በአጣዬ ከተማ በነበረው የጸጥታ ችግር ወደ ሰላምና መረጋጋት በመመለሱ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ የኢፌዴሪ መከላከያ ጥሪ አስተላለፈ።በነበረው የጸጥታ ችግር በሰውና ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግም ተገልጿል።የኢፌዴሪ መከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአጣዬ ከተማ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ወደ ሰላምና መረጋጋት ተመልሷል።የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት በትብብር ባከናወኑት የፀጥታ ማስከበር ስራ በአሁኑ ወቅት አካባቢው ወደ ሰላምና መረጋጋት መምጣቱን ተናግረዋል።

በመሆኑም በነበረው የጸጥታ ችግር የተፈናቀሉ ወገኖች ወደየቀዬአቸው እንዲመለሱ ጥሪ አስተላልፈዋል።ወደ ቀዬአቸው ለሚመለሱ ሁሉ ሰራዊቱ አስፈላጊውን ሁሉ ጥበቃና ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።በአሁኑ ወቅት በርካቶች ወደ ቀዬአቸው እየተመለሱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት በመፈጠሩ ቀሪዎችም እንዲመለሱ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በጸጥታ ችግሩ ለተጎዱ ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ ሲሆን ተቋርጦ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎትም መጀመሩን ገልጸዋል።በአካባቢው የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ሕዝቡን በማወያያት እያረጋጋ እና ሰላም የማስከበር ስራ በማከናወን ላይ መሆኑን ኮሎኔል ጌትነት ተናግረዋል።አጣዬ ከተማ ወደ ሰላምና መረጋጋት ብትመለስም አሁንም በዜጎች ላይ የስነ ልቦና ጫናና ስጋት ለመፍጠር የሚነዙ መሰረተ ቢስ አሉባልታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

“የጠላት ሃይሎች ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ፍላጎት ቢኖራቸውም አይሳካላቸውም” ብለዋል።በአጣዬ ከተማ በሰውና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት አሳዛኝ እንደሆነ ገልጸው፤ በሰውና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።በአጣዬ ከተማ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞኖች በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎችና አምስት ከተሞች ኮማንድ ፖስት መቋቋሙ የሚታወስ ነው።


መከላከያ ሚኒስቴር ከአጣዬ እና ከከሚሴ አካባቢ ለተፈናቀሉ ወገኖች የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአጣዬ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከሚሴ አካባቢ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው እና ለተፈናቀሉ የኅብረተስብ ክፍሎች የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። የገንዘብ ድጋፉን የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቀነአ ያደታ ለአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ አስረክበዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ በገንዘብ ርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሀገርን ከወራሪ ኃይል ከመጠበቅ ባሻገር ሀገር ውስጥ ሰው ሠራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ ማኅባራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከብሔር እና ሃይማኖት ልዩነት የፀዳ አገልግሎትን እየሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል። ችግሮቹን ለመፍታት እየጣረ ያለውን ኃይል ለመደገፍ ሁሉም ዜጋ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣም ጥሪ አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው፣ በአሁኑ ሰዓት በክልሉ 565 ሺህ ስደተኞች እንደሚገኙ ተናግረዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ችግሮች ሲፈጠሩ ፈጥኖ የሚደርስ መሆኑን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ሕዝቡም ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም የአንዱ መጎዳት የኔም መጎዳት ነው ብሎ መከላከል እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል። የክልል መንግሥታትም ሆኑ ተቋማት የመከላከያ ሠራዊትን አርአያ በመከተል የተፈናቀሉትን ለማቋቋም መሥራት እና ሀገርን ከመፍረስ አደጋ መታደግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል። ሁለት ሚሊዮን ብሩ ለተጠቀሱት አካባቢዎች እንደሚከፋፈል ነው የተገለጸው።

በሣራ ሳህለሥላሴ – (ዋልታ)


    Leave a Reply