ስልጠና የታሪኩ ባለቤት በውትድርና ህይወት አሁን ያለበት ደረጃ ለመድረስ ከጓድ ጀምሮ ባሉ አጀረጃጀቶች ውስጥ አልፏል። ሃያ ዓመታትን ወደኋላ እየተመለሰ በሐሳብ ሲቃኝ ብዙ ነገሮች ያስደምሙታል።ወታደር ሰው ነውና ሐዘንና ደስታ ፣ ፍቅርና ጥላቻ ፣ ልፋትና ዕድገት ፣ ተስፋና ምኞት ሊኖረው እንደሚችል ምንም ጥርጥር ባይኖረውም ተራኪው ከረጅም ዘመን የአገልግሎት ልምዱ ተነስቶ ሊያወጋን የፈለገው ለየት የሚያደርገውን ውሎና አዳሩን ነው።

ህዝባችን በጋ ወቅት ሠርግ ፣ ማህበር እቁብ ፣ ዕድር የመሳሰሉ የግንኙነት አጋጣሚዎች ሁሉት ዓላማ አላቸው ። ማህበራዊ መስተጋብር መፍጠር እና እግረ መንገዳቸውንም መዝናኛ ናቸው።ከዚህ ማህበረሰብ የወጣው የመከላከያ ሠራዊት ህይወትስ ካልን በብዙ መልኩ የተለየ ይሆናል። በሣምንት ሰባት ቀናት ፣ በቀን ሃያ አራት ሠዓታት ሌላ የአኗኗር ባህል አለው።

በተለይ ሀገር ላይ የተቃጣ ግዳጅ ሲኖር በማለት አፅንኦት ይሰጠዋል – ከመሠረታዊ ወታደር ተነስቶ ሁሉንም እርከኖች አልፎ በሻለቃ ማዕረግ ተቋሙንና ከምንም በላይ የሚወዳት ሀገሩን በማገልገል ላይ የሚገኘው መኮንን።ታረኩን የሚያካፍለን አባል ወደ ኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የተቀላቀለው በ1991 ዓ.ም ነው።

ወደ ተመደበበት ክፍል ሲደርስ የገጠመው ከሀገር ቤትም ሆነ ከማሰልጠኛው የባሰ እረፍት አልባ ህይወት ነው።እሱና ጓደኞቹ አቀባበል ከተደረገላቸውና የተመደቡበትን ክፍል ታሪክ በተመለከተ ግንዛቤ ካገኙ በኋላ የገቡት ወደ ማመጣጠን ስልጠና ነበር።አንድ ወታደር የሚጠበቅበትን የትጥቅ ሎድ ይዞ ወደ ግዳጅ ከመሠማራቱ በፊት የማመጣጠን ስልጠና ይወስዳል።ድካም አለ።

ለምን ያለመጠን እንደክማለን? ላባችን ለምን እንደ ጎርፍ ይፈሳል? የበዛ እረፍት የተጠላበት ምክንያት ምንድነው? የዚህ ሁሉ ድካም ለምን ዓላማ ነው? የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙ ዘንድ ከነባሩ ጋር የአስተሳሰብ መመጣጠን ያስፈልጋል። በስተመጨረሻ ተራኪያችን ያገኘው አጭርና አሳማኝ መልስ “ላብ ደምን ያድናል” የሚል ታላቅ እውነት ነው ።

“ጦርነት እንዳይመጣብህ ከፈለክ ሁሌም ለጦርነት የተዘጋጀ ሁን” የተባለው አለምክንያት አይደለም።ጦርነት በህይወት ሁሉ ከሚያጋጥሙ ፈተናዎች ከባዱ ነው ማለት ይቻላል።ሞትን ፊት ለፊት መጋፈጥ ከእናት ልጅ በላይ የሚወዱትን በድንገት የማጣት ክፉ አጋጣሚዎች አሉትና ! በመሆኑም ድል ለማድረግ ከጠላት በአሸናፊነት ስነልቦና ፣ በአካላዊ ብቃት ፣ የተጠቁትን መሣሪያ የመጠቀም ብቃት መያዝ ያስፈልጋል። ማመጣጠን የመሠረታዊ ውትድርና ዕውቀትን ወደላቀ ብቃት በራስ መተማመንና የአሸናፊነት ስሜት ይቀይራል ሲሉ ከራሳቸው ተሞክሮ በመነሳት ነው።

ስፓርት በወታደር ቤት አካል ማጎልበቻ ፣ የጤንነት መጠበቂያ ብቻ ሳይሆን ባህል ነው። ከዕሁድ በስተቀር የጠዋት ስፓርት አለ። የመጀመሪያ ወቅት ከሲቪል ህይወት ለመጣ ሰው ከጣፋጭ የጠዋት እንቅልፍ ተነስቶ ከማሟቂያ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ እንቅስቃሴዎች መሥራት ይከብዳል። ሲቆይ ግን በመቀስቀሻ ሠዓት ቀስቃሽ እንኳን ባይኖር የሚተኛ የለም። እሁድንም እረፍት ነው ብሎ ማሰብ ይከብዳል። የግልና የአከባቢ ንፅህና ለሠኞ የጎደሉ ግብአቶችን ማሟያ ነው።

የስፓርት ጥሩ ነገር ሲጀምሩት አሰልቺና አድካሚ እየቆየ ሲሄድ ተወዳጅና ተናፋቂ ሱስ መሆኑ ነው። የወታደር ስፓርት ከአካላዊ እንቅስቃሴ ውጭ አእምሮን ገንቢ መልዕክቶች የሚተላለፉበት ነው።አሰሪው – “አላችሁ ሆይ?” ይላል…አባላቱ – “አለን ፡፡ አለን ፡፡ አለን ፡፡” ሲሉ በህብረትና ከፍ ባለሞራል ይመልሳሉ።”አንተ ማን ነህ ?” ሲል ያክላል”የጀግና ልጅ ጀግና ፣ የአንበሳ ልጅ አንበሳ ፣ ተኩሶ የማይስት ፣ አንድ ጥይት ለአንድ ጠላት” ሲሉ በህብረት ይመልሳሉ።”እጅ ወደፊት” ሲባል ምላሹ እጅ ወደ ፊት በመዘርጋት “ኢትዮጵያ” የሚል ይሆናል የጋራ መልሱ።”ወደኋላ” ሲባል ደግሞ “ጠላት” ይባላል።

“አንድ… ሁለት… ሦስት…” ሲባል በከፍተኛው ሶስቴ ከተጨበጨበ ቦኃላ “ኢትዮጵያ ” የሚል አስደንጋጭ ምላሽ ይሰጣል። የሞራል መገንባያ ጥያቄዎችና ምላሻቸው በርካታ ናቸው።በየስልጠና መሀሉ ኢትዮጵያ በጀግንነት ተዋግተው አዋግተው ያቆዩ ስመ-ጥር ጀግኖች ይነሳሉ። የከፍሎች ስያሜም በዚች ጥቁር አፈር ብቃዮች ፣ የነፃነቷ ምክንያቶች ናቸው። ቴዎድሮስ ፣ ባልቻ ፣ በላይ ፣ አሉላ ፣ አብዲሣ ፣ ዑመር ሰመትር ወዘተ ይሰኛል።ኢትዮጵያ ወደፊት ፣ ጠላቷ ወደኃላ የሚል ከልብ የመነጨ ምኞት ፤ የአበው ታሪክ ወራሽ ፤ የጀግና ህዝብና ሀገር ታሪክ ወራሽነት በውትድርና ሙያ የጀግንነትና ተኳሽነት ለድርድር ያለማቅረብና አስፈላጊነት በአእምሮ ይቀረፃል ከልብ ይሰርፃል።

ከስፓርት መልስ በፈለጉት አቅጣጫ መበተን ፤ ደስ ያለን ነገር መከወን የለም። ጥቂት ደቂቃዎች ተወስደው የአሠራሩ ሂደት ይገመገማል። መብዛት ያለበት ካነሳ ፤ ማነስ የነበረበት ከበዛ ውይይት ይደረጋል። የበረታው እንዲቀጥል የደከመው እንዲበረታ በግልፅ ተነግሮት በሚቀጥለው ይታረማል። በውትድርና ህይወት የግል ጥረት አስፈላጊ ቢሆንም ተፈላጊው የቡድን ውጤት ነው።”24 ሠዓታት በውትድርና ህይወት ውስጥ” ክፍል ሁለትን ነገ እናስነብባችኋለን ፡፡ ሻለቃ ፈይሳ ናኔቻ

ፎቶግራፍ ብዙአየሁ ተሸመ – ከመከላከያ ፌስ ቡክ


Leave a Reply