በቅርቡ የመከላከያ ሠራዊት ዩኒፎርም በመልበስ በተለያዩ የዕምነት ተቋማት ሲያመልኩ የሚያሳይ መረጃዎች በሚመለከታቸው የተቋሙ የፍትህ አካላት ተጣርቶ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ የመከላከያ ሠራዊት አስታወቀ፡፡

የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በሰጡት መግለጫ ፤የመከላከያ ሠራዊት ገለልተኛ ፣ የትኛውንም የሀይማኖት ተቋም እንደማይወክል ገልፀዋል፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የማይወግን እና የማንኛውንም ዕምነት የማያራምድ መሆኑ በህገ- መንግስታቱም ይሁን በቅርቡ በጸደቀው የመከላከያ ስትራቴጂክ የግንባታ ሰነድና በአስተዳደራዊ ደንብ ላይ በማያሻማ ሁኔታ ተደንግጓል ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡

ከዚህ በፊት የመከላከያን የደንብ ልብስ በመልበስ በተለያየ የዕምነት ተቋም ሲያመልኩ የተገኙ በቁጥጥር ስር ውለው እና ሪሀብሊቴሽን ማዕከል ገብተው ቅጣታቸውን ፈጽመው የወጡ መኖራቸውን ኮሎኔል ጌትነት ጠቁመዋል።

መሰል ድርጊቶችም በሰራዊቱ ውስጥ ሲከሰቱ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸውን አመልክተዋል ፡፡

የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ በቅርቡ በተለያዩ የዕምነት ተቋማት የጀግናውን እና የየትኛውንም እምነት የማይወክለውን ሠራዊት የደንብ ልብስ በመልበስ የታዩ ግለሰቦችን በማጣራት ክስ ይመሰረትባቸዋል ነው ያሉት።

በእንደዚህ አይነት ጥፋት የሚገኙ የሰራዊት አባላት እስከ አምስት አመት የሚደርስ የእስር ቅጣር እንደሚበየንባቸው ገልፀዋል።

መከላከያ ሰራዊት ዕምነትም ሆነ ሀይማኖት የማይወክል በመሆኑ በዚህ ድርጊት የተሳተፉ አባላት እደዚህ ቀደሙም እርምጃም ይወሰድባቸዋል ብለዋል፡፡

የሠራዊቱ አባላት የፈለጉትን ዕምነት የመከተል መብት አላቸው ያሉት ኮሌኔሉ ይሁን እንጂ የተከበረውን የኢትዮጵያ ህዝቦች መመኪያ የሆነውን የደንብ ልብስ በመልበስ ማምለክ ፈጽሞ የተከለከለ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የዕምነት ተቋማቱም በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት በርካታ ሙያዎች ውስጥ ሠራዊቱን መርጠው በዚህ መልኩ ማሳየት የፈለጉበት ምክንያት ምን እንደሆነ መከላከያ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚከታተለው ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያ ፤ የተቋሙን ዩኒፎርም የለበሱ እና በፓትሮል መኪና ሆነው ሰው እየደበደቡ የተላለፈው ዘገባ እውነተኛነቱ ተረጋግጦ እርምጃ ይወሰዳል ሲሉ ገልጸዋል።

ሆን ብለው የተቋሙን አልባሳት እያስመሰሉ የሚለቀቁ ምስሎች እንዳሉ እንረዳለን ያሉት ኮሌኔል ጌትነት ፤ ይህን እና መሰል የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲኖር ህዝቡ እየተከላከለልን ውስጣችንን ደግሞ ራሳችን እያረምን እንሄዳለን ብለዋል።

ህዝቡ መሰል የመከላከያ ሠራዊትን ክብር እና መልካም ስም ለማጉደፍ የሚደረጉ ጥረቶችን ሲመለከት ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል ፡፡

(ኤፍ ቢ ሲ)


Leave a Reply