“ሌሎች ህወሃቶችና ኦነግ ሸኔ ጨረሱን” የአጣዬ ነዋሪዎች ” ጅብ የሚነክሰው አናክሶ ነው ” የአቶ ምግባሩ ትንቢት

በክፉዎች ሴራ ቤተሰቦቻቸው፣ የአማራ ክልል፣ ኢትዮጵያና ወዳጆቻቸው ያጡዋቸው አቶ ምግባሩ ከበደና ባልደረቦቻቸው የሚረሱ እንዳልሆኑ በሁሉም ዘንድ እምነት አለ። ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የአቶ ምግባሩ ከበደና የርዕሰ መስተዳደሩ አማካሪ የአቶ እዘዝ ዋሴ በጁን 25 ቀን 2019 የቀብር ስነስርዓታቸው የተከናወነው በክፉዎች ሴራ መሆኑንን መላው የአማራ ሕዝብ ጠንቅቆ ያውቃል።

ኢትዮ ቲዩብ በዚህ የሽኝት ቀን ይፋ ባደረገው የምስል መረጃ በዋሽንግቶን ለህዝብ ንግግር ሲያደርጉ ” ጅብ የሚነክሰው አናክሶ ነው” ሲሉ ይደመጣሉ። እጅግ ባማረው ለዛቸው አፈር በቀመሱበት ዕለት ለማስታወሻቸው ይሆን ዘንድ በተሰራጨው በዚሁ ቪዲዮ ” በተበታተንን ቁጥር እንነከሳለን” ሲሉ የነብይ ያህል የተናገሩት ዛሬ እውን ሆኗል። እኒያ እሳቸውንና ውድ ባልደረቦቻቸውን ያስበሉ ዛሬም አማራን እየበታተኑ እያስበሉት ነው። አያይዘው ” የችግሮቻችን ሁሉ ቁልፍ ያለው አንድነታችን ውስጥ ነው” ሲሉ ደጋግመው አስረዱ።

” የአማራ ህዝብ ለኢትዮጵያ ያልከፈለው መስዋዕትነት የለም፤ ቢወራ ተዘርዝሮ አያልቅም” ሲሉ ሌሎችን በሚስከፋና በትዕቢት ሳይሆን በበሳል ማብራሪያ ነበር። በዚህ ታሪካዊ ቪዲዮ ” ብቻቸንን ግን አልነበረም” ሲሉ ቀድመው የገለጹት ድል እንዴት ጣፋጭ እንደሆነ አመላከቱ። ” ከሌሎች ጀግኖች ወንድሞቻችን ጋር ሆነን ስለነበርን ድሉ የሚጣፍጥ ሆነ” አሉ። ሲያስሩት ” የሚያምርብን አንድነትና ህብረታችን ነው። አለበለዚያ እንበታተናለን። ከተበታተን እንነከሳለን” አሉ። ዛሬ የሆነው ይህ ነው። አቶ ምግባሩ አማራን ከመስለ ወንድሞቹ ጋር አብረው ለማሻገር ከምርጥ አጋሮቻቸው ጋር ደፋ ቀና ማለታቸው እንደ ክፋት ተቆጥሮ ተፈረደባቸው። ነብሰ በላዎቹና ሴረኞቹ ዛሬም አሉ። ምን ይጠበቃል?

የክልሉ የድህንነት ሃላፊ አቶ ሲሳይ መንግስቴ ይህንኑ ነው የደገሙት። የአማራን ሕዝብ ክተት ጠርተዋል። የፖለቲካ ቁማርተኞች አጋጣሚውን ለግል አላማቸው እንደ ግብዓት እየተተቀሙበት መሆኑንን ነው ያስታወቁት። ንግግራቸው መራር፣ ጥንካራ ሰሚ የሚሻው፣ ማስተዋል የተመላበት አተያይን የሚጠይቅም ጭምር ነው። ጥሪው እንደ ባሎን የሚነፍስ የባዶ ጩኸትና ጠላት የሚያበዛ ሳይሆን በስክነት የሚከናወን ነው።

ቢቢሲ ዛሬ ስለ ሰሜን ሸዋ በተለይም ስለአጣዬ ሲዘገብ ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ የሸዋ ሮቢት ነዋሪ “ትናንት ረፋድ ላይ ጀምሮ በርሃ አርባ አምባና ብርጭቆ ከሚባለው አገር “ሰው አለቀ፤ ተለበለበ” ሲሉ የደረሰውን ጉዳት ገልጸዋል። እርሳቸው አካባቢውን ለቀው እንደወጡ የገለጹት እኝህ ነዋሪ፤ ጥቃቱን የፈፀሙት “የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችና ሌሎች የህወሓት ኃይሎች” እነደሆኑ አመክቷል። ቢቢሲ ” ሌሎች የህወሃት ሃይሎች ” ያላቸውን ተናጋሪው እንዲያብራሩ አልጠየቀም። በደፈናው የህወሃት ሃይሎች ቢባልም ቀደም ሲል ህወሃት በሰሜን ሸዋ ያዘጋጀው ሃይል እንዳለና የህወሃት ሃይሎች በአፋር እያቆራረጡ ወደ አካባቢው ይዘልቁ እንደነበር ሲገለጽ እንደነበር ይታወሳል።

የአማራ ክልል በውስጡ እሳት የሚቆሰቁሱበት ተላላኪዎች ያሉበት። አስተምራኡአቸው ሁሉ ሌላውን በመነካካት የተካኑ ጠማሞች ያሉበት፣ ከሱዳን ድንበረተኛ መሆኑ፤ በየጫካውም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያ የመሸጉ የትህነግ ሃይሎች በንዴት እለት እለት የሚዝቱበት፣ በቅማንት ፈንጂ የተተመደለት፣ በቤኒሻንጉል ዓላማው ግልጽ የሆነ ጥቃት የሚሰነዘርበት፣ ሰፊ ቁጥር ያላቸው ወገኖቹ በየቦታው ተበትነው ያሉ መሆናቸው የተዘነጋ ይመስላል።

ይህ በሰሜን ሸዋ እሳት እያነደደ ህዝብ የሚፈጀው አራጅ ቡድን ጥያቄው ምን እንደሆነ በግልጽ አይነገርም። በምን መነሻ ንጹሃንን እንደሚያነድ አይገልጽም። እንዲህ ላለ ሽፍታ የአማራ ሕዝብ ተጋልጦ ባለበት፣ በቀን ውስጥ 300 የሚሆን ሕዝብ ሲሰዋ እንዴት የአማራ ሕዝብ እንወክላለን የሚሉ ድርጅቶች በምርጫ ስም ይካሰሳሉ? እንዲህ ያለ የክፋት ሰደድ እየነደደ እንዴት አማራን እንወክላለን የሚሉ ሁሉንም እርግፍ አድርገው “ህዝብ ቅድሚያ” አይሉም? አሳፋሪ ነው።

ክልሉ የክተት ያህል ህብረትን፣ አንድነትን፣ መተሳሰብን በገሃድ ጠይቋል። ይህ ካልሆነ ህዝባችንን መታደግ አንችልም ብሏል። ሰሜን ሸዋ ብቻ ሳይሆን በማዕከላዊ ጎንደርና ፍኖተ ሰላምም እየሆነ ያለውን ይፋ አድርጓል። ትህነግ ያስለጠናቸው እንደተነሱ አውጇል። ቢቢሲ ያናገራቸው ቪኦኤ ጃል መሮ የሚባለውን የሽፍቶች አለቃ አምጥቶ ማስተባበያ እስኪያሰማ ደረሰ “ኦነግ ሸኔና ሌሎች የህወሃት ሃይሎች” ሲሉ የሚያርዷቸው እነማን እንደሆኑ ሰለባዎች ተናግረዋል። አማራ አቶ ምግባሩ እንዳሉት አንድ የሚሆንበት ወቅት ይህና ይህ ብቻ ነው። በውጭም በውስጥም ያሉ ይህንን ሊያከብሩና ቅድሚያ ሊሰጡት ይገባል። አሳቡ አማራውን በጣጥሶ መንከስና ውስጡ ባሉ አስገዳዮች ማስነከስ ስለሆነ ላለመነከስ፣ ላለመነካክሰ አንድ ሆኖ መቆም ግድ ይሆናል።

ትሀንግ የሚባል ክፉ ድርጅት በማያወቀው ጉዳይ በዚህ ዘመን ያለን ትውልድ በስሙ ፈርጆ ላለፉት 28 ዓመታት ሲያሳርደው ኖረ። በዚያ መቆጨት ሲገባ ዛሬም ራሳቸውን በአዲስ መልክ የሸጡ እንግዴ ልጆች ይህን ምስኪን ህዝብ ዳግም የቁማራቸው ካርድ እያደረጉት ነው።

በየትኛውም አካል ይፈጸም፣ ማንም ይፈጽመው፣ ከየትም ስፖንሰር ይደረግ፣ ቅድሚያ አንድነት ከሌለ ራስን መከላከል አይታሰብም።በሚፈታተኑ ሁሉ ዘንዳ ደቃቃ ሆኖ ከመታየት አይዘልም፤ እውነት ላይ የተደገፈ ፍትህና ርትዕ ማስፈን አይቻልም፤ ይልቁኑም የጠላት እንኳን ቢቆም ወደ እርስ በርስ መነካከስ ይቀየራል። ስለዚህ ህዝብ አንድነቱን ከሚበሉት ሁሉ ራሱን ሊጠብቅ፣ ሊያጋልጣቸውና ሊያሰናብታቸው ይገባል። አማራ ላይ አተኩረን እንሰራለን የሚሉ አካላት በሚዲያም ሆነ ባላቸው አግባብ ሁሉ ይህንኑ አጠንክረው ሊሰሩ ይገባል። የዩቲዩብ ሳንቲም ለቀማ ሰውና አገር ሲኖሩ ይደርሳልና ለጊዜው ለገበያ ሳይሆን ለህልውና ቢሰራ!!


Leave a Reply