በኢትዮጵያ እውነተኛ ሁሉንም ያማከለ ዴሞክራሲያሲዊ ስረዓተ መንግስት ካልተመሰረተ አሁን ያሉትንና ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ የአገሪቱን ችግሮች ለመፍታት ከባድ ሊሆን እንደሚችል በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር ያደረጉ ምሁራን ገለጹ። ‘ኢትዮጵያዊነት’ በተሰኘ የሲቪክ ማኅበር አዘጋጅነት ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያያዙትን የተሳሳተ አቋም በተመለከተ በአለም አቀፍ ደረጃ የዌቢናር ውይይት እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ሌሎችም አለም አቀፍ ምሁራን እየተሳተፉ ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ ባለፉት ከ30 በላይ አመታት ለታዩ ችግሮች ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ተነስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በቅርብ ጊዜ የተካሄደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያ የተሳሳተ የመረጃ ዘመቻ መከፈቱና መረጃውም በምዕራባውያን መስተጋባቱም ተነስቷል።

ይህም በተሰሳቱ የመረጃ ምንጮች የሚሰሩ ዘገባዎች እውነቱ እንዲሸፈንና ትክክለኛ መረጃ ለአለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዳይዳረስ አድርጓል ተብሏል። በአገሪቱ በየጊዜው ለሚከሰቱ ችግሮች መንስዔ ከሆኑት መካከል ውጫዊና ውስጣዊ ሁነቶች የተጠቀሱ ሲሆን በተለይም ባለፉት 60 ዓመታት የመንግስታት መለወዋወጥ ያስከተላቸው ጉዳዮች የውስጣዊ ችግሮች መንስዔ መሆናቸው ተነግሯል።

ከዚህ ባለፈ ከ3ሺ ዓመታት በላይ ያለ ቅኝ ግዛት የጸናው የኢትዮጵያ መንግስት በምእራባውያን ዘንድ የፈጠረው ከፍተኛ ቅሬታና ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች እንዳትረጋገ ብሎም ቅኝ ተገዢ ለማድረግ የሚደረጉ ሙከራዎች በውይይቱ ተነስተዋል። ይህም በየጊዜው ለሚታዩ የማንነትና ሌሎች ግጭቶች መከሰት አንዱ ምክንያት ነው ተብሏል።

እነዚህን የቆዩና ወቅታዊ ችግሮች ለመፍታት በልዩነት ውስጥ ባለ አንድነትና በአንድ ነት ውስጥ በሚጠበቅ ልዩነት የቆየውን ኢትዮጵያዊነት የሚያስቀጥል ተግባር በሁሉም መከናወን እንደሚገባ ተጠቁሟል። እውነተኛና ሁሉንም ያማከለ ዴሞክራሲያዊ ስረዓተ መንግስት ካልተመሰረተ አሁን ያሉትንና ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ የአገሪቱን ችግሮች ለመፍታት እንደማይቻልም በውይይቱ ተገልጿል።

በውይይቱ አለም አቀፍ ምሁራን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፎችን ያቀረቡ ሲሆን በተሳታፊዎች በሚነሱ ጥያቄዎችና ሃሳቦች ላይ በምሁራኑ ምላሽ እየተሰጠ ነው ሲል ኢዜአ ዘግቧል።


Leave a Reply