በእነ አቶ ታምራት ላይኔ መዝገቦች 20 ዓመታት በላይ ሲካሄድ የነበረ የፍርድ አፈጻጸም ክርክር መቋጫውን አገኘ

በአጠቃላይ ሰማንያ ስድስት ሚሊዮን


እነ አቶ ታምራት ላይኔ (9 ሰዎች) ተከስሰውበት በነበረው ከ1987 እስከ 1989 ዓ.ም ድረስ በነበሩት ጊዜያት የመንግስትን ስልጣን ያለአግባብ የመገልገል ወንጀል አቶ ታምራት ላይኔን ጨምሮ አምስት ተከሳሾች ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የወንጀል ቅጣት የተጣለባቸው ሲሆን አራቱ ተከሳሾች በወንጀሉ ምክንያት የተመዘበረን የመንግስት ሀብት እንዲመልሱ ተጨማሪ ውሳኔ ተሰጥቶ ነበር፡፡

ከተመዘበረው የመንግስት ሀብት መካከል ከኢትዮጵያ ቡና ላኪ ድርጅት አሰራር ውጪ በሆነ መንገድ 1000 ቶን ቡና ወደ ጅቡቲ ሀገር በባቡር እንዲላክና እንዲሸጥ በማድረጋቸው ከሽያጩም የተገኘውን ገንዘብ በመከፋፈላቸውና በወቅቱ የነበረው የቡና ዋጋ 4,200,000 (አራት ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺ) የአሜሪካን ዶላር፣ ለቀረጥ 703,802.51 ብር፣ ለሱር ታክስ 695, 000 ብር እንዲሁም ቡናውን በባቡር ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ ለማጓጓዝ 78,617.15 ብር ለመንግስት ገቢ እንዳይሆን ያደረጉትን እንዲመልሱ ተወስኖ እንደነበር የገለጹት አቶ ሄኖክ ተስፋዬ የፍትሃብሔር ፍትህ አስተዳደር ዳይሬክተር ጄኔራል ናቸው፡፡

ዳይሬክተር ጄኔራሉ የተደረገውን ክርክር አስመልክቶ እንደተናገሩት በወንጀል ፍርድ ቤቱ ተሰጥቶ የነበረው ይህ ውሳኔ አራቱም ተከሳሾች በአንድነትና በነጠላ እንዲከፍሉ ትዕዛዝ እንዲሰጥበት፣ ለዘገየበት ጊዜ በሙሉ ወለድ እንዲታሰብበት እንዲሁም በአሜሪካን ዶላር የተወሰነው በወቅቱ በነበረው የብር ምንዛሬ ተመን ተመንዝሮ እንዲከፈል እንዲደረግ የፍትሐ ብሔር ፍርድ አፈጻጸም ክርክር ሲደረግ ቆይቶ በተጠየቀው መሰረት አራቱ ተከሳሾች በአንድነትና በነጠላ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን፣ ከሰኔ 10/1987 ዓ.ም ጀምሮ ገንዘቡ ተከፍሎ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ በዓመት 9 በመቶ ወለድ እንዲከፍሉ እና ዋናው እዳ በወቅቱ በነበረው የምንዛሬ ተመን ተመንዝሮ እንዲከፈል ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በደረሱ የተለያዩ መዝገቦች ክርክሮች ሲደረጉ ቆይተው ውሳኔው ጸንቷል፡፡

ለዚሁ ይላሉ አቶ ሄኖክ፤ ለዚሁም ውሳኔ አፈጻጸም ይረዳ ዘነድ ዐቃቤ ህግ በ3ኛና በ4ኛ ተከሳሾች ስም በኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ አ.ማ ተመዝግቦ ይገኝ የነበረን የአክሲዮን ድርሻ አሳግዶ የነበረ ሲሆን የ4ኛ ተከሳሽ አክሲዮኖች በሌላ እዳ መክፈያነት በመሸጣቸው የ3ኛ ተከሳሽ አክሲዮኖችን በግልጽ ሀራጅ ለመሸጥ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት በኩል የሀራጅ ማስታወቂያ ወጥቷል፡፡ ሆኖም ግለሰቡ ቀርበው አክሲዮኖቹን በሌላ አኳኋን በመሸጥ በመንግስት የሚፈለግባቸውን ሙሉ እዳ ገቢ በማድረጋቸው የጨረታ ሂደቱ ተቋርጦ የፍርድ አፈጻጸም ሂደቱ መቋጫውን አግኝቷል፡፡

ከሰኔ 10 ቀን 1987 ዓ.ም ጀምሮ በዋናው የቡናው ዋጋ ላይ የ9 በመቶ ወለድ ተሰልቶ፣ ዋናውን እዳ ጨምሮ እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት ከዚሁ ጋር የተያያዙ ለመንግስት ገቢ የተደረጉ ገንዘቦች እና በክርክር ሂደቱ የወጡ ወጪዎች ተደምረው በአጠቃላይ 86,391,114.16 (ሰማንያ ስድስት ሚሊዮን ሶስት መቶ ዘጠና አንድ ሺህ አንድ መቶ አስራ አራት ብር ከአስራ ስድስት ሳንቲም) ለመንግስት ገቢ ተደርጓል፡፡

በስተመጨረሻም ዳይሬክተር ጄኔራሉ አቶ ሄኖክ ተስፋዬ ባስተላለፉት መልዕክት ይህ ከሁለት አስርተ አመታት በላይ ያስቆጠረ ረዥም የፍርድ አፈጻጸም ሂደት ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠናቀቁ የህዝብና የመንግስት ኃብት ተመዝብሮ እንደማይቀርና ምንም ያህል ጊዜን ቢፈጅ ከነወለዱ ተመላሽ መሆኑ እንደማይቀር በጎ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

Federal attorney general


Leave a Reply

%d bloggers like this: