኪኖቹ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ አምሥት የኦሮሚያ ከተሞች ጭምር ስለሚያከፋፍሉ ከፍተኛ የሆነ የተሽከርካሪ እጥረት አለ ብለዋል።

እንደ አቶ አካለወልድ ገለፃ፣ የአቅርቦት ችግሩን ለመቅረፍ ተጨማሪ ተሽከርካሪዎችን ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት ጥያቄ ቀርቦ በሂደት ላይ ነው፤ ሁኔታዎች በፍጥነት ካለቁ በሰዓቱ የሚደርስበት ሁኔታ እንደሚኖር ጠቁመዋል።
በሞገስ ተስፋ. – (ኢ ፕ ድ)

Leave a Reply