ምርጫውና የግድቡ ሙሊት- “ ሟርት አይደለም በህልም የታየ ሆረር ትዕይንትም አይደለም። ወይም ባዶ ቅዠት”

ምናልባት መንግስትን ላንደግፍ እንችል ይሆናል። በሚፈጸመው፣ በሚሆነው፣ በሚደረገው፣ እጅግ ተቆጥተን፣ በመንግስትም ይሁን በገዢው ፓርቲ ላይ ምርር ያለ ተቃውሞ ሊኖረንም ይችላል። በየቦታው ባለው ግድያና መፈናቀል ምክንያት የመንግስትን ውድቀት እንደብቸኛ መፍትሄ አድርገን ያመንን፣ አምነንም ትግል የጀመርን ልንኖር እንደምንችል ጥርጣሬ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም። ምንም ይሁን ምንም ግን በምርጫው መካሄድና በግድቡ ሙሌት ላይ ልዩነት ሊኖረን ግን አይገባም።

ሟርት አይደለም። በህልም የታየ ሆረር ትዕይንትም አይደለም። ወይም ባዶ ቅዠት። ካይሮ አድብታ፣ ካርቱም በሆዷ ቋጥራ፣ ሁለቱም ከሌሎች መድረኩ ላይ በፊት ለፊት ከማይታዩ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በህብረት ተነስተው የወረወሩብን የጥፋት ቀስት እንጂ። ቀስቱ ኢትዮጵያ ላይ አነጣጥሮ ተወውሯል። መንግስት ላይ የተወረወረ መስሎን “የታባቱ፣ ይበለው” እያልን ከሆነ ነገ ሀገር አልባ ሆነን እንደሶርያውያውን በየሀገሩ ስንከራተት ያን ጊዜ ይገለጥልናል። ይህ የተነሳው ሃይል መዳረሻው የኢትዮጵያ ጥፋት ነው። ኢትዮጵያ የምትባልን ሀገር ከዓለም ካርታ ላይ መፋቅ ነው። ህወሀት መቃብር ፈንቅሎ እንዲወጣና ነፍስ ዘርቶ ቤተመንግስት እንዲጋራ የሚደረገው ርብርብ ሌላ ስም ይሰጠው እንጂ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በተዘጋጀ እቅድ ውስጥ የተቀመጠ ቁልፍና ወሳኝ ተግባር ነው። በየቦታው የሚታየው ግድያና መፈናቀል የዚሁ እቅድ ማስፈጸሚያ እንጂ መንግስት ላይ ያኮረፉ ሃይሎች የሚያደርጉት የትግል ስልት አይደለም።

ስለኢትዮጵያ ሲባል የሁለቱ ክስተቶች ስኬት ወሳኝ ነገር ነው። ስለ ሀገራችን መጻዒ እድል ለምንገበገብ፣ የኢትዮጵያችን ህልውና በማያወላውል ጽኑ መሰረት ላይ ሆኖ እንዲቀጥል ምርጫውም መደረግ፣ ግድቡም ሁለተኛው ዙር ሙሌት መከናወን አለበት።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከዚህም ከዚያም፣ ከውስጥና ከውጪ፣ በአንድ ድምጽ የተነሱት ጠላቶች ሁለቱን ክስተቶች በማጨናገፍ ሴጣናዊ ህልማቸውን ለማሳካት ከምንጊዜውም በላይ በመረባረብ ላይ ናቸው። ከዋሽንግተን ዲሲ፣ ካይሮ፣ ካርቱም፣ ትግራይ በረሀ እስከአዲስ አበባ የተዘረጋው “የኢትዮጵያን እናፍርስ” ሃይል ምርጫው እንዳይካሄድና በምትኩ የመንግስት እጅ ተጠምዝዞ እነ ኦነግ ሸኔና መቃብር ውስጥ የሚያቃስተው የህወሀት ትርፍራፊ ሃይል በድርድር ስም ቤተመንግስት ገብተው መንግስትን ስልጣን እንዲጋሩ በስፋት እየሰራበት ነው። በየቦታው የሚታየው ግድያና መፈናቀል የዚሁ ስውር ተልዕኮ ዋና ተግባር ነው። ምርጫውን ማንም ያሸንፍ ማን፣ መካሄዱ ብቻውን የዚህን ሃይል መርዛማ ተልዕኮ ያከሽፈዋል፣ በምትኩ ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና ትቀጥላለች።

የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት እንዳይከናወን ማድረግ የዚህ ኢትዮጵያ ላይ የተነሳው የጥፋት ሃይል መሰረታዊ ዓላማው ነው። ለዚህም ግብጽና ካይሮ ሀብት ገንዘባቸውን በአያሌው መድበዋል። ቧጠውም፣ ገደል ገብተውም ቢሆን ሙሊቱ እንዳይፈጸም ለማድረግ ታጥቀው ተነስተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግን የቤተሰብ ጸብ ሳይቀር ሀገር የሚያቃውስ ብጥብጥ ሆኖ እንድንተራመስበት በግልጽ በአደባባይ የክተት ነጋሪት እየተጎሰመልን ነው። በፊት በጓዳና በጓሮ ሲይንሸኳሽኩ የነበረውን የኢትዮጵያን ማፈራረስ እቅዳቸውን በቴሌቪዥን መስኮት መጥተው እየነገሩን ነው።

የግብጽ ሚዲያዎች የሚያስተልፏቸው መልዕክቶች ቃናቸውን ቀይረዋል። አረቦች እስራዔልን እንደወረሩ ሁሉ ኢትዮጵያንም በጋራ መውረር አለባቸው የሚል አደገኛ መልዕክት ማሰራጨት ጀምረዋል። ሱዳን ትላንት የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልልን የይገባኛል ጥያቄ ለማንሳት ዳርዳር ያለችበትን መግለጫ አውጥታለች። ነገሩን ሌላ መልክ ለማስያዝ በግብጽና በሱዳን በኩል ሰፊ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ተከፍቷል። ይህን ሁሉ የሚያከሽፈው የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ነው። ኢትዮጵያ እንደእቅዷ ተፈጻሚ ካደረገች ፉከራው ሽለላው፣ ተልኮል ሴራው አፈር ድሜ ይበላል። ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና ትቀጥላለች።

አሜሪካንና አውሮፓ ጫናቸው በርትቷል። ምርጫው እንዳይደረግና በድርድር የሆነ መንግስት እንዲመሰረት እጅ ጥምዘዛውን ገፍተውበታል። ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ጊዜው አሁን ነው ብለው ለተነሱ የውጭና የውስጥ ጠላቶች ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እያደረጉ ነው። ሩሲያና ቻይና አፍሪካን ሊነጥቁን ነው የሚል ስጋት የሚንጣቸው ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ እንዳታመልጣቸውና በቁጥጥራቸው ስር እንድትሆን ለማድረግ በሚል የኢትዮጵያን ጠላቶች አጀንዳ ቅዱስ አድርገው ተቀብለውታል። በዚህና በዚያ በራሳችው ሀገራዊ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሯሯጡ ሀገራት ኢትዮጵያን የመስዋዕት በግ አድርገው ሊያርዷት ተዘጋጅተዋል። ለዚህም ሁነኛ አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል። ምርጫውን ማደናቀፍና የግድቡን ሙሊት ማስቆም ኢትዮጵያን ያንበረክካል፣ በሂደትም ያፈርሳታል ብለው አምነውበታል። አምነው ብቻ ቁጭ አላሉም። ባላቸው አቅም፣ በጉልበት በገንዘባቸው ሃይል ተጠቅመው ሊያስፈጽሙ እየተረባረቡ ነው።

እናም ኢትዮጵያን ያልክ ወገን ኩርፊያህን ለጊዜው ተወው። ቅሬታህን ለነገ አስቀምጠው። መንግስትና ሀገርን ለይ። አሁን የዘመተው ሃይል ጸቡ ከመንግስት ጋር እንዳይመስልህ። ከትግራይ በረሃ የሞት ሳል እያሳለ፣ ቤተመንግስትን ከመቃብር ውስጥ ሆኖ የሚመኘው ህወሓት ጉዳዩ ከዶ/ር አብይ ጋር ከመሰለህ ተሳስተሃል። በወለጋ ምድር የአማራውን ደም የሚያፈሰው፣ ህጻናትን አጋድሞ የሚያርደው ኦነግ ሸኔ፣ ብልጽግና ፓርቲን ገልብጦ ስልጣን ለመያዝ የሚያደርገው ትግል አድርገህ ከደመደምክም ነገሮች በጥልቀት አልገቡህም። ቤንሻንጉል ጉምዝ ላይ የሚታየው የሰው ልጅ መከራ በመንግስት ላይ ያኮረፉ ሃይሎች ኩርፊያቸውን ማሳያ፣ መንግስትን አስገድደው የሚፈልጉትን ለማስፈጸም የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መስሎ ከታየህ እውነት አንተ ደመ ነፍስ ውስጥ ነህና በአስቸኳይ ከዚያ ለመውጣት ሞክር። ይህ ሁሉ ነገር መቋጠሪያው አንድን ዓላማ ለማሳካት ነው። ኢትዮጵያን ለማፍረስ። በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ትናንሽ ደካማ መንግስታትን ለመፍጠር። ይኸው ነው።

ሟርት አይደለም። በህልም የታየ ሆረር ትዕይንትም አይደለም። ወይም ባዶ ቅዠት። ካይሮ አድብታ፣ ካርቱም በሆዷ ቋጥራ፣ ሁለቱም ከሌሎች መድረኩ ላይ በፊት ለፊት ከማይታዩ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በህብረት ተነስተው የወረወሩብን የጥፋት ቀስት እንጂ። ቀስቱ ኢትዮጵያ ላይ አነጣጥሮ ተወውሯል። መንግስት ላይ የተወረወረ መስሎን “የታባቱ፣ ይበለው” እያልን ከሆነ ነገ ሀገር አልባ ሆነን እንደሶርያውያውን በየሀገሩ ስንከራተት ያን ጊዜ ይገለጥልናል። ይህ የተነሳው ሃይል መዳረሻው የኢትዮጵያ ጥፋት ነው። ኢትዮጵያ የምትባልን ሀገር ከዓለም ካርታ ላይ መፋቅ ነው። ህወሀት መቃብር ፈንቅሎ እንዲወጣና ነፍስ ዘርቶ ቤተመንግስት እንዲጋራ የሚደረገው ርብርብ ሌላ ስም ይሰጠው እንጂ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በተዘጋጀ እቅድ ውስጥ የተቀመጠ ቁልፍና ወሳኝ ተግባር ነው። በየቦታው የሚታየው ግድያና መፈናቀል የዚሁ እቅድ ማስፈጸሚያ እንጂ መንግስት ላይ ያኮረፉ ሃይሎች የሚያደርጉት የትግል ስልት አይደለም።

እናም አንዱን ዓይንህን ከምርጫው ላይ ትከል። በነቂስ ወጥተህ አስተዳዳሪዎችህን ምረጥ። ምርጫው እንደከዚህ በፊቱ የዲሞክራሲ መቀልጂያ ድግስ አድርገህ ተስፋ እንዳትቆርጥበት። ይህ ምርጫ ከዲሞክራሲ መለማመጃነቱ ይልቅ የሀገር ህልውናን ማስቀጠያ ሁነኛ ክስተት አድርገህ ውሰደው። ጠላቶቻችን የመጡብን ይህንን በማጨናገፍና በሂደትም ለኢትዮጵያ መፈራረስ በተዘጋጀ የሽግግር መንግስት ላይ ድርድር እንዲካሄድ ነው። ይህ ነው ቁልፉ ጉዳይ። ሌላኛውን ዓይንህን ከግድቡ ሙሊት ሂደት ላይ አድርገው። እነግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያን ለማዳከም የዘረጉት ወጥመድ የሚገኘው እዚያ ቤንሻንጉል ጉምዝ ውስጥ ነው። ሁለተኛውን ዙር በእኛ ድክመትና በእነሱ ብርታት ካልተሞላ ልፍስፍስ፡ ደካማ፡ የማንም መጫወቺያ፡ የምትሆን ሀገር ታቅፈን ዘላለማችንን እያለቀስን፡ አንገታችንን ደፍተን እንኖራለን። ምርጫው በእጃችን ነው። ጊዜ የለንም። ዋጋ ከፍለን፡ ሀገራችንን ታድገን ነገን ቀና ብለን እንኖራለን፡ አልያም እጃችን ላይ ሀገራችን ፈርሳ ዘላለማዊ ውርደት እየተጎነጨን፡ በዓለም መድረክ ፊት አንገታችን ተሰብሮ ተበታትነን እንቀራለን።

ኢትዮጵያን ያልክ ተነስ። ከሀገርህ ጎን ቁም። ምርጫውን ተሳተፍ። ሌላው እንዲሳተፍ ቀስቅስ። በምርጫው ሀገርህን ታድናለህ። በምርጫው ለኢትዮጵያ የተዘጋጀውን የሞት ድግስ ታከሽፋለህ። ማንም ይመረጥ ማን በውጤቱ ኢትዮጵያ ማሸነፏ አይቀርም። የፈለከውን መንግስት ላይሆን ይችላል። ቤተመንግስት ላይገባልህም ይችላል። ኢትዮጵያ ግን ታሸንፋለች። የግድቡ ሙሊት እንዲከናወንም መንግስትን አግዝ። በምትችለው ደግፈው።ይህን የምታደርገው ስለኢትዮጵያ ብለህ ነው። ግድቡ ቢሞላ ኢትዮጵያ ታሸንፋለችና። ጉልበቷን ሊሰብሩ፡ ማጎንበሷን ለናፈቁ ሃይሎች እድል አትስጣቸው። ዛሬ በምታደርገው ነገር ነገ ሀገርህ ትታደጋታለህ። ነገ ከፍሬዋ ትበላለህ። ግድየለም። ዛሬን ዋጋ ክፈል። ኢትዮጵያ የምትድነው በቆራጥ ልጆቿ እንጂ በማንም አይደለም።

መልካም በዓል! Mesay Mekonnen

DONATE US – ቢረዱን አስፍተን ለመስራት አቅም ይፈጥሩልናል

About topzena1 2659 Articles
A journalist

Be the first to comment

Leave a Reply