ቴሌ ብር የሞባይል ገንዘብ ማዘዋወር አገልግሎት ፈቃድ ለኢትዮ ቴሌኮም ሲሰጥ ድርጅቱ አቅሙን አጎልብቶ ከውጭ ተቋማት ጋር የመወዳደር ብቃት እንዲያጎለብት መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ይህ ለኢትዮ- ቴሌ ኮም ብቻ የተሰጠ እድል ለአንድ አመት ብቻ የሚቆይ መሆኑን ጠቁመዋል ። እድሉን በመጠቀም ኢትዮ ቴሌኮም በጥብቅ ዲሲፕሊን ሥራውን በውጤታማነት መፈጸም እና አቅሙን ማጎልበት እንዳለበት አሳስበዋል።

መንግሥት በቴሌኮም ዘርፍ ሁልጊዜም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንደሚያስቀድም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስታወቁ። ኢትዮ ቴሌኮም ‹‹ቴሌ ብር ››የተሰኘ ለማህበረሰቡ ምቹ እና ሁሉን አካታች የገንዘብ ማስተላለፊያ እና የመገበያያ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት አስጀመረ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የሞባይል የክፍያ ሥርዓቱን ትናንት በወዳጅነት አደባባይ በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳስታወቁት ፣ኢትዮጵያ በሞባይል ገንዘብ ማዘዋወር አገልግሎት ከዓመታት በፊት መጀመር ሲገባት ባለመጀመሯ ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ ለመቀበል ተገዳለች ።

በሞባይል ገንዘብ ማዘዋወር አገልግሎት ካለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር እንዲጀመር ከ10 ዓመት በፊት ለመንግሥት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም መንግሥት እንዲጀመር ፍላጎት አለማሳየቱን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ የቴሌኮም ዘርፉ ከሁለት አመት በፊት ለውጪ ባለሀብቶች ክፍት ይሆን ተብሎ ሲወሰን አንዱ እና አከራካሪው ጉዳይ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር እንደነበር አመልክተዋል ።

እንደ አገር በሞባይል ብር የማዘዋወር አገልግሎትን ስንጀምር ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎናል።በአሁን ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰሙ የመገናኛ ብዙኃን ፕሮፖጋንዳዎች በአብዛኛው ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ጠቁመዋል።

የመገናኛ ብዙኃን የፕሮፖጋንዳ ዱላ እንዲያርፍብን የመረጥንበትን ዋናው ምክንያት በቀጥታ ከብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚያያዝ ስለሆነ ነው። በአሁኑ ወቅትም በዘርፉ ለመሳተፍ ጥያቄ ላቀረቡ የሞባይል የገንዘብ ዝውውር አለመካተቱን አስታውቀዋል ። በዚህም ሀገሪቱ በትንሹ 500 ሚሊየን ዶላር እንደምታጣ አመልክተዋል ።

በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው አካል፤ ማወቅ የሚገባቸው ሁሌም ቢሆን መንግስት በቴሌኮም ዘርፉ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም እንደሚያስቀድም ነው ብለዋል።

ቴሌ ብር የሞባይል ገንዘብ ማዘዋወር አገልግሎት ፈቃድ ለኢትዮ ቴሌኮም ሲሰጥ ድርጅቱ አቅሙን አጎልብቶ ከውጭ ተቋማት ጋር የመወዳደር ብቃት እንዲያጎለብት መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ይህ ለኢትዮ- ቴሌ ኮም ብቻ የተሰጠ እድል ለአንድ አመት ብቻ የሚቆይ መሆኑን ጠቁመዋል ። እድሉን በመጠቀም ኢትዮ ቴሌኮም በጥብቅ ዲሲፕሊን ሥራውን በውጤታማነት መፈጸም እና አቅሙን ማጎልበት እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው፣ኩባንያው ባለፉት 127 ዓመታት ካቀረባቸው አገልግሎቶች ለየት ያለውን የቴሌ ብር አገልግሎት ለደንበኞቹ ማቅረቡን አስታውቀዋል።

የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ምቹ እና ሁሉን አካታች የገንዘብ ማስተላለፊያ እና የመገበያያ ዘዴ መሆኑን ያስታወቁት ወይዘሪት ፍሬህይወት ፣ አገልግሎቱን ደንበኞች ስልካቸውን በመጠቀም ብቻ መጠቀም እንደሚችሉ ገልጸዋል። በአገልግሎቱም ገንዘብ መላክ ፣ መቀበልና ግዢ መፈጸም እንደሚችሉም ጠቁመዋል ።

ቴሌ ብር የተሰኘው የክፍያ ስርዓቱት ደንበኞች ጥሪ ብር ወይም ቼክ ሳያስፈልጋቸው ዘርፈ ብዙ ክፍያዎችን እንዲፈፅሙ የሚያደርግ ነው። አገልግሎቱ ጤናማ የገንዘብ ፍሰትን ከመፍጠሩም ባሻገር ቁጠባን በማሳደግ፣ ድህነትን ለመቀነስ ፣ ሥራ ፈጣሪነትንና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እንዲሁም ገንዘብ የሚታተምበትን ወጪ በመቀነስ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድገው አስታውቀዋል ።

በፋይናንስ አገልግሎት ዘርፉ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ እና የኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የምትደርገው ሽግግር ለማገዝ ሁነኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሪት ፍሬህይወት ፣ አገልግሎቱ ኢትዮ ቴሌኮም ካለው ሰፊ ተደራሽነት አንፃር ትልቅ የሚባል ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል ። በተለይም በውጭ አገር ከሚገኙ ተጠቃሚዎች የሚደረገው የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት፣ ለኩባንያውም ሆነ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ እንደሆነ ገልጸዋል።

በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ ከ 40 በመቶ እስከ 50 በመቶ ያሕል ጠቅላላ የአገሪቱ ግብይትና የገንዘብ ፍሰት በቴሌ-ብር እንዲከወን መታቀዱን ያመለከቱት ወይዘሪት ፍሬህይወት ፣ መተግበሪያም በአምስት ቋንቋዎች መዘጋጀቱን አስታውቀዋል ።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም

Leave a Reply