ኮሮናቫይረስ፡ ሁለት የተለያዩ የኮቪድ-19 ክትባቶችን ብንወስድ ምን እንሆናለን?

የዓለም አገራት የክትባት ሽሚያ ላይ ናቸው። የሃብታም አገራት መሪዎች “ከሕዝባችሁ ሕዝቤ ይቀድማል” እያሉ ከሚያስፈልጋቸው ክትባትም በላይ ገዝተው መጋዘን እየቆለፉ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ የሃብታም አገራት መስገብገብን ክፉኛ ተችተዋል፤ በተደጋጋሚ። አሁን በዓለም ቅቡልነት ያገኙት ክትባቶች የሩሲያው ስፑትኒክ፣ የቻይናው ሲኖፋርም፣ የእንግሊዙ አስትራዜኔካ፣ የአሜሪካኖቹ ፋይዘር፣ ሞደርና እንዲሁም ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ይገኙበታል።

እነዚህ የኮቪድ-19 ክትባቶች በአውሮፓና በአሜሪካ በስፋት እየተሰጡ የሚገኙ ናቸው። በደቡብ አሜሪካ፣ በአፍሪካና በእሲያም አንዳንዶቹ እየተዳረሱ ናቸው።

ክትባቱን ለዜጎቿ በከፍተኛ ትጋት እያቀረበች የምትገኘው አሜሪካ በመጪው ሐምሌ ወር 70 ሚሊዮን ዜጎች ክትባት አግኝተው በነጻነት መንቀሳቀስ ይጀምራሉ ስትል ዕቅድ ይዛ እየሠራች ነው። ባይደን በክትባቱ ዘመቻ ላሳዩት ትጋትም እየተሞካሹ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ሳይንቲስቶች አዲስ ምርምር ይዘዋል።

ሰዎች አንድ ክትባት ተከትበው ሲያበቁ በ2ኛው ዙር ሌላ ዓይነት ክትባት ቢወስዱ ይሞታሉ? ይጎዳሉ? ወይስ ይጠቀማሉ? የሚል ነው ምርምሩ። ምርምሩ ገና መቋጫ ባያገኝም ለጊዜው ያገኙት ውጤት አንድ ሰው አንድ ክትባት ወስዶ ሌላ ቢቀላቅል የጎንዮሽ ጉዳቱ መጠነኛ የሚባል ብቻ ነው የሚኾነው።

ክትባት የቀላቀሉ ሰዎች ክትትል ተደርጎላቸው ያሳዩት ብቸኛ ምልክት ብርድ ብርድ ማለት፣ ራስ ምታትና የጡንቻ ህመም ብቻ ነው። ይህ መካከለኛ የጎንዮሽ ጉዳት አንድ ዓይነት ክትባት የወሰዱት ሰዎች ከሚያሳዩት ህመም ባስ ያለ ነው። ክትባት የቀላቀሉ ሰዎች ይህ ነው የሚባል ለሕይወት አስጊ የሆነ ምልክት አላሳዩም።

“ምርምሩን ስንጀምረው ይህን ውጤት አልጠበቅንም ነበር” ብለዋል የኦክስፎርድ የክትባት ቡድን ባልደረባ ፕሮፌሰር ማቲው ስኔፕ። ይህ ካም-ኮቭ የተባለ ስም የተሰጠው ጥናት የተጀመረው ባለፈው የካቲት ወር ነበር። ዓላማ ያደረገውም በአንደኛና በሁለተኛ ምዕራፍ አንድ ሰው ሁለት የተለያዩ የክትባት ጠብታዎችን ቢቀላቅል የመከላከል አቅሙ ይበልጥ ያድጋል ወይስ በተቃራኒው ይሆናል? የሚል ነበር።

መላምቱ የነበረው የክትባት ጠብታ ቀላቅለው የወሰዱ ሰዎች የመከላከል አቅማቸው ይጎለብት ይሆናል የሚል ነበር። አንዳንድ አገሮች አንዱን የክትባት ዓይነት ቢጨርሱ በምዕራፍ ሁለት ጠብታ ለሚወስዱ ሰዎች ሌላኛውን ዓይነት ክትባት ቢሰጧቸው ምን ሊፈጠር ይችላል የሚል ነበር። ጥናቱ የተመራው በኦክስፎርድ ዩነቨርስቲ ነበር።

See also  አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ – የተሳሳተውን የውጫሌ ውል የመረመሩ ጀግና ኢትዮጵያዊ

ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ 830 በጎ ፈቃደኞች በዚህ ጥናት ውስጥ ተሳትፈዋል። በመጪው ሰኔ የዚህ ምርምር የተሟላ ውጤት ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል ተብሏል። አሁን የጥናቱ ቅድመ ውጤት የታተመው በዝነኛው ‘ላንሴት’ የጤና አካዳሚ መጽሔት ላይ ነው። የካናዳ ግዛቶች የሆኑት ኦንታሪዮና ኩቤክ ይህን የመቀላቀል ሙከራ ተግባራዊ ለማድረግ እያሰቡበት እንደሆነ ተነግሯል።

ሙከራው ከተደረገባቸው 10 ሰዎች በአንዱ አነስተኛ የሚባል የጎንዮሽ ጉዳት ያሳያል። እነዚህ 10 ሰዎች በአራት ሳምንት ልዩነት አስትራዜኒካ ክትባትን ብቻ የወሰዱ ናቸው። ይህም ማለት ሌላ የክትባት ዓይነት አልቀላቀሉም። ይህ አነስተኛ የጎንዮሽ ጉዳት የተባለውም ትኩሳታቸው ከፍ በማለቱ ነው።

አስትራዜኒካንና ፋይዘርን በ4 ሳምንት ልዩነት ቀላቅለው የወሰዱ (ማለትም መጀመርያ አስትራዜኒካን ከ4 ሳምንታት በኋላ ደግሞ ፋይዘርን የወሰዱ) የሚያሳዩት የጎንዮሽ ምልክቶች በ34 ከመቶ ከፍ ብሎ ታይቷል። ከፍ ካሉ ምልክቶች መካከልም ድካም፣ የጡንቻ ህመም፣ ራስ ምታት ይገኙበታል።

“ምርምሩ ያመለከተው ነገር ቢኖር ክትባቱን ቀላቅለን ለነርሶች ብንሰጣቸው በነገታው ወደ ሥራ የሚመጡት ነርሶች ቁጥር እንደሚቀንስ ነው” ብለዋል ፕሮፌሰሩ። ይህም አባባላቸው ክትባቶችን መቀላቀል ለጊዜው የጎንዮሽ ጉዳቱን (ምንም እንኳ ለጤና አስጊ የሚባል ባይሆንም) እንደሚጨምር ነው። ለጊዜው ሙከራው የተደረገው አስትራዜኒካን ከፋይዘር ጋር በመቀላቀል ነው።

በመጋቢት ወር የበጎ ፍቃደኞችን ቁጥር ወደ 1ሺህ 50 አድጎ ሌላ ሙከራ ተደርጓል። እነዚህ በጎ ፈቃደኞች ደግሞ እንዲወስዱ የተደረገው የሞደርና እና የኖቫቫክስት ክትባቶችን ነው። የዚህ ውጤት ገና ለኅትመት አልበቃም።

BBC AmharicLeave a Reply