ከጥቂት ዓመታት በፊት በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆች ሲዘዋወር ያየሁትን እጅግ ቁም ነገር አዘል መልዕክት በመጥቀስ ጽሑፌን ልጀምር።

“በቂ መረጃ በሌለኝ ጉዳይ ላይ ባለመዘባረቅ ለሃገሬ ሰላም የበኩሌን አበረክታለሁ” ይላል መልዕክቱ። ይህ በአንድ መስመር አጠር ብሎ የተላለፈው ትልቅ መልዕክት በተለይ አሁን ላይ ቢተገበር ብዬ ተመኘሁ።

ሀገራችን በተለያዩ ችግሮች ተወጥራ ባለችበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት፣ እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ለችግሮቿ መፍትሄ መሆን ባልችል እንኳን ችግሮቿን አባባሽ መሆን የለብኝም የሚል እምነት አለኝ።

በእርግጥ በጣም ውስብስብ በሆነና ተጨማሪ ምርመራን በሚጠይቅ ሁኔታ እዚህም እዚያም የሚሰማው የወገኔ ሞትና መፈናቀል፣ የንብረት መውደም እና የከተሞች መፈራረስ ዜና አንገታችንን የሚያስደፋ እና ልብ ሰባሪ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።

በንፁሃን ዜጎች ደም መፍሰስ ማዘን እና መብከንከን ሰዋዊ ባህሪ ቢሆንም ሀዘንን ዋጥ አድርጎ ይህ ጥቃት ነገም በሌላኛው ወገኔ ላይ ተፈፅሞ ለሌላ የልብ ስብራት እና ጥልቅ ሃዘን እንዳንዳረግ ምን ማድረግ አለብን ብሎ መምከር እና መዘየድ የትልቅ ህዝብ መገለጫ ነው።

ይህን መሰል ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መደጋገም አገርን እስከማፍረስ ሊያደርሱ እንደሚችሉ ማሰብ እና ቀድሞ መዘጋጀት ብልህነት ነው።

አገርን የማዳን ስራ ደግሞ ለአንድ ወገን(አካል) የሚተው ጉዳይ አይደለም።

አገርን የማዳን ሃላፊነት የኔ፣ ያንተ፣ ያንቺ ባጠቃላይ የሁላችንም ነው።
የመንግስትን ኃላፊነት እና ግዴታ ለመንግስት እንተውና እስኪ የእኔ ኃላፊነት ምንድነው? እንዴትስ ልወጣው? ብለን እያንዳንዳችን ኃላፊነት እንውሰድ።

ይህች ሃገርኮ የእኛ ነች። ሰላማችንን፣ አብሮ የመኖር እሴቶቻችንን የማስጠበቅ ኃላፊነት የመንግስት ብቻ ሳይሆን የኛም ጉዳይ ነው፡፡ ምንም እንኳን የኃላፊነት ድርሻችን የተለያየ ቢሆንም።

የዜጎችን ሰላም የማስጠበቅ እና የህግ የበላይነትን ማስከበር የመንግስት ድርሻ ሲሆን በቂ እውቀትና መረጃ በሌለን ጉዳይ ላይ (በተለይ የእርስ በእርስ ግጭትን በሚያባብሱ) ጉዳዮች ላይ የተሳሳተ መረጃ ያለመስጠት ኃላፊነት አለብን።

ይህችን ትንሿን ኃላፊነታችንን በአግባቡ ብንወጣ እስካሁን ያጋጠሙንን የሰው ህይወትና ንብረት ኪሳራ በእጅጉ መቀነስ በቻልን ነበር።

“ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንዲሉ አበው ግጭት በተከሰተበት ስፍራ ሳይሆን በኢትዮጵያ የማይኖርና ምንም መረጃ የሌለው ቅጥረኛ አክቲቪስት ያሰራጨውን የጥፋት መረጃ የሚቀባበለውና የሚያስተጋባው ወገን ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።

በዚህ የተሳሳተ መረጃ ዜጎች ለአላስፈላጊ ግጭት ሀገራችን ደግሞ ለሌላ ተጨማሪ ችግር ትዳረጋለች።

በዚህም አንድነታችን ይሸረሸራል። አንድነታችን ካጣን ኃይል አቅም አይኖረንም።

ጠላቶቻችን ደግሞ የተዳከምን ሲመስላቸው ኢትዮጵያን የማፈራረስ ህልማቸውን እውን ለማድረግ ይጣጣራሉ። ምንም እንኳን ህልማቸው ባይሳካም ሁሉም ነገራችን ከዜሮ ይጀምራል። ኢኮኖሚያችን ይደቃል፤ ልማታችን ይደናቀፋል።

ለሶሪያ ማለቂያ የሌለው የእርስ በእርስ እልቂት እና በሚሊየን ለሚቆጠሩ ዜጎቿ ሞት፣ ስደትና እንግልት ኃሰተኛ መረጃዎች ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ አበርክተዋል።

ጠንካራ ህዝብ የችግሮችን ምንጭ መርምሮ ለመፍትሔው ይዘይዳል እንጂ በተባራሪ የበሬ ወለደ ትርክት ተነሳስቶ ወገኑ ላይ ጦር አይሰብቅም። አገርን ለማፈራረስ አይጣደፍም።

የሚደርሰውን መረጃ በሰከነ አዕምሮ እና ብስለት ይመለከተዋል እንጂ እውነትነቱ ያልተረጋገጠን መረጃ ለሌላው አያጋራም።

መረጃው የተረጋገጠ እንኃ ቢሆን ለሌላው ከማጋራታችን በፊት የመረጃው መሰራጨት ለሀገራችን እና ህዝባችን ያለው ፋይዳ ምንድን ነው? ብሎ መመርመር አንድ ሀገሩን እና ህዝቡን የሚወድ ሰው ተግባርና ኃላፊነት ነው።

ሁላችንም የተሳፈርንባት ኢትዮጵያ የተሰኘች መርከብ ሳትሰጥም እና በወጀብ ሳትመታ እንድትንሳፈፍ ሁላችንም የየራሳችንን ድርሻ መወጣት ይኖርብናል።

ሀገሬና ህዝቤን ስለምወድ እውነትነቱ ያልተረጋገጠን መረጃ ለሌሎች ባለማጋራት ለአገሬ እና ህዝቤ ሰላም የበኩሌን ድርሻ አበረክታለሁ! እናንተስ?

ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ከክፉ ያርቅ!

(በነስረዲን ኑሩ)


    Leave a Reply