አቡል ሚስክ፡ ግብጽን የገዛው ኢትዮጵያዊ ወዚር

ባለ ታሪካችን “አቡል ሚስክ ካፉር” ይባላል፡፡ በአስረኛው ክፍለ ዘመን የኖረ ትውልደ-ኢትዮጵያዊ የግብጽ ገዥ ነው፡፡ አቡል-ሚስክ ወደ ግብጽ የተወሰደው በጉርምስና ዕድሜው በባርነት ተሸጦ ነው፡፡ በዘመኑ ባሮችን መሰለብ በሰፊው ይተገበር ነበር፡፡ በመሆኑም አቡል-ሚስክም ወደ ግብጽ የተወሰደው ጃንደረባ (eunuch) ሆኖ ነው፡፡

አቡልሚስክ በ923 በአንዱ ቀን ለገበያ ቀርቦ ሳለ “የኢኽሺዲ” ስርወ-መንግሥት መስራች የነበረው ሱልጣን ሙሐመድ ኢብን ቱግጅ በድንገት አየው፡፡ ኢብን ቱግጅ በብላቴናው ወጣትነት ተማረከ፡፡ ወደ ነጋዴዎቹ ቀረብ ካለ በኋላም “ይሄ ወጣት ከየት ሀገር ነው የመጣው?” በማለት ጠየቃቸው፡፡ ነጋዴዎቹም “ከሐበሻ ነው” በማለት መለሱ፡፡

ኢብን ቱግጅ የነጋዴዎቹን ምላሽ ሲሰማ የጥንቱ ቢላል ኢብን ረባህ ትዝ አለው፡፡ በደም ፍላት መንፈስም “የሐበሻን ልጅ ነው እንዲህ አስራችሁ ለሽያጭ ያመጣችሁት? የነጃሺ ውለታ ተረስቶ ነው የሐበሻ ልጅ በሀገሬ ምድር በባርነት የሚሸጠው?” በማለት በንዴት ወረደባቸው፡፡ ነጋዴዎቹም “እኛ እኮ አይደለንም የፈነገልነው! ከሀገሩ ነጋዴዎች ነው ገዝተን ያመጣነው” በማለት መለሱለት፡፡

ኢብን ቱግጅ “በሉ ቶሎ ለኔ ስጡኝ! ሁለተኛ የሐበሻ ተወላጅ የሆነን ሰው በባርነት እንዳትሸጡት” በማለት አቡልሚስክን ከነጋዴዎቹ እጅ ተረከበው፡፡ ወደ ቤተ መንግሥቱ ወስዶትም ልብሱን ከቀየረለት በኋላ እዚያው እንዲኖር ፈቀደለት፡፡ በዘመኑ በታወቀው ኒዛሚያ መድረሳ የካይሮ ቅርንጫፍ አስመዝግቦት ትምህርቱን እንዲማርም አደረገው፡፡

ወጣቱ አቡልሚስክ በትምህርት ቆይታው ዐጃኢበኛ ተማሪ ወጣው፡፡ በትምህርት መደቡ ከሁሉም ተማሪ መካከል አንደኛ እየወጣ ይሸለም ጀመር፡፡ ሌሎች ተማሪዎች ብዙ ዓመታት የሚወስድባቸውን የዒልም ጉዞ እርሱ በጥቂት ዓመታት ውስጥ አጠናቀቀው፡፡ ሱልጣን ሙሐመድ ኢብን ቱግጅ የአቡል ሚስክን ጉብዝና ሲያይ እርሱን ከነጋዴዎቹ እጅ መንጭቆ የወሰደበትን ቀን አወደሰው፡፡

የመድረሳው ኃላፊዎች አቡልሚስክን “ሙዓሊም” (ፕሮፌሰር) አድርገውት ሊቀጥሩት ፈልገው ነበር፡፡ ሱልጣን ሙሐመድ ግን “እርሱን ለከፍተኛ ስራ ስለምፈልገው አስተማሪ አይሆንም” በማለት ከለከላቸው፡፡ ወደ ቤተ መንግሥቱ ወስዶትም ዋና አማካሪው አድርጎ ሾመው፡፡ ልጆቹ እንደርሱ ጎበዝ እንዲሆኑለት ስለተመኘም ከስራ ሰዓት ውጪ የግል መምህራቸው ሆኖ እንዲያስተምራቸው መደበው፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ በግብጹ ሱልጣን ስር ይገዙ በነበሩት ሶሪያና ሒጃዝ አመጽ ፈነዳ፡፡ ሱልጣን ሙሐመድ የመደባቸው ጄኔራሎች እየተሸነፉ ከግዛቶቹ ተባረሩ፡፡ ሱልጣኑ አመጹን ለመቆጣጠር እንዲመቸው አዲስ ጦር አዘጋጀ፡፡ አቡልሚስክንም የዚህ ጦር አዛዥ አድርጎ አዘመተው፡፡ አቡልሚስክ ወደ ሶሪያና ሒጃዝ ገብቶ አማጺዎቹን ድል በማድረግ ሱልጣኑ በግዛቶቹ ላይ የነበረውን የበላይነት አስከበረ፡፡

See also  "ዝናብ አትገድቡ ተብለን በቀረብንበት መድረክ 'ድል ተገኘ ' ብሎ መፈንጠዝ ነገሩ እንዳልገባን አመላካች ነው"

አቡልሚስክ በስልጣን ላይ ሳለ ከፈጸማቸው ዋና ተግባራት አንዱ ትምህርትን ማስፋፋቱ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በግብጽ ምድር በመቶ የሚቆጠሩ መድረሳዎችን ገነባ፡፡ ለትምህርት የሚሆን መደበኛ ፈንድም መሠረተ፡፡ ለአስተማሪዎች በቂ ክፍያ እንዲፈጸምም አደረገ፡፡ በዘመኑ ተዳክሞ የነበረው የአልኬሚ ምርምር እንዲጠናከር በትጋት ሠራ፡፡

አቡልሚስክ በዘመኑ መለኪያ በቂ በሚባል ደረጃ የተማረ ሰው ቢሆንም እውቀትን ጠግቦ አያውቅም፡፡ በመሆኑም በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው እውቀት የመጠቁ ምሁራንን ወደ ቤተመንግሥቱ እየጠራ ያወያያቸው ነበር፡፡ ለገጣሚዎችም ፍቅርና ክብር ነበረው፡፡ በዚህ ሁኔታ ወደ ቤተመንግስቱ ከመጡት አንዱ ታዋቂው ገጣሚ “አል-ሙተነቢህ” ነው፡፡

አል-ሙተነቢህ ጎበዝ ገጣሚና ባለቅኔ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁንና ከገጣሚነቱ ባሻገር ስልጣንና ገንዘብም በብዛት ይወድ ነበር፡፡ ወደ ካይሮ ከተማ የመጣውም የሶሪያው ገዥ ስልጣን ስላልሰጠው “የርሱ የበላይ ከሆነው የግብጽ ሱልጣን ዘንድ ሄጄ ፍላጎቴን መፈጸም እችላለሁ” በሚል ምኞት ነበር፡፡

አቡልሚስክ የአልሙተነቢህን ቅኔዎች ቢያደንቅም ሌሎች ሰዎችን እየተነኮሰ መዘባበቻ እንደሚያደርጋቸው ያውቅ ነበር፡፡ ስለዚህ ወደ ቤተመንግሥቱ በጣም እንዲቀርብ አልፈቀደለትም፡፡ በከተማዋ አንድ ቤት ሰጥቶት ለኑሮው መደጎሚያ የሚሆን ተቆራጭ ብቻ ይልክለት ነበር፡፡ አልሙተነቢህ አቡልሚስክን በቅኔዎቹ እየደጋገመ ቢያሞግሰውም ወዚሩ ፊት አልሰጠውም፡፡ ገጣሚው አልሙተነቢህ ለሶስት ዓመታት (ከ957-960) የገዥውን ልብ ለማማለል ያደረገው ሙከራ ስላልተሳከለት ከግብጽ ወደ ኢራቅ ለመሰደድ ወሰነ፡፡ ታዲያ ወደ ባግዳድ ሲሄድ በልቡ የተደበቀውን በሽታ ይፋ ያወጣበትንም ድርጊት ፈጸመ፡፡ አቡልሚስክ በባርነት ተፈንግሎ ወደ ግብጽ የመጣ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ መሆኑን እየጠቀሰ አንድ ገጽ የሚሆን ቅኔ ጻፈበት፡፡

አቡልሚስክ ግብጽንና በርሷ ስር የነበሩትን ግዛቶች (ሂጃዝ፣ ሶሪያ፣ ፈለስጢን) ለሀያ ዓመታት ከገዛ በኋላ በ966 የገዥነቱን ስልጣን ዓሊ ለተባለው የሱልጣን ሙሐመድ ልጅ አስረከበ፡፡ ከመንግሥት ስራ ሙሉ በሙሉ ተገልሎም በዒባዳና ሌሎችን በማስተማር ህይወቱን መግፋት ጀመረ፡፡ በ968 ግን በተስቦ በሽታ ተለክፎ አረፈ፡፡

አፈንዲ ሙተቂ
ጥር 3/2010
በሸገር ተጻፈ፡፡

Leave a Reply