ኢራን እስራኤል ላይ ዛተች፤ የከፋ ጥቃት ደርሶባታል

ኢራን በናታንዝ የኒኩልየር ማብላያ ጣቢያ ላይ ለደረሰው ጥቃት እስራኤልን ተጠያቂ አደረገች። በመዲናይቱ ቴህራን ደቡባዊ ክፍል ተገንብቶ ስራ ከመጀመሩ ትናንት እሁድ ጥቃት የደረሰበት የማብላያ ጣብያው ብርቱ ጉዳት ሳይደርስበት አልቀረም ተብሏል። ነገር ግን ለጥቃቱ እስራኤል ሃላፊነቱን አልወሰደችም ።

የእስራኤል የመገናኛ ብዙኃን የደህንነት ምንጮችን በመጥቀስ የሀገሪቱ የስለላ ተቋም ሞሳድ በኒኩልየር ማብላያ ጣቢያው ላይ የበይነ መረብ የመረጃ ጥቃት ማድረሱን በስፋት ሲዘግቡ ውለዋል።

ጥቃቱን ተከትሎም ኢራን ከኃያላን ሀገራት ጋር በቀጣይ በኒኩልየር መርኃ ግብር ላይ ሊደረጉ በታቀዱ ውይይቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ እንደማይቀር የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቃባይ ዛኤድ ካቲብዛዴህ ገልጸዋል። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔትያናሁ ትናንት እሁድ የዩናይትድስቴትሱን የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስቲን ጋር ተገናኝተው በተነጋገሩበት ወቅት እንዳሉት የኢራን የኒኩልየር መርሃ ግብር ስምምነትን ለማደስ የሚደረገውን ጥረት በቻሉት አቅም ሁሉ ተጠቅመው ለማስቆም እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በተያያዘ እንደተባለው ለትናንቱ የናታንዝ ጥቃት እስራኤል ኃላፊነቱን የምትወስድ ከሆነ ከጫፍ የነበረው የሁለቱ ሃገራት መፈላለግ መካከለኛው ምስራቅን ወደ ለየለት ግጭት እንዳያስገባ ያሰጋል ሲል አሶሽየትድ ፕረስ ዘግቧል።

˝እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ጣቢያ ላይ ጥቃት መፈፀሟን ተከትሎ˝ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ኢራን አስታወቀች። የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በወሳኝ የኒውክሌር ጣቢያ ላይ በቅርቡ ለተፈፀመው ጥቃት እስራኤልን ተጠያቂ አድርጓል።

የኢራን ባለስልጣናት የኒውክሌር ሽብርተኝነት ብለው የገለፁት ጥቃት በናታንዝ ዩራኒየም ማበልፀጊያ ላይ የሀይል መቋረጥ ማስከተሉ ተነግሯል። በዚህ የኒውክሌር ጣቢያ ላይ ኢራን ዘመናዊ የዩራኒየም ማበልፀጊያ ስራ ማስጀመሯን ነው ቢቢሲ የዘገበው። እስራኤል በጉዳይ ዙሪያ አስተያየት ባትሰጥም በእስራኤል የሚገኝ የሬዲዮ ጣቢያ በሞሳድ የተፈፀመ የመረጃ መረብ ጥቃት መሆኑን የደህንነት መረጃ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ  ዘግቧል።

ጄሩሳሌም ፖስት ባወጣው ዘገባም  ጥቃቱ የኒውክሌር ማበልፀጊያው ውስጣዊ የሀይል ስርዓት ለማውደም  ማስቻሉን  ኒውዮርክ ታይምስ ጠቅሶ ዘግቧል። በዘገባው ጥቃቱ በናታንዝ ዩራኒየም ማበልፀጊያ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከቱ የተገለፀ ሲሆን የኒውክሌር ጣቢያው በድጋሜ ወደ ስራ ለመመለስ በትንሹ ዘጠኝ ወራት ያስፈልገዋል ተብሏል።

dw


Leave a Reply

%d bloggers like this: