የባህር ኃይል አርማ፣ የትከሻ ምልክትና የደንብ ልብስ ይፋ ተደረገ

የባህር ኃይል አርማ፣ የትከሻ ምልክትና የደንብ ልብስ ዛሬ ቢሾፍቱ በሚገኘው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ይፋ ተደርጓል።

በሥነሥርዓቱ ላይ የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ፣ የባህር ኃይል ዋና አዛዥ አድሚራል ክንዱ ገዙና ጥሪ የተደረገላቸው የውጭ አገራት አታሼዎችና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ተገኝተዋል።

አርማው ቀይ፣ ነጭና ቢጫ ቀለማትን ሲይዝ፣ ቀዩ መስዋዕትነትንና ዝግጁነትን፣ ነጩ ሰላም፣ እውቀት፣ ላብና የመለያ ክብርን እንዲሁም ቢጫው ለሀገርና ለህዝቦች መጪው ጊዜ የብሩህ ተስፋ ዘመን መሆኑን የሚያመላክት መሆኑ ተገልጿል።

በአርማው ላይ የባህር ኃይል ዓለምአቀፍ ምልክት የሆነው መልህቅ እና በቀላሉ የማይበገር የባህር ኃይል በተሰማራበት ቀጠና ላይ የሚሰጠውን ግዳጅ በብቃትና በጥንካሬ እንደሚወጣ የሚያሳየው የወይራ ዘለላ ተቀምጦበታል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በአርማው ላይ ያለው ሰማያዊ መደብ ባህር ኃይሉ ተልዕኮውን የሚወጣው በባህርና በውቅያኖስ ላይ መሆኑን ሲያሳይ ሰንደቅ አላማው ደግሞ ለሀገርና ለሰንደቅ አላማ ዘብ መቆምን ያሳያል ተብሏል።

ይፋ የተደረገው የባህር ኃይል አርማ በጠቅላይ መምሪያው፣ በመርከቦችና በተለያዩ የህትመት ውጤቶች ላይ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተገልጿል።

አብራችሁን ስለሆናችሁ ደስተኞች ነን! Via walta

Leave a Reply