ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ አገራትን ጣልቃ ገብነት በመቃወም “እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ” በሚል መሪ ሐሳብ በያሉበት ሆነው ለአንድ ሰዓት መልዕክታቸውን የሚያስተላልፉበት መርሃ-ግብር ነገ ይከናወናል።ጣልቃ ገብነቱን የሚቃወም የዲጂታል ፊርማ ማሰባሰብ መርሃ-ግብርም ዛሬ ማምሻውን እንደሚጀመር ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ በሚገቡ የውጭ አገራትን የሚቃወም ንቅናቄ ነገ በመላው ኢትዮጵያና ዓለም አቀፍ ደረጃ ይካሄዳል።መርሃ-ግብሩ “ብሔራዊ ክብር በሕብር” የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን ንቅናቄውን ያዘጋጁት ከማህበረሰብ አንቂዎች፣ አርቲስቶች፣ ሲቪክ ማህበራትና ታዋቂ ግለሰቦች የተወጣጡ ናቸው።በንቅናቄው የተለያዩ መርሃ-ግብሮች ይካሄዳሉ።

የንቅናቄው አስተባባሪ አቶ አቢይ ታደለ ነገ ከቀኑ 10 እስከ 11 ሰዓት ድረስ የሚቆይ “ከኢትዮጵያ እጃችሁን አንሱ” በሚል መሪ ሐሳብ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በያሉበት ሆነው ድምጻቸውን የሚያሰሙበት ዝግጅት እንደሚከናወን ገልጸዋል።መርሃ-ግብሩ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ አገራትን ጣልቃ ገብነት በመቃወም አጋርነታቸውን ለማሳየት ተዘጋጅተዋል።በአንድ ሰዓቱ መርሃ-ግብር “ብሔራዊ ክብር በሕብር”፣”እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ”፣”የውጭ አገራት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማክበር አለባቸው”፣”የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነታቸውን ያቁሙ”፣”የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ከማከናወን የሚያግደን ሃይል የለም” እና “ምርጫውን ማካሄድ የውስጥ ጉዳያችን ነው” የሚሉ ሐሳቦችን ያዘሉ መልዕክቶች ይተላለፋሉ ተብሏል።

ዜጎች የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም እንዲሁም በአደባባይ በመውጣት መልዕክታቸውን ማስተላለፍ እንደሚችሉ ነው አቶ አቢይ የገለጹት።በተያያዘም ንቅናቄውን በማስመልከት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት የዲጂታል ፊርማ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ዛሬ ማምሻውን ይጀመራል።በየፊርማ ማሰባሰቡ “እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ” በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄድ መሆኑን አስተባባሪው ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ነገ ማለዳ ከታዋቂ ግለሰቦችና አርቲስቶች የተወጣጡ ግለሰቦች በአዲስ አበባ በሚገኙ ኤምባሲዎች በመሄድ የተዘጋጁ ደብዳቤዎችን እንደሚያስገቡ ተናግረዋል።ደብዳቤው የውጭ አገራት በኢትዮጵያ የሚያከናውኗቸው መልካም ተግባራት ቢኖሩም በአሁኑ ሰዓት በውስጥ ጉዳይ እያሳዩ ያሉት ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት የሌለውና እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ የሚል ይዘት ያለው ነው ብለዋል።በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ የዚሁ ንቅናቄ አካል የሆነ የኪነ-ጥበብ ዝግጅት ይካሄዳል ያሉት አቶ አቢይ ዘላቂነት ባለው መልኩ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።ንቅናቄው የታለመለትን ግብ እንዲመታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።


Leave a Reply