‹‹በትግራይ ያለው ቀጣይ የእርሻ ስራ ትልቅ ትኩረትና አስቸኳይ እገዛ ይፈልጋል ›› ዶ/ር አባዲ

አዲስ አበባ፡- በትግራይ ያለው ቀጣይ የእርሻ ስራ የሁሉንም አካላት ትልቅ ትኩረትና አስቸኳይ እገዛ እንደሚፈልግ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አባዲ ግርማይ አሳሰቡ፡፡

ዶክተር አባዲ በተለይ ለወጋሕታ ጋዜጣ እንዳስታወቁት ፣ ለቀጣይ የእርሻ ወቅት ሁሉም አካላት ትልቅ ትኩረትና አስቸኳይ እገዛ አድርገው ወደ ስራ መግባት ካልተቻለ ችግሩ ብዙ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል።

ገበሬው በአሁኑ ሰአት መሬቱን ማረስና ለዘር ማዘጋጀት ካልቻለ መዝራትና ማረስ ካልቻልን በሚመጡት ሶስትና አምስት ዓመታት ድረስ የሚዘልቅ

 ትልቅ ችግር ላይ ልንወድቅ እንችላለን ብለዋል።

በተረጋጉ የክልሉ አካባቢዎች መሬት የማረስ ስራ መጀመሩን ያመለከቱት ዶክተር አባዲ ፣ በቂ ማዳበርያ እና የዘር አቅርቦት አለመኖሩን አስታውቀዋል። ገበሬው ወደ እርሻ ለማስገባት ገንዘብ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የትግራይ የእርሻ መዋቅር ፈርሷል ያሉት ዶክተር አባዲ፣ የእርሻ መሳርያ፣ ማዳበርያና ዘር የግብርና ስራውን ለማስጀመር ወሳኝ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ሆኖም ትልቁ ችግር ጊዜ እየሄደ ነው ፤ ይህ ወቅት ካለፈ ሁኔታዎችን ለማስተካከል አስቸጋሪ እንደሚሆን ያመለከቱት ዶክተር አባዲ ፣ በዚህ ሰዓት በተለይ ዘር አስፈላጊ እንደሆነና በጣም ለተጎዳ አካባቢ ከተለያዩ አጋዥ ድርጅት ገንዘብ በማሰባስብ እንዲገዛ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል ።

በትግራይ ለእርሻ የሚሆን በሬ እንደሌለ የገለፁት ዶክተር አባዲ ፣አንድ በሬ ለመግዛት ከ 25ሺ እስከ 30ሺ ብር እንደሆነ እና ለዚህም 350 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።ይህን ለማስተካከል በቂ እገዛ ከተገኘ ትራክተር በመከራየት ወደ 15ሺ ሄክታር መሬት ለማረስ እየታሰበ እንደሆነ ገልፀዋል።ለዚህም 120 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

ዘርን በሚመለከት ከተለያዩ ድጋፍ ሰጪዎች 120ሺ ኩንታል የሚያስገዛ ድጋፍ ለማድረግ ቃል እንደተገባ ፣ የትግራይ እርሻ 600ሺ ኩንታል ዘር ያስፈልገዋል ለዚህም 2.4 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋስትና 800 ኩንታል ማዳበርያ ግዢ እንደተፈፀመ ጠቁመዋል፡፡

ገበሬው በርትቶ ካገዘን እኛም እምንችለው ካደረግን የእርሻውን ስራ መጀመር ይቻላል ያሉት ዶክተር አባዲ ፣ ቢያንስ በቀጣይ ዓመት የራሳችንን ዘር እና ቀለብ እንዲኖረን መስራት ይገባናል ብለዋል።የትግራይ ህዝብ ታታሪ ነው፣ በዚህ ሰዓት ትንሽ እገዛ ነው የሚፈልገው ያሉት ሃላፊው፣ የሰላምና መረጋጋት ጉዳይም ትኩረት የሚሻ ነው ብለዋል።

በዚህ ሰዓት አርሰን መዝራት እንችላለን ወይ? የሚል የሁሉም ጭንቀት ነው ያሉት ዶክተር አባዲ ፣ ገበሬው ተስፋ እንዲያደርግ ያለንን አቅም ተጠቅመን መንግስትና ህብረተሰብ በማስተባበር ወደ እርሻ ለመግባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የእርሻ ስራውን ለማስጀመር የተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ እየጠየቅን እንገኛለን ያሉት ሃላፊው፣ አብዛኛው ቃል የተገባ በተግባር ላይገኝ ይችላል፣ ሁኖም ዘርንና ማዳበርያ ለማቅረብ ሊያግዙን ከሚችሉ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ወደ እርሻ ለመግባት እንሞክራለን ብለዋል፡፡

የሚመጣው ድጋፍ አሁን ካልደረሰ ምንም ጥቅም እንደሌለውና ፣ማገዝ የሚፈልግ ዓለም አቀፍ ተቋም፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የትግራይ ተወላጅ ሆነ ማንም ሰብአዊነት የሚሰማው አካል በዚ ሰዓት ሊደርስልን ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመሰረት ገ/ዮሃንስ – አዲስ ዘመን ሚያዚያ 14/2013


Leave a Reply

%d bloggers like this: