አሁንም አብሯቸው መቃብራቸው ድረስ የተከተላቸው ነገር ቢኖር ውሸታቸው ነው። እየሞቱ ገደልን ፣ እየተደመሰሱ ደመሰስን ፣ እየተቀበሩ ቀበርን ፣ እየጠፉ አጠፋን የሚለው አሳሳች ፕሮፖጋንዳቸውን በተከፋዮቻቸው ቢያሰራጩም ወጣቱን የስርዓት ጠባቂ ሊያደርጉት ቢሞክሩም ከመደምሰስ አላተረፋቸውም።

የእጅህን ይስጥህ

ለሀገር ፍርሰትና ለንፁሀን መገደል በጀት መድቦ አጥፊዎችን አሰልጥኖ አመራርነት እየሰጠ እያስታጠቀና እያቀነባበረ በእቅድ ይሰራ የነበረው ህወሀት በሰራዊቱ የክፋት እጁን ማንሳቱን ተከትሎ ሰራዊቱ በወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ አሁን ላይ ጁንታውና የጁንታው ታጣቂዎች ከገቡበት እየተለቀሙ እየተደመሰሱ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ።

ጁንታው የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ወደ ሀገራችን ሰሜኑ ክፍል ከተንቀሳቀሱ የሰራዊቱ ክፍሎች መካከል ምዕራብ ዕዝ ይገኝበታል።

በዕዙ ካሉት ክ/ጦሮች ሁለቱን ይዞ በሰሜን ምዕራብ ግንባር ዳንሻ በ5ኛ ሜ/ድ ክ/ጦር ላይ ውጊያ የከፈተውን የጁንታውን ታጣቂዎች በመደምሰስ የነበረውን የመከላከል ቁመና ወደ ማጥቃት አሸጋግሮ ግዳጁን አሀዱ አለ።


RECENT POST


ከዳንሻ ዲቪዥን ድል በኋላ ባዕከር ሁመራ እያለ ወደ ፊት የቀጠለው የዕዙ ግዳጅ እጅግ በሚገርም ፍጥነት ጁንታው ቀደም ሲል የሚያሳዝን ግፍ የሰራባቸውን ተቆጣጠርኳቸው እያለ ከበሮ የደለቀባቸውን ቦታዎች እያስለቀቀ ሲገሰግስ ፣ በጀግንነቱ ሀገራዊ ሀላፊነቱን ሲያረጋግጥ በየቦታው ለሲቪሎች የሚሰጠው ከለላ ደግሞ ደግነቱን ይናገር ነበር።

የጁንታው ታጣቂዎች በተፎከረላቸው ልክ አልነበሩም። በአጭር ጊዜ የተኩስ ልውውጥ እግሬ አውጭኝ ማለት መበተን መለያቸው ነበር። ይህን በአደረግናቸው የውጊያ ዓውዶች ተመልክተናል። ይህ የሚያሳየው የጁንታው ታጣቂዎች አንድም ተገደው አንድም በሀሰት ፕሮፖጋንዳቸው ተታለው እንደገቡ ነው።

የዘረፋቸውን መድፎች ሳይጠቀምባቸው አንድም እያወደማቸውና እየጣላቸው ፈረጠጠ። የሰሜን ምዕራብ ግንባር አንበሳው ምዕራብ ዕዝም ከጁንታው ያስጣላቸውን መድፎች እየተጠቀመ ወደ ፊት የሚያደርገውን ግስጋሴ ቀጠለ።

ጁንታው የተማመነባቸው በርካታ ምሽጎች ከምንም ሳይጠብቁት በአጭር ጊዜ እየተሰበሩ ስለ ሀገሩ የማይደራደረውን ጀግናው ሰራዊት ፍጥነቱን ማስቆም ሳይችሉ ቀሩ።

የምዕራብ ዕዝ ሁለት ክ/ጦሮች እየተቀያየሩ ከ7ኛና 8ኛ ሜ/ድ ክ/ጦሮች ጋር በፈጠሩት ጥምረት የጁንታው ታጣቂዎች ብትንትናቸው ወጣ። ያ ሁሉ ጉራ ፣ ያ ሁሉ ፉከራ የት ገባ?

የምዕራብ ዕዝ አንበሶች ከዳንሻ የጀመሩት የጀግንነት እርምጃ መቀሌ አደረሳቸው። መቀሌም ለጀግኖቹ በሯን አልዘጋችም። ይልቁንም ወንጀለኞችን ጠራርጋ አስወጣች እንጂ።

የዘመቻው ኮከቦች ግን በዚህ አላበቁም። ጁንታው ወደ ፈረጠጠበት ተንቤን ሀገረ ሰላምና አብይ አዲ እቅጣጫ ማሳደዱን ቀጠሉ። እዛም እነሱን የሚደብቅ ምሽግ ፣ የሚከልል ተራራ ክፋታቸውን የሚሸከም ዋሻ አላገኙም ፡፡ የሰራዊቱን የጀግንነት እርምጃ የሚያስቆምም ፈተና አልነበረም።

የጁንታውን የጓዳ ጉድ እየጎለጎሉ ፣ የደበቋቸውን ከባድ ወታደራዊ ትጥቆች ፣ ብዛት ያለው የመሳሪያና የተተኳሽ ዴፖዎች ፣ የተደበቁ ብዛት ያላቸው መኪኖችን እና ሌሎች የሀገርና ወታደራዊ ንብረቶችን እያስጣለ ቀጠለ።

ጠላት የደበቀውን የሀገርና ወታደራዊ ንብረት የተመለከተ ሁሉ በርግጥም ጁንታው ሀገርን ከማፍረስም በላይ የማጥፋት እቅድ እንደነበረው መገመት አያዳግተውም። ይህ ሁሉ ግን ጁንታውን አሸናፊ አላደረገውም። ከሽንፈትም አላዳነውም።ምክንያቱም የሚዋጋው ወታደራዊ እውቀትና ልብ ነውና።

ጁንታው የሚችለው ምሽግ መቆፈር መዝረፍና የውሸት ፕሮፖጋንዳ ብቻ ነው። እናም ጁንታውን የሽንፈት ጎርፍ ጠራርጎ ከውጊያው ሜዳ አውጥቶ ከተፈጥሮ ጋር አጋጨው።

የተደበቁበት በረሀ ተፈጥሮው ገደል ተራራ ሞቃታማ ነው። በዛ የቅምጥል ህይወት የለም። ውስኪ ቤት መቀያየር ሳይሆን ዋሻ መቀያየር ፣ በቪ8 መንፈላሰስ ሳይሆን በእግር መኳተን ፣ ተስፋ መቁረጥ መንደላቀቅ ሳይሆን መሽሎክሎክ ፣ መዝለል መሮጥ ሳይሆን በቃሬዛ መጎተት። የእጅህን ይስጥህ ማለት ይሄ አይደል።

የእጅህን ይስጥህ ምርቃትም እርግማንም ነው። ለጁንታው ግን ምርቃት ነው ብዬ በአራዳኛ ቋንቋ ሙድ አልይዝባችሁም። ሁላችንም የክፋታቸውን ልክ ፣ የተንኮላቸውን ጣሪያ ፣ የድርጊታቸውን አደገኛነት ፣ በሀገርና በህዝብ ያደረሱትን ጉዳት እናውቀዋለን።

ተከዜ በረሀ ለህወሀት ጁንታ ተሸከርካሪ ወንበር ላይ ሆነው የሚያዙት ፣ ሁን ያሉትን የሚሆን አይደለም። በተቃራኒው በበረሀው ተፈጥሯዊ ህግ አሜን ብሎ መገዛት ብቻ። ነጋ ጠባ ከተራራና ዋሻ ጋር መፋጠጥ። መጥፎ ስራ እንዲህ ነው። መጠጊያ መሸሸጊያ ያሳጣል።

አሁንም አብሯቸው መቃብራቸው ድረስ የተከተላቸው ነገር ቢኖር ውሸታቸው ነው። እየሞቱ ገደልን ፣ እየተደመሰሱ ደመሰስን ፣ እየተቀበሩ ቀበርን ፣ እየጠፉ አጠፋን የሚለው አሳሳች ፕሮፖጋንዳቸውን በተከፋዮቻቸው ቢያሰራጩም ወጣቱን የስርዓት ጠባቂ ሊያደርጉት ቢሞክሩም ከመደምሰስ አላተረፋቸውም።

እውነቱ እነሱ ጋር ነው። እነሱ ሀገርን ሊያፈርሱ ፣ ወታደሩን ከጀርባው የመቱ ፣ በሀገሪቱ እልቂት እንዲሆን ግጭት በመቀስቀስ በርካታ ህፃናትን ያለአሳዳጊ ያስቀሩ ፣ በርካታ እናቶችን የደም እንባ ያስነቡ ፣ በርካታ ወጣቶችን ወግ ማዕረግ ሳያዩ የጥይት እራት ያደረጉ ፣ የገደሉና ያስገደሉ ወንጀለኞች ናቸው።

እነዚህ ወንጀለኞች መሞትን ፈፅሞ ይፈሩታል። ለእነሱ መኖር ሁሌም የሚሞትላቸው እንዲኖር አጥብቀው ግን ይፈልጋሉ። ወደ ዋሻ እግሬ አውጭኝ ማለታቸውም ለዚህ ነው።ሞትን እንደሚፈሯት አንዱ ማሳያ ነው ፡፡

ዓንድም ጁንታ የመጨረሻዋን ፅዋ በራሱ አልተጎነጨም። ከሀገረሰላም እስከ አብይ አዲ ፣ ከጉሮሮ እስከ ዛና ፣ ከእንዳባጉና እስከ አዲገብሩ ፣ ከተከዜ እስከ ፍየል ውሀ ፣ ከሳምሪ እስከ ራያ በረሀዎች ቢማስኑ ፣ ቁመተ መለሎ ተራራዎችን የሙጥኝ ቢሉ ፣ አንዱም ሊደብቃቸውና ሀይል ሆኖ እንደፈለጉት ሊያደርግላቸው አቅም ሆኖ ሊያሸንፍላቸው አልቻለም።

የምዕራብ ዕዝ ጀግኖች ከሌሎች አቻ ዕዞች ጋር እየተቀናጁ ከገቡበት ሁሉ እያሳደዱ እስከነ ታማኝ ጠባቂዎቻቸው በቆፈሩት ጉድጓድ ቀበሯቸው። ሞት ለጁንታው ሆነ።

ፍልሚያውን አሸንፎ ለመውጣት ከራዊቱ በላይ ጠንካራ መሆን ይጠበቅባቸዋል። አቅማቸው ልፍስፍስ ፣ ሌላው ያደረገውን አደረግሁ እያሉ መልካም ስራ የሚሰርቁ ፣ የማይችሉትን እችላለሁ የሚሉ ፣ የትግራይ ተወላጅ የሌለበት ጦርነት ውጤቱ ሽንፈት ነው እያሉ ለራሳቸው የሰጡት ግምት ለውድቀታቸው ምክንያት የሆናቸው ፣ ታሪካቸው በጫካ ጀምሮ በጫካ አለቀ።

የውርደቶች ሁሉ ትልቁ ውርደት ይህ ነው። ከጫካ ቀጥታ ታላቁ ቤተመንግስት የገቡት ህወሀቶች ጥልፍልፍ ወንጀላቸው ከቤተ መንግስት አሽቀንጥሮ ወደ መቀሌ ሲወረውራቸው መቀሌም ከትንሽ ጊዜ መታገስ በኋላ ክፋታቸውን የሚሸከም ተከሻ የለኝም ስትል ወደ መነሻቸው የመሰሪነት ክፋት ወደ ጠነሰሱበት ጫካ ጠራርጋ አስገባቻቸው።።

የሚጥል እንጂ የሚያጠነክር ክፋት የለምና እጣ ፈንታቸው የመጥፋት ፅዋ ሆነ። አሁን ላይ ጁንታውና የጁንታው ታማኝ ጠባቂዎች በራያ በረሀ ላይ ሊድኑ የማያስችላቸው ጠንካራ ምት ተመተዋል። በደረሰባቸው ሰብዓዊ ፣ ማቴሪያላዊና ሞራላዊ ኪሳራም ምንም ማድረግ ወደ ማይችሉበት አቋም ደርሰዋል።

አሁንም ተደብቀው ተራቸውን የሚጠብቁትም ቢሆኑ ማምሻም እድሜ ነው እንዲሉ ካልሆነ እጣ ፈንታቸው መጥፋት እንደሆነ እነሱም ተከፋይ ፕሮፖጋዲስቶቻቸውም አሁንም ህወሀት ይመጣል ብለው በራቸውን ከፍተው የሚጠብቁ ታማኝ አማኞቻቸውም ያውቁታል።

እውነቱ ህወሀት ሞቷል። ቀሪዎቹም ክፋታቸው የጣረሞት ስቃይ ውስጥ ከቷቸዋል።ይህን የራያ በረሀዎች ይናገሩታል። አዛውንቶቹ የእጃቸውን አግኝተዋል። ሁላችንም የእጃችን ይስጠን።

ታገል አልማው ( ከግዳጅ ቀጣና )
ፎቶግራፍ ሽመልስ እሸቱ – via መከላከያ ፊስ ቡክ

    Leave a Reply