ከአምስት አመት በፊት በእንጀራ እናቷ ተገደለች የተባለችው ግለሰብ በህይወት ተገኘች

በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃና ወደራ ወረዳ ከአምስት ዓመት በፊት በእንጀራ እናቷ ተገደለች የተባለችው ግለሰብ በህይወት መገኘቷ ታወቀ።

ግለሰቧ መሞቷ በሀሰተኛ ምስክሮች ተረጋግጦ የእንጀራ እናቷ የ20 ዓመት እስር ቅጣት ተጥሎባቸው ነበር።

ሞታለች የተባለችው ግለሰብ እና ከሳሽ የነበሩት በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የዞኑ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኮማንደር ደበበ መኩሪያ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በተደራጀ የሃሰተኛ ምስክሮች የሚፈፀሙ ወንጀሎች የማህበረሰቡን መልካም እሴቶች የሚሸረሽሩ ናቸው።

በሃሰተኛ ምስክሮች በደል ከደረሰባቸው ግለሰቦች መካከልም በሞጃና ወደራ ወረዳ ሰላ ድንጋይ ከተማ ነዋሪ ጉዳይ አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል።

ግለሰቧ የእንጀራ ልጃቸውን ገድለዋል በሚል የሰሜን ሸዋ ዞን ዐቃቤ ህግ የወንጀል መዝገብ ቁጥር 134/2008 ክስ ተመስርቶባቸው ሲከራከሩ መቆየታቸውን ኮማንደር ደበበ አስታውሰዋል።

የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበውን ወንጀል በመመርመር ምስክር በማሰማት ጥፋተኛ ናት ብሎ በ20 ዓመት ጽኑ እስራትና በአምስት ዓመት ከማንኛውም ማህበራዊ ግንኙነት እንዲገለሉ ውሳኔ ማስተላለፉን ጠቅሰዋል።በተሰጠው ውሳኔ መሰረትም ግለሰቧ አምስት ዓመት ከሁለት ወራት ያህል በማረሚያ ቤት በእስር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ሆኖም ሞተች ተብላ በሃሰተኛ ምስክሮች የተረጋገጠላት ግለሰብ ከሌላ አካባቢ በህይወት ቆይታ በቅርብ ጊዜ ወደ ትውልድ አካባቢ መምጣቷን ማወቅ እንደተቻለ ኮማንደር ደበበ አብራርተዋል።

ሞተች ተብላ ጥፋተኛ ያልሆነችን ግለሰብ እንደጥፋተኛ ተቆጥራ ማረሚያ ቤት እንድትወርድ ያደገችው ግለሰብ ማንነቷ በአካባቢው ማህብረተሰብ እንደተረጋገጠ ገልጸዋል።

“በሃሰተኛ ምስክሮች እና በምርመራ መላላት የማህበረሰቡን መልካም እሴቶች ከማጠልሸቱም በላይ በመንግስት ሀብት ያለአግባብ የሚያባክኑ በመሆናቸው ሃሰተኛ ከሳሾችና ምስክሮች መንግስት ጠበቅ ያለ እርምጃ ሊወስድ ይገባል” ብለዋል።

ግለሰቧ በአማራ ክልል የተሻሻለው የይቅርታ አሰጣጥ መወሰኛ መመሪያ ቁጥር 30/2010 መሰረት ጉዳያቸውን ለይቅርታ ቦርዱ በማቅረብ በሚሰጠው ውሳኔ መሰረት ተፈጻሚ እንደሚሆን ኮማንደር ደበበ አስረድተዋል። ተበዳይዋ ግለሰብ በበኩላቸው በወቅቱ ጉዳዩን ሀሰት እንደሆነ ለመከራከር ብሞክሩም በፍትህ መዛባት ምክንያት ያለ ጥፋታቸው ለእስር እንደተዳረጉ ገልጸዋል።

ሞታለች የተባለችው ልጅ በህይወት መገኘቷ በመረጋገጡም በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁና ለደረሰባቸው በደልም ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል። ሃሰተኛ ምስክሮችና ከሳሾች በፈፀሙት ወንጀል በህግ እንዲጠየቁ መደረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

See also  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ - ለሚሰሙ ይህን ጥሪ አሰምተዋል

Via – ሚያዚያ 09 ቀን 2013 (ኢዜአ)


Leave a Reply