ሠራዊቱ ዝግጁነቱን አረጋግጦ ይገኛልየህዳሴ ግድባችን ሕልውናችንና የሕዝባችን አንጡራ ሃብት…

የህዳሴ ግድባችን ሕልውናችንና የሕዝባችን አንጡራ ሃብት በመሆኑ በግድቡ ላይ የሚቃጡ ትንኮሳዎችና ጥቃቶችን ለመከላከል የምዕራብ ዕዝ ከመቼውም ጊዜ በላቀ የዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛል ሲሉ የዕዙ ም/አዛዥና የመተከል ዞን የተቀናጀው ግብረ – ኃይል ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ ብ/ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ ገለፁ።

የግድቡ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ ሠራዊቱ ዝግጁነቱን አረጋግጦ ይገኛልም ብለዋል።

ጄኔራል መኮንኑ አክለውም ፣ የውሃ ሙሌቱን ማንም የውጪ ኃይል አያስቆመውም፤ የሰራተኞቹ ደኀንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ይጠበቃል፤ስራው ያለምንም እንቅፋት እንዲከናወንም በየደረጃው ያለ የሰራዊት አባል ከሌሎች ተጓዳኝ የጦር ክፍሎች ጋር በመሆን በቁርጠኝነት እየሰራን እንገኛለን በማለት ተናግረዋል።

ብ/ጄ አለማየሁ አያይዘውም ፣ መጪው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ተጀምሮ እሰከሚያልቅ ድረስ ፀጥታውን አስተማማኝ ለማድረግ ዕዙ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉንም ገልፀዋል።

የመተከል ዞንን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ የዞንና የወረዳ ኮማንድ ፖስቶች በትኩረት እየሰሩ እንደሚገኙ የገለፁት ጄኔራል መኮንኑ ፣ የህዝቡን ሞትና መፈናቀል ለማስቀረት የፀጥታ ኃይሉ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፤ሠራዊቱ ለህዝቡ ሲል ቆስሏል መስዋዕትነትም ከፍሏል፤ መስዋዕትነቱ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለሰጡት ተልዕኮ የተከፈለ ነው በማለትም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ወደ ተሃድሶ ማዕከል ገብተው በስልጠና ላይ የሚገኙ ታጣቂዎችን ከሕብረተሰቡ ጋር የማገናኘትና የማቀራረብ ስራ እየተሰራ ነው ፤ ታጣቂዎቹ ወደ ሰላም አማራጭ በመምጣታቸውም ሕብረተሰቡ አንፃራዊ ሰላም ተፈጥሮለታል ሲሉ ጨምረው ገልፀዋል።

ዳዊት እንዳለ
ፎቶግራፍ ዳዊት እንዳለ

See also  ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተጸነሰው ሴራ ( አክሎግ ቢራራ – ዶ/ር)

Leave a Reply