“ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በአንድነት በመከባበር፤ በመተሳሰብ እና በመረዳዳት ሊያከብር ይገባል”

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር ኢድሪስ

ሕዝበ ሙስሊሙ 1442ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓል ሲያከብር በአንድነት ፣በመከባበር፤ በመተሳሰብ እና በመረዳዳት መሆን እንዳለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር ኢድሪስ አሳሰቡ።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር ኢድሪስ የኢድ አልፈጥር በዓል አስመልክተው በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት የእንኳን አደረሳችሁ መግለጫ፣ ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር በአንድነት፣ በመከባበር፤ በመተሳሰብ ያለው ለሌለው በማካፈል በመረዳዳትና በአንድነት መንፈስ መሆን እንደሚገባው አሳሰበዋል።

ለኢድ ቀን ሰደቃ ማብላት፤ የደከሙትን መጠየቅ፤ አብሮ መብላት፤ መደገፍ መጠያየቅ አስፈላጊ ነው ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ፣ ለሌለው በመስጠት በሰላም፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በመከባበር በዓሉ መከበር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በተለይም በሀገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉ መልካም ያልሆኑ ነገሮችን አላህ እንዲያነሳልን ፀሎት ማድረግ አለብን ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ለሰላም መሰረቱ አንድነት መሆኑን ጠቁመዋል።

በዓሉ በአዲስ አበባ ስታድየም የሚከበር መሆኑን ያስታወቁት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ፣ ሕዝበ ሙስሊሙ ለመስገድ ሲሄዱም ሆነ ሲመለስ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በስክነት ኃይማኖታዊ ሥርዓቱን ማካሄድ እንደሚኖርበት  አሳስበዋል።

“በአገሪቱ በየአቅጣጫው ችግሮች አሉ፤በግብፅም በሱዳንም በአገር ውስጥም ያሉ ችግሮች እንዲቀረፉ ዱኣ ( ፀሎት) ማድረግ ይገባል።

እኛ ማንም ሰው እንዲበደል፤ ማንም ሰው እንዲከፋ እንደማንፈልግ ሁሉ ሕዝባችንን የሚያስከፋ፤ ሰላማችንን የሚያደፈረስብን አንቀበልም። “በአገሪቱ ያሉ እህት ወንድሞች በሙሉ ወደ አንድነት እንመለስ፤ ወደመከባበር እንመለስ፤ በተለይ ሙስሊሙ ማህበረሰብ መጥፎ መናገር፤ በደል ማድረስ በሃይማኖቱ የተከለከለ ነው ። ከዚህ ይልቅ ሰላምን አጠንክረን ልማትን አፍጥነን ሀገራችንን ማሳደግ ይኖርብናል “ብለዋል።

̋ሀብት የሌለው ሰው፤ ያላደገ አገር፤ያላደገ ሕዝብ፤ ራሱን ማስከበር አገሩን ማስከበር አይችልምና እባካችሁ አንድ እንሁን አገራችንን አንድ እናደርግ።መሪዎቻችን በሰላም እንዲመሩ የምንመራውም በሰላም የምንመራ እንሁን”ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

አገር መብቷ እንዲከበር አንድነትና ሕብረት ወሳኝ መሆኑን ያመለከቱት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር፣ ጠብና ክርክርን ወደ ጎን በመተው በአንድነት አገርን ለማሳደግ መሥራት እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ሕዝብ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የጤና ሚኒስትር ኮቪድን ለመከላከል ያስቀመጣቸውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ እንደሆነ፤ ሕዝቡ ከወንጀል ራስን በመሰብሰብ፣ ከኃጥያት በመራቅ፣ ከበደል በመቆጠብና ወደ ፈጣሪ በመመለስ በሽታው እንዲወገድ መፀለይ ይኖርበታል ብለዋል።

See also  በአማራ ክልል በተፈጸመ ወረራ ከ700 ሺህ በላይ ንጹሀን ዜጎች ተፈናቅለዋል

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም


    Leave a Reply