መንግሥታችን ሆይ! ስምህን የተሸከሙ ተቋማትን ፈትሽልን -ዳግላስ ጴጥሮስ

የሀገራችንን ተቋማት ቢያንስ በአራት ዋና ክፍሎች መመደብ ይቻላል።ምደባውን በአምስትም፣ በስድስትም የሚከፍሉ ካሉም ችግር የለውም።ብቻ መሠረታዊ መልእክቱ ይድረስልኝ።በጸሐፊው ምልከታ የመጀመሪያዎቹ ተቋማት መንግሥታዊ የሚል “ማዕረግ” የተሸከሙት ናቸው።እነዚህ ተቋማት ቀለባቸው የሚሰፈርላቸውና የሠራተኞቻቸው የዕለት እንጀራ (“ደመወዝ”) የሚጋገርላቸው ከመንግሥት ጎተራ እየታፈሰ ነው።የመንግሥት ማዕድ ቤት ይሙላም አይሙላ ለእነዚህ ተቋማት እምብዛም ችግራቸው አይደለም።ሕግ የሚፈቅድላቸውን መንግሥታዊ በጀት እየዘገኑ ራሳቸውንና ሠራተኞቻቸውን እየቀለቡ ያኖራሉ።

ሠራተኞቻቸውም ቢሆኑ የ“ደመወዛቸው” አዝመራ የሚታጨደው ከድሃው የሀገሪቱ ዜጎች ኪስና አፍ በግብርና በታክስ ስም በእሽቅድምድም እየተሸመጠጠ ስለሆነ የመንግሥታዊው ጎተራ መትረፍረፍም ሆነ መሟጠጥ እጅግም አያስጨንቃቸውም።ከነስማቸውስ መታወቂያቸው የመንግሥት ሠራተኞች ወይንም በባዕድ ስያሜው (Civil Servants) እየተባሉ አይደል።በግሌ ባዕድ ናፈቂ ካላሰኘ በስተቀር የአማርኛው ስያሜ ከዚህኛው የፈረንጅ አፍ ተተርጉሞ “የሕዝብ አገልጋዮች” ቢባል ወይንም እንዳለ እንግሊዘኛውን መጠቀም ቢቻል ትርጉሙ ለሀገራችን የምር ይመጥን ይመስለኛል።

ችግሩ ተግባሩ “የመንግስት ሥራ” መባሉና ስማቸውም በመንግሥት ትከሻ ላይ ፊጥ ብሎ “የመንግሥት ሠራተኞች” በሚል መለያ መንጠልጠሉን ደፍረን ብዙ እንዳንናገር፤ ብንናገርም አድማሱ ስለሚሰፋ እሪታችን የቁራ ጩኸት እየሆነ የተቸገርነው የተሸከሙት ከባድ ስም ጥላው ስለሚገዝፍብን ይመስለኛል፡፡

ሁለተኛዎቹ የተቋማት ዓይነቶች የላይኛውን መጠሪያ በማፍረስ “መንግሥታዊ ያልሆኑ” (Non-Governmental) በመባል የሚታወቁት ናቸው።የእነዚህ ተቋማት የስንቅ አገልግል በአብዛኛው ተሸክፎ የሚመጣው ከባዕዳን ሀገራትና ዜጎች የተራድኦ ስም የሚል መለያ እየተለጠፈለት ነው።ተቋማቱም ሆኑ ሠራተኞቻቸው የወር አስቤዛቸውንና የዓመት ቀለባቸውን የሚያወራርዱት በአብዛኛው ባህር ተሻግሮ በመጣ ሙዓለ ነዋይ ነው።ሲከፈላቸውም አብዛኛውን ጊዜ በፖስታ ታሽጎ እንጂ እንደ መንግሥት ሠራተኞች ጥሬው ብር በምራቅ በረጠቡ ጣቶች እየተቆጠረ አይደለም።የገንዘቡ መጠንም ቢሆን ለብዙዎች ሚዛኑ ከፍ ያለ፣ ምንዛሪውም የበረታ ስለሆነ ከመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ እስኬል ጋር የሚነጻጸረው ከጎልያድና ከዳዊት አቅም ጋር ነው፡፡

ሦስተኞቹ ተቋማት “የግል” የሚሰኙት “የእኔነት” ውጤቶች ናቸው።እነዚህ ተቋማት በአብዛኛው ህልውናቸው የተመሰረተው በግለሰቦች ብርታትና ጥንካሬ ላይ ስለሆነ “የላብ ውጤቶች” ናቸው ማለት ይቻላል።ከመንግሥት ተቋማት ጎን ለጎን ሌላኛውን የሀገር ወጋግራ የተሸከሙት እንደነዚህ ዓይነቶቹ የግል ድርጅቶች/ኩባንያዎች/አክሲዮን ማኅበራት ወዘተ. ናቸው።እርግጥ ነው አንዳንድ የግሉ ዘርፍ ድርጅቶች የህልውናቸውን እስትንፋስ የሚያቆዩት በላይኞቹ ሁለት ተቋማት “ባላዎች” ላይ ተንጠልጥለው ስለመሆኑ ቢጠቆም ከሃሜት አያስቆጥርም።“ሁለት ባላ ትከል፤ አንዱ ቢነቀል በአንዱ ተንጠልጠል” እንዲሉ መሆኑ ነው።

እነዚህን መሰል የግል ተቋማት ሁነኛ መገለጫቸው (ሁሉንም ባይመለከትም) የግብርና የታክስ ክፍያቸውን በተመለከተ ከመንግሥት ጋር “ሌባና ፖሊስ” ወይንም እንደ ልጅነታችን “በድብብቆሽ ጨዋታ” የሰለጠኑና የተራቀቁ መሆናቸው ነው።በላብና በወዛቸው የረጠበ ረብጣ የታቀፉ ምስጉኖች የመኖራቸውን ያህል በአንጻሩም በሸርና በሴራ የናጠጡም መኖራቸው እኛ ብቻ ሳንሆን “ሰማያዊቷ ፀሐይም” ራሷ ለመመስከር አትሽኮረመምም፡፡

አራተኞቹ ተቋማት የእስትንፋሳቸው ምንጩ ከፈጣሪ ዘንድ መሆኑን የሚያምኑና የሚያሳምኑ፤ የሃይማኖት ካባ ደርበው ወይንም ተጎናጽፈው ፈጣሪ በፀጋው ያኖረናል እያሉ በምእመናን መባና አስራት ወይንም ዘካ የሚተዳደሩት ዓይነቶች ናቸው።እምነታቸውና መልካም ተግባራቸው በአደባባይ የሚመሰከርላቸው ጥቂት የሃይማኖት ተቋማት መኖራቸውን ሳንክድ የአብዛኞቹን ገመና እንፈትሽ ብንል የመሪዎቹ “ውግዘት እና ፈጣሪን አታስቆጡ” የሚለው ማስፈራሪያቸው ባይገድበን ኖሮ ጓዳ ጎድጓዳቸውን ዘክዝከን አሰር ገሰሱን መዘርገፍ ይቻል ነበር።ተቋማቱንም ሆነ መሪዎቹን ጫን ብለን እንዳንዳፈር በዋነኛነት “ወልድ ሲነካ አብ ስለሚቆጣ” ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ስለሚቀር “ሾላ በድፍን” ብሎ ማለፉ ይቀላል፡፡

ስምን ተሸክሞ ግብርን ረስቶ፤

አራቱንም የተቋማት ዓይነቶች አንድ በአንድ በተግባራቸው መፈተሽ ቢቻልም አነሳሳችን ሲለሚወስነንና የዐምዱ ጥበትም ስለማያወላዳን ቀሪዎቹን ሦስቱን ተቋማት ለጊዜው በይደር አስተላልፈን ስለ መጀመሪያው መንግሥታዊ ተቋማት ጉዳይ ጥቂት ቁዘማ ማድረጉ ይሻል ይመስለናል፡፡

የአብዛኞቹን የመንግሥት ተቋማት የቅርብ ጊዜ የአገልግሎት አሰጣጥ ብልሹነት በተመለከተ ቢያንስ አንድ አጠቃላይ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አይቸግርም።አጠቃላይ መዳረሻው ሁሉንም ይመለከታል ብሎ መደምደሙ ቢያዳግትም የመጥፎ ጠረኑ ሽታ ያልጎበኘው መንግሥታዊ ተቋም ማግኘት ከተቻለ ዕድለኛነት ብቻም ሳይሆን በአደባባይ ከፍ ተደርጎ ቢጨበጨብለትም አይከፋም፤ ይገባዋልም።ለዚህም ነው “መንግስት ሆይ! ስምህን የተሸከሙ ተቋማትን ፈትሽልን?” በማለት አቤቱታ ለማቅረብ የተገደድነው፡፡

በየትኞቹም የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት ለመጠየቅ የሄደ ዜጋ “በአግባቡ ተገልግዬና መብቴ ተከብሮልኝ፤ እኔም ነዎሩ ተብዬና ተስተናግጄ ተመለስኩ” የሚል ምስክር ከተገኘ ምናልባትም የረዳውና ያገዘው በማለዳ ጸልዮ የወጣው ጸሎት ተሰምቶለት ወይንም “ሥራ ክቡር ነው! ማገልገል መባረክ ነው!” የሚል እምነት የተላበሱ ጨዋ ኢትዮጵያዊያን ቅሪቶች አጋጥመውት ስለሚሆን ፈጣሪውን የጾም ጸሎት ጊዜ ወስኖ ሊያመሰግን ይገባዋል፡፡

መሠረታዊ የሚባሉትን የውሃና የመብራት አገልግሎቶች ለማግኘት እንኳን ወደ “መንግሥታዊዎቹ” ተቋማት ጎራ ያለ ሰው እንደምን ተዋርዶ፣ ተንጓጦና ተሰድቦ ጭምር እንደሚገፈተር የዕለት ገጠመኛችን ስለሆነ ተለማምደነዋል።“መብቴ እኮ ነው!” ብሎ መከራከር እነዚህ ተቋማት ውስጥ መደመጥ ካቆመ ዓመታት ተቆጥረዋል።በዚህ ጉዳይ እንኳንስ እኛ ምድራዊያን ዜጎች ቀርተን ፈጣሪ ራሱ “የመንግሥትን ስም የተሸከሙ የሀገራችንን ተቋማት” በተመለከተ ከአቅሙ በላይ እንደሆነበት አምነንና በአሜንታ ተቀብለን ከችግሩ ጋር ተላምደን በእህህታ ቀን መግፋቱን ምርጫችን አድርገናል።

በርካታ መንግሥታዊ ተቋማት በሰበሰቧቸው ምንግዴ ኃላፊዎችና ሠራተኞቻቸው አማካይነት ሕዝብን ለማሳዘንና ለማስለቀስ ተልዕኮ የተሰጣቸው ይመስል ስራቸው ዜጎችን ማበሻቀጥና ማዋረድ ከሆነ ወሎ አድሯል።ቆሽታችን አሮና ደብኖ ከማለቁ በፊት “የመንግሥት ያለህ!” ብለን መጮኹ አግባብ መስሎ ታይቶናል።“ምን ይደረግ ውሱን ሃብታችን ለዜጎች ሁሉ መዳረስ ስለማይችል ነው” የሚለው “የከረቫት ለባሾቹ ሹማምንት” አሰልቺ መልስ የቃር ያህል እየጎረበጠን ስለሆነ ደጋግመው ባይሸነግሉን እንመርጣለን።አገልግሎቱ የማይዳረስ መሆኑ መች ጠፋን።ጩኸታችን የዜግነት መብታችን እንኳን ቢቀር የሰብእናችን ክብር ሳይጎድፍ በአግባቡ አስተናግዱን ነው፡፡

በብዙ ቀበሌዎች፣ ወረዳዎች፣ ክፍለ ከተሞችና የክልል ቢሮዎች አገልግሎት ለመጠየቅ የሚሄድ ማንኛውም ዜጋ አስቀድሞ “ተናግሮ አናጋሪ ሰይጣንን እንደ እምነቱ በጸሎት አስሮ ካልሄደ በስተቀር” የሚመለሰው የስኳርና የደም ግፊት በሽታዎቹ እያስቃሰቱት ይሆናል።ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ስለ ሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም መወራት ከጀመረ ወዲህ ችግሩ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ሪፎርመኞቹ ወረድ ብለው ቢያዩት ክብራቸው ዝቅ እንደማይል እኛ ግፉዓን ዜጎች እናረጋግጥላቸዋለን፡፡

በተደጋጋሚ እኔም ሆንኩ ሌሎች ጸሐፍት በዚሁ አንጋፋ ጋዜጣ ላይ “የየብዕራችንን ቀለማት ለማፍሰስ እንደሞከርነው” የሀገራችን የፍትሕ ተቋማት መልክ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ እንደሚሄድ ሰሚ ባይገኝም “ሁለት እጆቿን ዘርግታ ሚዛንና ሰይፍ ለጨበጠችው እመቤት ሆይ ፍትሕ” አቤቱታችንን ሳንሰለች በጩኸት ከማሰማት አልቦዘንንም።የቀረን፤

“ጩኸቴን ብትሰሙ፤

ይሄው አቤት አቤት እላለሁ፣

በደል ደርሶብኝ እጮኻለሁ”

በማለት እንደ ነፍሰ ሄር ጥላሁን ገሠሠ በዜማ ማንጎራጎር ብቻ ነው፡፡

“የመንግሥት ስም ተሸከመው” ስለ ተቋቋሙት አብዛኞቹ የመንግሥት መስሪያ

ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ ብዙ ማለት ቢቻልም ብዕርን ማልፋት ስለሚሆን አንዳንዶቹን ብቻ ለማሳያነት ጠቃቅሶ ማለፉ ይበቃ ስለመሰለን እንጂ የችግራችንን ጎተራ ሙሉ ለሙሉ እንዘርግፈው ብንል ምሬቱና ጠረኑ ክፉኛ እያስነጠሰ ስለሚያሳምመን “በሆድ ይፍጀው” ማለፉን ግድ ይሏል፡፡

እንዲያም ቢሆን ግን ጸሐፊውን በቅርቡ የገጠመው አንድ ክስተት የሚታለፍ አይደለም።ይህ ጸሐፊ እግር ጥሎት በሁለቱ የመንግሥትና የግል ሰራተኞች ጡረታ ዋስትና ተቋማት ተገኝቶ ነበር።በእነዚህ ሁለት መንግሥታዊ ተቋማት የሚስተናገዱት ባለጉዳዮች በሙሉ የዕድሜያቸውን ዘመን ሁሉ ከፋም ለማ ሀገርና ሕዝብ ሲያገለግሉ ከመኖራቸው የተነሳ ጉልበታቸው የዛለና አንቱታ የሚገባቸው ባለ “ነጭ ሽበት ተጥዋሪ ጎምቱ ዜጎች (Senior Citizens) ናቸው።እንደ ሌሎች ሀገራት ባንታደል እንጂ እነዚህን መሰል የሀገር ባለውለታዎች ማገልገል የሚገባው ተቀምጦ ሳይሆን ቆሞ ጭምር መሆን ነበረበት።መቼስ ምኞት አይከለከልም አይደል!?

በእነዚህ ሁለት መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የጡረታ ፕሮሰሳቸውን ለማስጨረስ ወይንም አገልግሎት ለመጠየቅ የመጡ አረጋዊያን እንደምን ኢሥነ-ምግባራዊ በሆነ ድርጊት እንደሚበሻቀጡ ያስተዋልኩት በዓይኔ በብረቱ ነው።ምናልባትም የልጅ ልጆቻቸው በሚሆኑ ወጣቶች አንደበት ሲመነጫጨቁና ሲበሻቀጡ መመልከት በምድራዊም ሆነ በሰማያዊ ፍርድ የሚያስጠይቅ ይመስለኛል።“ልጄ ሀገሬን ሳገለግል መኖሬን አታከብሪልኝም” በማለት ቅሬታቸውን ያቀረቡ አንድ ባለጉዳይ ጡረተኛ የደረሰባቸውን ዘለፋ እዚህ መጥቀሱ የአንባቢን ሞራል አይመጥንም።እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ ኃላፊ ተብዬዋ አለቃ ተለጥጣ ሁኔታውን እያስተዋለች ሠራተኛዋን አለመገሰጽዋና መፍትሔ አለመስጠቷ ነው።የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ጉዳዩን በቅርብ ይከታተል ስለነበር ሥራዬ ብሎ ወደ ሌላኛው የበላይ ኃላፊ ዘንድ ሄዶ ሲያነጋግረው የተሰጠው መልስ በእጅጉ የሚያስፈግግም፤ የሚያሳምም ነው፡ “ሥነ ምግባር በእኔና በአንተ ዘመን ቀረ።ምንም ማድረግ አንችልም፡፡” የሚል ነበር።መንግሥታችን ሆይ ትሰማናለህን!?

ጥያቄዎችን ኮልኩለን ርዕሰ ጉዳያችንን እንቋጭ።ለመሆኑ በመንግሥት ተቋማት ከሥነ ምግባር ውጭ የሚያፈነግጡ ሠራተኞች የሚቀጡበት መመሪያ የላቸው ይሆን? ኃላፊ ተብዬዎቹስ ሥልጣናቸውና የኃላፊነት ድርሻቸው ተሽከርካሪ ወንበር ላይ ተሰፍተው በጸሐፊያቸው አማካይነት “ጃስ!” እያሉ ማስደንበር ነው? የባለ ጉዳዮችን ጠረን እያሸተቱ ለማገልገልስ ለምን ጥዩፍ ሆኑ? ለመሆኑ “የዕለት ቀለባቸው የሚሰፈርላቸው ከድሃው ጉሮሮ እየተነጠቀ” መሆኑን አልተረዱት? መንግሥታችን ሆይ እንደነዚህ ዓይነቱን ተቋማት ወይ ስምህን ንጠቃቸው ወይንም አርማቸው፡፡

መቼም ርዕሰ ጉዳዩን በእዬዬ ጀምሮ በእዬዬ መጨረሱ አግባብ ስላልሆን አንድ ልብ የሚያሞቅ ምስክርነት በማስታወስ በእፎይታ መሰናበቱ ይቀላል።ይህ ጸሐፊ “የታክስ አምባሳደር” የሚል የአገልግሎት አደራ ከመንግሥታችን ትልቁ ሰውዬ መቀበሉ ግድ ስለሚለው አልፎ አልፎ የገቢዎች ሚኒስቴር እና ቅርንጫፍ ተቋማቱ እየጋበዙት የማኅበራዊ ተሳትፎውንና የዜግነቱን አደራ ለመወጣት ተግቶ ጥረት ያደርጋል።በቅርቡ በሰሜን ምዕራብ አዲስ አበባ የገቢዎች ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት በተገኘበት አጋጣሚ ያስተዋለውን የተቋሙን ኃላፊ የመስተንግዶ ብቃትና የሠራተኞቹን የአገልግሎት አሰጣጥ በእጅጉ የሚያስመሰግን ሆኖ አግኝቶታል።ያለ ምንም ማጋነን የተቋሙ መሪ የአመራር ብቃትና የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍና የሚባል ብቻ ሳይሆን የቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ የቢሮ አደረጃጀት፣ ውበትና ለሥራ ምቹነት በራሱ ከብዙ የሀገራችን ከፍተኛ መንግሥታዊ ተቋማት በመቶ እጥፍ ብልጫ የሚያስንቅ ነው።የዚህን ምስክርነትና እውነታነት በቦታው ተገኝቶ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

እንዲህ ዓይነቶቹ ተቋማት፣ ኃላፊዎችና ሠራተኞቻቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ በይፋ ቢመሰገኑና አርዓያነታቸው ቢዘከር ለብዙ ግዴለሽ መንግሥታዊ ተቋማት፣ ሠራተኞችና ኃላፊዎች ትልቅ ትምህርት ሊሰጥ ስለሚችል ይመለከተኛል ባይ ክፍሎች ቢያስቡበት አይከፋም።በተረፈ ግን አብዛኞቹ “የመንግሥትን ክቡር ስም መሸከም አቅቷቸው የሚንገዳገዱ ተቋማት” የሚያስፈልጋቸው ሪፎርም ሳይሆን ዳግም ልደት (Rebirth) መሆኑን ቢረዱት አይከፋም።መንግሥታችን ሆይ! እሪታችን ተሰማህ!? ሰላም ይሁን!

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 16/2013 (ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ) gechoseni@gmail.com


    Leave a Reply