ድሮ ድሮ በደጋጎቹ ዘመን “ጮሌዎቹ” በግ ከአርሶ አደሩ በስሙኒ ገዝተው ቆዳውን መልሰው በስሙኒ በመሸጥ ስጋውን በነጻ “እንክት” አድረው ይበሉ ነበር ይባላል። ታዲያ የስጋን ያህል ዋጋ ያወጣ የነበረ የቆዳ ዋጋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዋጋ መውደቁን (መርከሱን) ተከትሎ በተለይ በበዓላት ሰሞን በየቦታው ተጥሎ አካባቢን ሲበክል ይስተዋላል።

“በአንድ ወቅት ከቡና ቀጥሎ ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስገኝ የነበረው የቆዳው ዘርፍ ዛሬ ላይ የቆዳ ዋጋ ረክሶ ቆዳ በየቆሻሻ መጣያው ለመጣል ያደረሰው ምክንያቱ ምንድነው?” ሲሉ አንባቢዎቻችን በኢሜል አድራሻችን የሚመለከተውን አካል ጠይቀን ምላሽ እንድንሰጣቸው ጠይቀውናል።

በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው በኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ሰርጀቦ እንደገለጹት፤ የቆዳ ገበያ በተፈጥሮው በዓለም ገበያ የሚመራ ነው። የዓለም ገበያ ከፍ ሲል በአገር ውስጥ ያለው የቆዳ ዋጋም በዛው ልክ ከፍ ይላል። በአንጻሩ የዓለም ገበያ ዋጋው በጣም ዝቅ በሚልበት ጊዜ ደግሞ የአገር ውስጥ የቆዳ ዋጋም በዛው ልክ ዝቅ ይላል። በተለይ ከአሜሪካና ቻይና የንግድ ጦርነት ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ ቀውስ ተከስቷል። የሁለቱ ኃያላን አገራት የንግድ ጦርነት ዳፋው ለሁሉም የዓለም አገራት በመትረፉ ኢትዮጵያም አንዷ ገፈጥ ቀማሽ ናት።

የኢትዮጵያ ዋና ቆዳ ገዥ ወይም ተረካቢ ደግሞ ቻይና ናት። ቻይና ቆዳ ከተለያዩ አገራት ገዝታ ምርቷን በብዛት አምርታ የምታቀርበው ለአሜሪካ ገበያ ነው። ነገር ግን ሁለቱ ኃያላን አገራት ወደ ለየለት የንግድ ጦርነት ገብተው በመቃቃራቸው ምክንያት አሜሪካ የቻይናን ምርት እየተረከበች አይደለም። ይህን ተከትሎ ቻይና በምትፈልገው ልክ ምርቷን አምርታ ለውጭ ገበያ እያቀረበች ስላልሆነ የኢትዮጵያ ቆዳ በቻይና ገበያ የሚፈለገውን ያህል ቀርቦ እየተሸጠና የሚፈለገውን ዋጋም እያወጣ አይደለም። በተመሳሳይ በሁለቱ ኃያላን አገሮች የንግድ ጦርነት ሳቢያ በአውሮፓ ብሎም በሌሎች አህጉሮችም የቆዳ ዋጋ ወድቋል። በጥቅሉ በአለም አቀፍ ደረጃ የቆዳ ዋጋ በመውረዱ የአገር ውስጥ የቆዳ ዋጋም በተመሳሳይ ዋጋው ሊረክስ ችሏል።

በሌላ በኩል በአሜሪካና ቻይና የንግድ ጦርነት ምክንያት ዓለም ከገባችበት ቀውስ በደንብ ሳታገግም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ላይ መከሰቱን ተከትሎ የዓለም ገበያ መቀዛቀዙን ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ በወረርሽኙ ሳቢያ የዓለም ገበያ መቀዛቀዙን ተከትሎ ኢንዱስትሪዎች ያመረቱትን ምርት እየሸጡ አይደለም። ስለዚህ ኢንዱስትሪዎች የሚያመርቱትን የቆዳ ምርቶች መሸጥ ካልቻሉ ጥሬ ቆዳና ሌጦ የመግዛት ፍላጎታቸው ይቀንሳል። በዚህም ኢንዱስትሪዎች ያመረቱትን ምርት እየሸጡ ስላልሆነ ቆዳ የመግዛት ፍላጎታቸው በመውረዱ የቆዳ ዋጋ ሊረክስ መቻሉን ይናገራሉ።

እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የቆዳ ጥራት መጓደል ለቆዳ መውደቅ አንዱ ምክንያት ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ እንስሳቱ በቁም እያሉ እንዲሁም በእርድ ወቅትና ከእርድ በኋላ በቆዳ ላይ የሚከሰቱ የጥራት ችግሮች ለአገሪቱ ቆዳና ሌጦ ጥራት መጓደል ምክንያቶች ናቸው። በእነዚህ ምክንያቶች የአገር ውስጥ ቆዳ ዋጋ ሊወድቅ ችሏል። ስለዚህ የቆዳ ዋጋ መውደቅ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኝት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ እንዳታገኝ ከማድረጉ ባሻገር ዜጎች በዘርፉ ሊፈጠርላቸው የሚገባውን የስራ እድል እንዳይፈጠርላቸው እንቅፋት መፍጠሩን ተናግረዋል።

በተለይ በበዓላት ወቅት ቆዳ በየቦታው እንደ ቆሻሻ እንዳይጣል መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ መንግስት የቆዳ ፋብሪካዎች የማምረቻ ካፒታል እጥረት እንዳያጋጥማቸው ባንኮች በልዩ ሁኔታ ብድር እንዲያዘጋጁ የተደረገ መሆኑና እንደኬሚካል በመሳሰሉ ግብዓቶች ላይ ደግሞ የታሪፍ ማሻሻያ የተደረገለቻው መሆኑን ጠቅሰዋል። እንዲሁም ባሳለፍነው የፋሲካ በዓል ከነጋዴዎች ባሻገር ፋብሪካዎች ጭምር ቆዳና ሌጦ እንዲሰበስቡ ተደርጓል። ይህም በመደረጉ በአሁኑ ጊዜ የቆዳ ዋጋ አንሰራርቶ በበዓሉ የበግ ቆዳ እስከ ከ40 እስከ 60 ብር ፤ የበሬ ቆዳ ደግሞ ከ130 እስከ 150 ብር መሸጡን ተናግረዋል።

አቶ ብርሃኑ በፋሲካ በዓል ላይ የተሰራው ስራ በቀጣይ በኢዳልፈጥርም ሆነ በሌሎች በዓላቶች ተጠናክሮ ከቀጠለ ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆናቸው በርካታ ቆዳ ያገኛሉ። ይህም ፋብሪካዎች ከፍተኛ ምርት አምርተው ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ አቅርበው ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ ይሆናል። ፋብሪካዎቹ ብዙ ምርት ለማምረት ደግሞ የሰው ኃይል ስለሚያስፈልጋቸው ለብዙ ዜጎችም የስራ እድል ይፈጠርላቸዋል። ስለዚህ አገሪቱን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንድትሆን ያደርጋታል ብለዋል።

አቶ ብርሃኑ በተለይ እንስሳት በቁም እያሉ በቆዳ ላይ የሚከሰተው የቆዳ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ በቆዳ ኢንዱስትሪው ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በተቻለ መጠን የቆዳ ጥራትን ለማሻሻል ግብርና ሚኒስቴር በእንስሳት ቆዳ ላይ የሚከሰቱ እንደ እከክ ያሉ መሰል በሽታዎችን ለመከላከል አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ እንስሳቱን በአግባቡ ተንከባክቦ እንዲያረባ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ በተለይ በበዓላት ወቅት በሚከናወነው እርድ የቆዳ ጥራት ተጠብቆ ለፋብሪካዎች እንዲቀርብ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን ለመስጠት እየሰራ ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ የገጠሩ ማህበረሰብ ቆዳና ሌጦ ተሸክሞ ረጅም ርቀት ተጉዞ ለገበያ ለማቅረብ ያለው እንግልት ወይም የትራንስፖርት ወጪ በመፍራት ቆዳው የሚባክንበት ሁኔታ ይስተዋላል። ችግሩን ለመፍታትም የእንስሳት ሃብት በብዛት ባሉባቸው አካባቢዎች የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ማቀነባበሪያ አነስተኛ ፋብሪካዎች በየክላስተሩ እንዲቋቋሙ ለማድረግ ፕሮጀክት ተጠንቶ ወደ ተግባር ለመግባት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንግስት ትምህርት ቤት ለሚማሩ ሁሉም ተማሪዎች ከመማሪያ ቁሳቁስ ባሻገር የትምህርት አልባሳትን ለማሟላት የተያዘው የትምህርት ቤት የጫማ ፕሮጀክት ከመዲናዋ አልፎ ለወደፊት በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ መነሻ መሰረት በአገሪቱ እስከ 30 ሚሊዮን ለሚደርሱ ተማሪዎች ለጫማ፣ ለቦርሳ ወዘተ መስሪያ ዋነኛ ግብዓት ሆኖ የሚያገለግለው ቆዳ በመሆኑ ቆዳ በአገሪቱ ተፈላጊነቱ ይጨምራል ። ህብረተሰቡም ጥቅሙን አይቶ ለቆዳ ትኩረት ይሰጣል። ወደፊት እነዚህ ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር ሲገቡ ቆዳ በአግባቡ ተሰብስቦ ለአገር ውስጥ ምርትና ለውጭ ገበያ ቀርቦ የውጭ ምንዛሬ ከማስገኝቱ ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር እንደሚሆን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ስለዚህ ህብረተሰቡ ለጊዜው ወደ ኪሱ የሚገባውን ገንዘብ ሳያሰላ ከእያንዳንዱ ህብረተሰብ ተሰብስቦ ወደ ፋብሪካ የሚገባው ቆዳና ሌጦ ለዜጎች የሚፈጥረውን የስራ ዕድልና ለአገር የሚኖረውን ገቢ ከግምት ውስጥ በማስገባት ቆዳን በአግባቡ ለነጋዴዎች ወይም ለፋብሪካዎች በማቅረብ ህብረተሰቡ የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት አለበት።

በአጠቃላይ ቆዳ ሲጣል የሚጣለው ገንዘብ ብቻ ሳይሆን አካባቢንም ጭምር ይበክላል። ይህም ህብረተሰቡን ለተለያዩ የጤና ጠንቅ የሚዳርግ ተግባር ነው። ስለዚህ ህብረተሰቡ በአንድ በኩል ጤናውን ለመጠበቅ በሌላ በኩል አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኝውን ጥቅም እንድታገኝ ቆዳን በአግባቡ ለፋብሪካዎች ወይም ለነጋዴዎች በማቅረብ አገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ኢንስቲትዩቱ መልዕክቱን ያስተላልፋል ብለዋል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 29/2013


Leave a Reply