ግንቦት 21 ቀን 2013 – ላብ ደምን ያድናል!! ከስፓርት መልስ የሚከወኑ ሥራዎች አሉ። በርግጥ በወታደራዊ ካምኘና በምሽግ ላይ ሠራዊት የሚወስኑት ሁኔታዎች አሉ። የመጀመሪያው ፊሽካ ሲነፋ አልጋ ጥፎ ወደ መፀዳጃ ቤት። መፀዳጃ ቤትም እንደሰው በየቀኑ ንፅህናውን መጠበቅ ባህል ነው።

የመቶው ስፖርት ከዛ ቀጣዩ ቁርስ ነው።ቀስ ብሎ ከረፈደ በኋላ መብላት የለመደ ፤ በተፈጥሮው ቶሎ ቶሎ መመገብ የማይችል ሰው በአዲስነቱ ይፈተናል። ባለታሪኩም በዚህ ለተወሰኑ ጊዜያት መፈተኑ አልቀረም። ግን ይለመዳል እና ለምዶ ባህሉ እንዳደረገው በኩራት ይናገራል።ውትድርና ችግርን በመቋቋም ፤ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም ፤ ከሲቭል ፍፁም የተለየ ማንነት የሚገነባበት ነው።

ቁርስም የተወሰነ ሠዓት ሲሆን ከዚያስ ? ካልን የቁጥጥር ሥርዓት ተከናውኖ ወደ ቀጣዩ ሥራ ከመሠማራት በፊት ሥራ አለ።ፂም ማስተካከል ለዕለቱ ሥራ አስፈላጊ የሆኑ ትጥቆችን ማማሟላትና ማስተካከል ግድ ይላል።የፂምና ፀጉር አቆራረጥ ምንም ያህል ሥራ በዛ ተብሎ ምህረት አያሰጡም። እንደ ሌሎች የዲሲኘሊን ጥፋቶች ሁሉ ያስቀጣሉ። ሽርፍራፊ ሰንከንድ አይባክንም። የተተከሉ ችግኞችም ወታደሩ ከመብላቱ በፊት የቁርስ ውሃ መጠጣት አለባቸው።ፎሌን ተብሎ የሚጠራው ቁጥጥር እራሱን የቻለ ሥርዓት አለው።

አሰላለፉ ሳይንሳዊና ምክንያታዊ ነው።ሪፓርት ተቀባዩ “መልስ ለተረኛ ሃምሳ አለቃ ( ማዕረጉ እንደ ተቀባዩ ማዕረግ ይወሰናል) በሰልፍ ቀሪ በሽተኛ ይላል።” ዛሬ በአንዳንድ ክፍሎች የሚታየው መልስ ቀሪ በሽተኛ በሠልፍ የሚለው ስህተትና ማስተካከል ያለበት መሆኑን ተራኪው በአፅንኦት ይመክራል ።

ምክንያቱ ደግሞ የፎሌን አላማ ለሥራ ዝግጁ የሆነን ሐይል መለየት እንጂ በሽተኛ መቁጠር ስላልሆነ የሚል ነው።ወደ ቀጣዩ የስልጠና ወረዳ የሚደረገው ጉዞ በሥርዓትና በቅደም ተከተል ነው። በሠልፍ በአግባቡ ተጉዞ ከቀጣዩ ሥፍራ መድረስ አንዱ የሥልጠና መሥፈርት ነው። በስልጠና ወቅት አንድም የሥልጠና አካል ያልሆነ ድርጊት የለም።የስልጠና ወረዳ ደርሶ ዘሎ ወደ ጅምናዚያም ፣ ሰልፍ ወይም ተኩስ መግባት የለም።እንደገና ቁጥጥር አሁንም የማሟቂያ ስፓርት አለ።ተኩስ ሲባል የተለያዩ ደረጃዎች አሉት።

ጅምናዚያም- ጅምናቲክም በተመሣሣይ በውስጣቸው በርካታ ነገሮች ይይዛሉ።ከዚህ በኋላ ያለው በየተመደቡበት ወረዳ ልምምድ ማድረግ ነው። በልምምድ ወረዳ ቁጭ ማለት ፈፅሞ አይፈቀድም። ሥራ በተራ የሚከናወን ከሆነም አካልና አእምሮ የሚያጠናክሩ ፣ ለቀጣዩ ተግባር ዝግጅት የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች አሉ።በስልጠና ወቅት ይሄንን ወረዳ ጨርሻለሁ ብሎ ተነስቶ ወደ ሚቀጥለው መሻገር የተከለከለ ነው።

የራሱ ሠዓት እና ፊሽካ አለ።በመቀያየር ወቅት ዘና ብሎ በግል በተናጠል መጓዝ ነውር ነው።በወል በሩጫ በሞራል ይሆን ዘንድ ግድ ይላል።በስልጠና ወቅት የሣምንታዊ ፣ የወራት እቅድና ግብ ብቻ ሳይሆን የቀን ግብ አለ። የቀን ግቡ ላይ ያልደረሰ ከሌላው የተለየ ሥራ ይጠብቀዋል። በየትኛው ሠዓት ሊባል ይችላል ግን ደግሞ ከግቡ እስኪደርስ በጎዶቹና አሰልጣኞቹ ተደግፎ ይሰራል።ተራኪው በዚህ ሂደት ካለፉት ውስጥ ይጠቀሳል።

በስልጠና ወቅት እረፍት አለ ከተባለ ለሽንት የሚሰጡ ጥቂት ደቂቃዎች ናቸው። በሠዓት መስፈርት የግለሰብ ብቻ ሣይሆን ለክፍሎች ውድድርም ይጠቅማል።ከስልጠና ወረዳ ወደ መኖሪያ ሠፈር የሚደረገው የመልስ ጉዞ እንደ ቦታው አመቺነት ሁለት መልክ አለው።በሞራል እየጨፈሩ እና በሠልፍ ሥርዓት ይዞ በመጓዝ ሊሆን ይችላል።ለምሳ ሁልጊዜ ወደ ሠፈር መመለስ የለም።

እዚያው መመገብ እንደ አሰፈላጊነቱና የልምምዱ ደረጃ መመገብ የሚባል ነገርም ላይኖር ይችላል።ወደ ሠፈር መልስ በሠልፍ አሊያም በሞራል እያጨፈሩ ሊሆን ይችላል ብለናል። በሞራል በሚሆንበት ወቅት ኢትዮጵያ ህብሯ ደምቆ ይታያል።ያ ሆ በለው ፣ ያ ሎላ ያ ሎላ የቦ ፤ ሃሃሃ ጉማ ወዘተ ሲሰሙ እግረ መንገድ የሀገራችንን መልክ ያሳያል።

ሀገር ብለው ከቤታቸው የወጡ ፣ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ፣ ባህል ቋንቋ ፤ የመጡትን አንድነት በፍፁም ዜጋዊ እኩልነት የእርስ በርስ ፍቅር በልባቸው ላይ ያትማል። በምሳ አመጋገብም የራሱ አካሄድ አለው። ነገ መጀመሪያ የተመገብ የመቶ በሚቀጥለው ተራውን ለሌላው ይለቃል።የተገኘውን ወይስ ሚንስ ቤት ያፈራው የሚባል ኘሮግራምም የለም።

የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በሚፈቅደውና በሥራ ለሚደክመው አካል አስፈላጊ በሆነ መልኩ ኘሮግራም አለ።የአንድ ሻለቃ አባላት በሣምንቱ የሚመገቡት ምግብ ፤ የሚወስዱት ስልጠና ፤ የሚጠብቁት ውጤት ፤ ለእያንዳንዱ ሥራ የሚመደብላቸው ሠዓት ተመሣሣይ ነው። ለአንዲት ሀገር ብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማ ክብር ፤ በአንድ ልብ በጋራ የመቆም አስፈላጊት የሚያስዝ ቤት ነው ውትድርና ፡፡ ምሳም የራሱ ሠዓት አለው።

ከዚያ ማለፍ አይቻልም። ባለች ጥቂት ጊዜም የሚሠሩ ሥራዎች አሉ።ቀጥሎ ያለው ወደ ልምምድ ወረዳ ተመልሶ እንደ ኘሮግራሙ ልምምዱን መቀጠል ነው።ከስልጠና መልስ እራት ከተበላ በኋላ ዘሎ ወደ መኝታ መሄድ የለም።ቀኑን ሙሉ የተሠራው ይገመገማል።ጉድለት ካለ ይታረማል።ከዚያስ ? ከዚያ ምን ቀረ? ካልን ምን ተነካ መልስ ይሆናል።በውትድርና ህይወት ቀን ለሰው ፣ ለሊት ለአውሬ የሚባል ነገር የለም።

ውጊያ በቀንም ሆነ በለሊት ፣ በቆላም ሆነ በደጋ ፣ በበጋም ሆነ በክረምት ፤ በሜዳም ሆነ ተራራ ወዘተ አለና በተለያዩ ወቅቶችና የአየር ፀባያት ልምምድ ይደረጋል። የለሊት ልምምድ ብቻ ሳይሆን እንደ ምሽግ ሁሉ የማያቋርጥ ጥበቃም አለ።ከዚህ ተነስቼ ሰባት ሃያ አራት በውትድርና ቤት ምን ያህል ሰፊ ጊዜ እንደሆነ ሳስብ ይገርመኛል ይላል ተራኪው። ማዕረግ ለብሶ አምሮ ከነግርማ ሞገሱ ሲታይ ፣ ትጥቁን ታጥቆ ሲንቀሳቀስ ቀለል አድርጎ የሚያዩ ሠዎች ሲገጥሙኝ እገረማለሁ ብሏል።

በነገራችን የሳቸው ገጠመኝ በእግረኛ ክፍሎች ሲሆን በአየር ሐይል ፣ ባህር ሐይልና ልዩ ዘመቻዎችም ተመሳሳይ ስርዓትና የማይዛነፍ ወታራዊ ባህል አለ። ቴክኒካዊ የአሰለጣጠን ጥበባት እንዳሉ ሆነው።ይሄ ከሠራዊቱ ህይወት ተቀንጭቦ የአንድ ስልጠናን ብቻ ላይ አተኩሮ የቀረበ ነው። ባለታሪካችን ገራሚ የግዳጅና የማህበራዊ መስተጋብር ትዝታዎችም አሉት ። በተከታታይ አጓጊ ትውስታውን እናስነብባችኋለን።

ሣምንታትና ወራት ቀርቶ 24 ሠዓታት በውትድርና ህይወት አጠቃቀምና ውጤት የማህበረሰቡም ቢሆን ሀገርን በአጭር ጊዜ ወደ አደጉት ሀገራት ተርታ የሚያስፈነጥር አይሆንም ትላላችሁ? “24 ሠዓታት በውትድርና ህይወት ውስጥ” ክፍል ሶስትን ሰኞ እናስነብባችኋለን ፡፡

ሻለቃ ፈይሳ ናኔቻ – መከላከያ ፌስ ቡክ

ፎቶግራፍ ብዙአየሁ ተሸመ


Leave a Reply

Previous post 24 ሠዓታት በውትድርና ህይወት – ምስክርነት ክፍል አንድ
Next post የኢትዮጵያ “ትንሣኤዋን እውነተኛ ልጆቿ እንጂ ጠላቶቿ ወዲያው አያዩትም” ተመስገን ትሩነህ
%d bloggers like this: