አስተዳደሩ ለጀግኖች አርበኞች ነፃ ህክምና እንዲሰጥ ወሰነ

አርበኞች ነፃ ህክምና እንዲሰጥ ወሰነ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጀግኖች አርበኞች ነፃ ህክምና እንዲሰጥ ወስኗል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጀግኖች አርበኞች በከተማዋ አስተዳደር ስር ባሉ የጤና ተቋማት በሙሉ ነፃ ህክምና እንዲሰጥ መወሰኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።

የከተማ አስተዳደሩ 80ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ቀን ምክንያት በማድረግ ከነፃ ህክምና አገልግሎቱም በተጨማሪ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የጠየቀው መሬት እንዲሰጠው መወሰኑንም ምክትል ከንቲባዋ ማስታወቃቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

በበአሉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጣልያን ኢትዮጵያን ዳግም ለመውረር ጥረት ባደረገበት ጊዜ ጀግኖች አባቶች እና እናቶች አይበገሬነታቸውን ያስመሰከሩበትን ድል የሚታሰብበት በዓል ነው ብለዋል።

ጣልያን ኢትዮጵያውያንን በዘር፣ በኃይማኖት እና በአካባቢ የመከፋፈል ሴራ ተጠቅሞ ኃይላችንን በማሳነስ ድል ለማድረግ ሙከራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፤ ጀግኖች አርበኞች የጠላትን ሴራ ቀድመው በመረዳታቸው ውጥኑ ሊከሽፍ እንደቻለ ወይዘሮ አዳነች አስታውሰዋል።

ጀግኖች አርበኞች ባደረጉት ማስተዋል የተመላበት ትግል ትውልዱ አንገቱን ቀና አድርጎ የሚሄድባት፣ የሚኮራባት አገር እንዲኖረው አድርገዋልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያን ከጀግኖች አርበኞች መማር ያለባቸው የጠላትን የመከፋፈል ሴራ በማስተዋል እና አንድነትን ማጠናከር መሆኑንም ገልጸዋል።

በስነ-ስርአቱ ላይ ወጣቶች ፉከራ እና ሽለላ ያቀረቡ ሲሆን የማርችባንድ ትርኢትም ቀርቧል።

FBC

Leave a Reply

%d bloggers like this: