ሱዳን በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የዝግ ስብሰባ ለማድረግ ጥሪ አቀረበች

ሱዳን በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የዝግ ስብሰባ ለማድረግ ለግብጽ እና ለኢትዮጵያ ጥሪ አቀረበች፡፡

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ተደራድረው ስምምነት መድረስ ያልቻሉት የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መሪዎች በሚቀጥሉት አስር ቀናት ተገናኝተው በዝግ እንዲወያዩ ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2015ቱ የመርሆዎች ስምምነት መሰረት ወደፊት ለመራመድ በሚያስችሉን አማራጮች ላይ ተወያይተን በመስማማት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነታችንንም ማደስ ይገባል ብለዋል፡፡

በመጋቢት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. የሶስቱ አገሮች መሪዎች ለትብብር እና ልዩነቶቻቸውን በሰላም ለመፍታት በፈረሙት ውል መሠረት ለመወያየት እና ለመስማማት ጽህፈት ቤታቸው ትናንት ማክሰኞ ዕኩለ ለሊት ባወጣው መግለጫ ማስታወቃቸውን ሱዳን ትሪብዩን ዘግቧል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከግብጽ እና ሱዳን መሪዎች የተፈራረሙት “የመርሆዎች ስምምነት” የተባለ ውል አስረኛ አንቀጽ፤ “ሶስቱ አገራት አለመግባባቶችን በምክክር ወይም በድርድር መፍታት ከተሳናቸው ዕርቅ ወይም ሽምግልና ሊጠይቁ ወይም ጉዳዩን ወደ መሪዎቻቸው ሊመሩ ይችላሉ” የሚለውን አንቀጽ በመጥቀስ ሱዳን የውይይት ጥሪውን አቅርባለች፡፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረጉት ተደጋጋሚ የሶስትዮሽ ድርድሮች ውጤታማ ሳይሆኑና ስምምነት ላይ ሳይደረስ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

(ዋልታ) –

Leave a Reply