የተላላኪው ጠበቃዎች – “አልጨረስንም?”

የተገደሉ ናቸው የተባሉ ሴቶች አስከሬናቸው አስፋልት ላይ ተደርድሮ ደማቸው ሲጎርፍ በቀጥታ ቴሌቪዥን ይተላለፍ ነበር። የቴሌቪዥን ዘጋቢው እነኝህ ከፖለቲካ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው እናቶች እንዴት በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉ እያብራራ ባለበት ሰአት ተገድለዋል ተብለው አስፋልት ላይ ከተጋደሙት ሴቶች መካከል አንዷ ድንገት ብድግ ብላ “አልጨረስንም?” ብላ ስትጠይቅ በቦታው የነበሩ ሰዎች እየተርበተበቱ መልሳ እንድትጋደም አደረጓት። ለካ አስፋልት ላይ

By Haile Mulu

እንደ ሲኤንኤን እና ኒው ዮርክ ታይምስ የመሳሰሉ ዓለም ዓቀፍ የሚዲያ ተቋማት በኢትዮጵያ ዙሪያ በየጊዜው አሉታዊ ዘገባዎች ሲያወጡ ሁሌም ትዝ የሚለኝ ከአመታት በፊት ወደ ቦትስዋና በተጓዝኩበት ወቅት የሰማሁት አስገራሚ ገጠመኝ ነው።
ዓለም ዓቀፉ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት (ICC) የሚሰራውን ስራና የተጣለበትን ሃላፊነት በተመለከተ ግንዛቤ ለማስጨበጥ አንድ የጀርመን በጎ አድራጎት ድርጅት ባዘጋጀው ወርክሾፕ ላይ ለመሳትፍ ወደቦትስዋና ዋና ከተማ ጋቦሮኒ በተጓዝኩበት ወቅት ከኮትዲቯር ከመጣ አንድ ጋዜጠኛ ጋር ተቀራርቤ በእየለቱ ስለየአገሮቻችን ፖለቲካ እናወራ ነበር።

በወቅቱ ፈላጭ ቆራጭ ናቸው ተብለው ሲነገርባቸው የነበሩት የኮትዲቯሩ ፕሬዝዳንት ሎረን ባግቦ “በምርጫ አሸንፊያለሁ” በማለት ስልጣን አለቅም በማለታቸው በፈረንሳይ ጦር በሚታገዘው የአላሳን ኦታራ ሰራዊት ከመሪነታቸው ተነስተው በቁጥጥር ስር ውለው ስለነበር በቅናት መንፈስ ታጅቤ “እኛ አለን እንጂ አሁንም በሰቆቃ ውስጥ ያለን እናንተስ ተገላገላችሁ” ስለው ከሙያ አጋሬ የሰማሁት መልስ የጠበኩት አልነበረም።

READ MORE


” ኮትዲቯር ውስጥ የሚከሰተውና እናንተ በሚዲያ የምትሰሙት ነገር የተለያየ በመሆኑ በሎረን ባግቦ ከስልጣን መወገድ ደስተኞች እንደሆንን ብታስቡ አልፈርድባችሁም። ለምሳሌ ሎረን ባግቦ ከመያዙ በፊት የተከሰተ አንድ አስገራሚ ነገር ልንገርህ። ምዕራባውያን ሚዲያዎች የባግቦ ሰራዊት ሴቶችንና ህፃናትን እንደሚገድል በተደጋጋሚ ይዘግቡ ስለነበር አለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ሎረን ባግቦ ከስልጣን መውረድ ብቻ አይደለም ተሰቅሎ ቢያየው ደስተኛ ነበር። ይሄ የሚዲያዎች ዘገባ ውሸት መሆኑን የምናውቀው እኛ ኮትዲቯራውያን ብቻ ነበርን።
ታዲያ አንድ ቀን ምን ተከሰተ መሰለህ። በሎረን ባግቦ ሰራዊት በጥይት ተጨፍጭፈው የተገደሉ ናቸው የተባሉ ሴቶች አስከሬናቸው አስፋልት ላይ ተደርድሮ ደማቸው ሲጎርፍ በቀጥታ ቴሌቪዥን ይተላለፍ ነበር። የቴሌቪዥን ዘጋቢው እነኝህ ከፖለቲካ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው እናቶች እንዴት በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉ እያብራራ ባለበት ሰአት ተገድለዋል ተብለው አስፋልት ላይ ከተጋደሙት ሴቶች መካከል አንዷ ድንገት ብድግ ብላ “አልጨረስንም?” ብላ ስትጠይቅ በቦታው የነበሩ ሰዎች እየተርበተበቱ መልሳ እንድትጋደም አደረጓት። ለካ አስፋልት ላይ የተጋደሙት ሴቶች ተገድለው ሳይሆን ተከፍሏቸው ድራማ እየሰሩ ነበር። ይህንን ድርጊት በአይኑ በብረቱ የተመለከተው የኮትዲቯር ህዝብ የውጭ ሚዲያዎች ይህንን ቅሌት ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ያጋልጣሉ ብሎ በተስፋ ጠብቆ ነበር። በማግስቱ የሰማነው ዜና ግን ‘የሎረን ባግቦ ወታደሮች ሴቶችን ጨፍጭፈው ገደሉ’ የሚለውን የፈጠራ ዜና ነበር” አለና የምፀት ሳቅ ከሳቀ በኋላ ፊቱን በሃዘን አኮማተረው።

See also  "3000 ሌሊቶች" Andwalem Arage

“ለምንድነው ምዕራባውያን ሎረን ባግቦን ሰይጣን አድርገው በመሳል ከስልጣን እንዲወርድ የፈለጉት?” የሚል ጥያቄ ሳነሳለት እንዲህ ሲል ቀጠለ “ሎረን ባግቦ በምዕራባውያን በተለይም በፈረንሳይ የተጠላበትና ከስልጣን እንዲወርድ የተፈለገበት ዋናው ምክንያት በምርጫ ውድድር ወቅት ‘ኮትዲቯርን ከፈረንሳይ ተፅዕኖ አላቅቄ ከሌሎች አገሮች ጋር የፈለገችውን የንግድ ግንኙነት እንድትመሰርት አደርጋለሁ” በማለቱ ነው። አገሬ ከቅኝ ግዛት ከተላቀቀች በርካታ አስርት አመታትን ያስቆጠረች ቢሆንም ያለፈረንሳይ ፈቃድ ከማንም አገር ጋር ግንኙነት መመስረት አትችልም። የግብርና ምርታችን ወደሌላ አገር መሸጥ የምንችለው ፈረንሳይ አልፈልገውም ካለች ብቻ ነው። ባግቦ እንደማንኛውም የአፍሪካ መሪ ስልጣን ይወዳል። ግን ፈረንሳይ ከስልጣን ያስወገደችው የአገሩን ጥቅም በማስቀደሙ እንጂ ስልጣን በመውደዱ አይደለም። የፈረንሳይን ጥቅም አስጠብቀው የሚኖሩ በርካታ የምዕራብ አፍሪካ መሪዎች ለሃያ እና ለሰላሳ አመታት በፈላጭ ቆራጭነት ህዝባቸውን ሲገዙ ማንም ጥያቄ አንስቶባቸው አያውቅም ። ባግቦ የሃገሩን ጥቅም ለማስጠበቅ በመነሳቱ ነው በምዕራባውያን ጥርስ ተነክሶበት ከስልጣን እንዲወገድ የተደረገው። ” ሲል በብስጭት የመለሰልኝ መልስ አሁንም ድረስ ከአዕምሮየ አይጠፋም።
እና ይሄንን ሁሉ የቀባጠርኩት ምን ለማለት ነው? መልሱ አጭርና ግልፅ ነው። አሜሪካና ሌሎች ምዕራባውያን ሃገራት መቃብር ቆፍረው ህወሓትን ወደስልጣን ለማምጣት የሚጋጋጡት ጥሩ ተላላኪያቸው ስለነበረ ነው የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ ብቻ ነው።

በነገራችን ላይ ሎረን ባግቦን አስወግዶ የኮትዲቯር ፕሬዚዳንት የሆነው አላሳን ኦታራ የቡርኪናፋሶ ዜጋ ነበር። የምዕራባውያንን ጥቅም የምታስጠብቅ ከሆነ ከአገር ውስጥ አይደለም ከሌላ አገር አምጥተው ሊሾሙህ ይችላሉ። እኛ ግን ኮትዲቯር አይደለንም ። በአባቶቻችን አጥንትና ደም ነፃነታችን አስከብረን የኖርን ዜጎች በዶላር ምፅዋት ክብራችን ለተላላኪው ጠበቃዎች አሳልፈን አንሰጥም። ሮፍናን እንዳለው “እሯ” ብለን እንመልሳቸዋለን :

Haile Mulu Fb

Leave a Reply