አማራ ክልል በአብን ላይ “የክህደት ፖለቲካ አራማጆች ከንቱ ሙሾ ለፖለቲካዊ ቁርሾ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው” ሲል መግለጫ አወጣ

“የአማራ ሕዝብ በተስፋና ጉጉት የሚጠብቀው ምርጫ በክህደት ፖለቲካ አራማጆች አይደናቀፍም ” በሚል ርዕስ በክልሉ ህጻናትን ከፊት ያስቀደመና ሆን ተብሎ ብጥብጥ በማስነሳት ምርጫውን ለማስተጓጎል ሙከራ መደረጉን የአማራ ክልል ብልጽግና አስታወቀ። ክልሉ ባወጣው መግለጫ አብንን ወቅሷል። “የክህደት ፖለቲካ አራማጆች ከንቱ ሙሾ ለፖለቲካዊ ቁርሾ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው” ብሏል። ሙሉ መግለጫው ከስር ያንብቡ።

በኢትዮጵያ የሚካሄደው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም እንዲካሄድ የመርሐ-ግብር ማሻሻያ ቀን ተቆርጦለታል። እንደ ሀገር ያሉብን የውስጥና የውጭ ውጥረቶች ተቋቁመን ምርጫውን ስናካሂድ፣ ምርጫው የኢትዮጵያን ልዖላዊነት፣ የሕዝቦቿን የመወሰን መብትና ነጻነት የሚረጋገጥበት እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለን።

ይህን ጽኑ እምነታችን መሠረት አድርገን፤ በመላው የክልላችን ከተሞችና ወረዳዎች የብልጽግና ፓርቲ የድጋፍ ሰልፎችና የምረጡኝ ቅስቀሳዎች በደማቅ ሁኔታ በመከናወን ላይ ናቸው። የዚህ መርሐ-ግብር አካል የሆነ፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን በመርዓዊ ከተማ አስተዳደር ግንቦት 12/2013 ዓ.ም. ብልፅግና ፓርቲ የምረጡኝ ቅስቀሳና የድጋፍ ሰልፍ አካሂዷል፡፡

በሰልፉ ላይ በሰሜን ሜጫ ወረዳ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎችና በመርዓዊ ከተማ የሚገኙ የሁሉም ቀበሌዎች የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ የድጋፍ ሰለፉ በአካባቢው የጀግንነት ባህል መሰረት በፈረሰኞች የታጀበ፣ ውብና ደማቅ ሥርዓት ነበረው።

የፓርቲያችን አባላትና ደጋፊዎችም፣ ኃላፊነት የተሞላበት የአማራንና የኢትዮጵያን አንድነት የሚያንጸባርቁ መልዕክቶችን በድጋፍ ሰልፉ ላይ አንጸባርቀዋል።

ይሁን እንጅ የምርጫ ዘመቻ በሕግና ሥርዓት የሚመራ፣ አባላትና ደጋፊዎች “ይወክለኛል”፣ “ጥቅሜን ያስከብርልኛል”፣… ብለው የሚያምኑትን ፓርቲ ደግፈው ሠላማዊ የሆነ የጎዳና ትዕይት በማድረግ የመደገፍ መብት እንዳላቸው ያልተረዱና ከአማራ ነባር ባህልና እሴት በተቃርኖ የቆሙ ጽንፈኛ ኃይሎች የድጋፍ ሰልፉን ለማደናቀፍ በማሰብ ተሳታፊዎች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።
በዚህ አሳፋሪ ድርጊት ምንም የማያውቁ ታዳጊ ሕጻናትን ጭምር በመጠቀም፣ የድጋፍ ሰልፉን የማወክና ኃይል የቀላቀል ረብሻ በመፍጠር ሰልፉን ለማደናቀፍ ተሞክሯል።


ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የተሰጠ መግለጫ

በምዕራብ ጎጃም ዞን በመራዊ ከተማ ትላንት ግንቦት 12 ቀን 2013 ዓ.ም ድምፃቸውን በሰላማዊ መንገድ ባሰሙ ተማሪዎች ላይ የጸጥታ አካላት በወሰዱት እርምጃ የሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት ደርሷል። አብን በተማሪዎች ላይ የተፈፀመውን ጥቃት በጥብቅ እያወገዘ መንግስት ለጥቃቱ ትዕዛዝ የሰጡና የፈፀሙ አካላት ላይ አስቸኳይ ምርመራ በማድረግ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እንዲሁም ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ እንዲያደረግ እንጠይቃለን። በተለይ አሁን ባለንበት የምርጫ ወቅት ከገዢው ፖርቲ የተለየ ኃሳብ በሚያራምዱና ለብልፅግና ፖርቲ ድጋፍ ለማድረግ በማይፈልጉ ወገኖቻችን ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች የሕዝባችንንና የአገራችንን ሰላም የሚያናጉ በመሆናቸው መሰል ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ሊቆጠብ እንደሚገባ ለማሳሰብ እንወዳለን። ገዥው የብልጽግና መንግስት ሕዝቡ የሚሰጠውን ፖለቲካዊ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ተቃውሞንም በአግባቡ ለማዳመጥ መዘጋጀት እና በርካታ ችግሮች ባሉበት ሕዝብ ላይ ተጨማሪ ተግዳሮቶችን ለመፍጠር መሞከር ኃላፊነት የጎደለውና አዋጭነት የሌለው መሆኑን መቀበል ይገባል። አብን የተፈጠረውን ጥቃት በቅርበት እያጣራ ሲሆን የጥቃቱ ፈፃሚዎችን ለሕግ ለማቅረብ በሚደረግ እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ማረጋገጥ ይወዳል።አብን በጥቃቱ ሕይወታቸውን ባጡ ወገኖቻችን የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለፅ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይመኛል። በደረሰባቸው ጥቃት ተጎድተው በሕክምና ክትትል ላይ የሚገኙ ወገኖቻችን በፍጥነት እንዲያገግሙም መልካም ምኞቱን ይገልጻል።


የድጋፍ ሰልፉ ድምቀት የነበሩት ፈረሰኞች ላይ በቅርብ ርቀት በድንጋይ ውርወራ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል። በአርሶአደርና በግለሰብ ንብረቶች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል።

ሰልፉን የማደናቀፉ ተግባር ሰፊ ዝግጅት የተካሄደበት እንደሆነ ግልፅ የሆነው በወቅቱ የመንግሥት ተቋማትን ዒላማ ያደረጉ የማጥቃት ሙከራዎች በመካሄዳቸው ነው።

የኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ መሰናዶ ት/ቤት እና የመርዓዊ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የጉዳቱ ሰለባ ሁነዋል። የሰሜን ሜጫ ወረዳ ሠላምና ደህንነት ጽ/ቤት ባወጣው መረጃ መሠረት፣ የዚህ ሁከትና ግርግር ዋና ዓላማ ሰልፉን ከማደናቀፍ ባሻገር በመርዓዊ ከተማ በልዩ ልዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በጊዜዊ ማረፊያ ቤት የሚገኙ እስረኞችን በማስመለጥ ከተማውን ወደለየለት ብጥብጥ ለመክተት ያለመ ነበር።

ሰልፉን ለመረበሽ ህጻናት ተማሪዎችን በመቀስቀስና በማሰማራት ፣ ህገወጥ ታጣቂዎችን በመጠቀም ተኩስ በመተኮስ፣ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ድንጋይ በማስወርወር ሰልፉን ለመበተን ተጨባጭ ወንጀል ተፈጽሟል።

በዚሁ ሂደት በመንግስት ተቋማት ጠባቂወች በተሰነዘረ እርምጃ የሰወች ሕይወት ማለፉ በእጅጉ አሳዝኖናል። ለሟች ቤተሰቦችም ልባዊ ቁጭታችንንና ሀዘናችንን እንገልፃለን።

በሂደቱ የተፈጠረ ያልተመጣጠነ እርምጃ ካለ አስፈላጊው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ሁሉ እንወጣለን።

የሀገር ውስጥና የውጭ ኃይሎች ምርጫውን ለማደናቀፍ ጫናና ተጽዕኖን እንደመታገያ ስልት መርጠው እየተንቀሳቀሱ ባሉበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት፣ ‘በምርጫው የመራጮችን ይሁንታ አናገኝም’ የሚል ፍራቻ የገባቸው ኃይሎች ቀውስን የምርጫ-ፖለቲካ አማራጫቸው ለማድረግ ሲጥሩ እያስተዋልን ነው።

ይህን ስንል ተጨባጭ ሁነቶች ላይ ተመርኩዘን ነው። ከመርዓዊው ሁከትና ግርግር በተመሳሳይ ሰአት በደብረ ማርቆስ ከተማ እስተዳደር የተደረገውን የሴቶች የድጋፍ ሰልፍ በተሽከርካሪ ሰብሮ በመግባት የድጋፍ ድምጻቸውን ለማደናቀፍ ጥረት ተደርጓል።

አሁንም በተመሳሳይ ቀን የደንበጫ ከተማ አስተዳደር ሰላማዊ የድጋፍ ሰልፍ ለማደናቀፍ ሙከራዎች ተደርገዋል። እነዚህ ሁነቶች በጥቂቶች ስሜታዊነት አልያም በገጠመኝ የተፈጠሩ ሳይሆን፤ ሆን ተብሎ ታስቦና ታቅዶ የምርጫ-ፖለቲካ የቀውስ ዲዛይን ተዘጋጅቶ፣ የሰው ኃይል ስምሪት አደረጃጀት ተፈጥሮላቸው የተከናወኑ የጥፋት ድርጊቶች ናቸው።

ጥፋተኛ አካላት በሕግ ክትትል እየተደረገባቸው ሲሆን፤ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አድኖ ለፍርድ የማቅረቡ ሥራ የመንግሥት ኃላፊነት ይሆናል።

እንደ አማራ ብልጽግና ከዚህ ቀደም በምርጫ የድጋፍ ሰልፎቻችንና ቅስቀሳዎች ላይ ያጋጠሙንን ትንኮሳዎች በምርጫ ቦርድ አስፈላጊው መጣራት ተደርጎ ጉዳዩ እንዲታይልን ቅሬታ ማሰማታችን ይታወሳል። ይህ ምላሽ ባልተሰጠበት ሁኔታ በሠላማዊ የምርጫ ሂደት በማያምኑ ኃይሎች መርዓዊ ከተማ ላይ በፓርቲያችን አባላትና ደጋፊዎች ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል። የዓይነት ጉዳቶችም ተመዝግበዋል። በመሆኑም የምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ላይ አስፈላጊውን የማጣራት ሥራ በመስራት እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን። በእኛ በኩል፣ በዚህ ሁከትና ግርግር ከአማራ ህዝብ የዳበረ ባህልና እሴት በተቃርኖ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ጽንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች እጃቸው እንዳለበት ምልክቶችን አስተውለናል።

በመሆኑም የሚከተሉትን ወቅታዊ መልዕክቶች እናስተላልፋለን፦

1) ምርጫው ሕግና ሥርዓትን መሠረት አድርጎ ሰላማዊ ሂደቱን ጠብቆ እንዲካሄድ፣ በአማራ ክልል የሚወዳደሩ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በኃላፊነት ስሜት የበኩላቸውን አዎንታ ሚና እንዲወጡ እያልን፣ በክልላችን የተቋቋመው የፓርቲዎች የጋራ ምክር-ቤትም በየጊዜው ትንኮሳ፣ ሁከትና ግርግር ለመፍጠር የሚሞክሩ ፓርቲዎችን በጋራ ስምምነታችን መሠረት እንዲከታተልና እንዲያወግዝ፤

2) የክልላችን ሕዝብ ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በየአካባቢው ስምሪት የወስዳችሁ የጸጥታ ኃይል አባላት የምርጫ ጊዜ በመሆኑ በየከተሞች የድጋፍ ሰልፎችና የምርጡኝ ቅስቀሳዎች ይካሄዳሉ። ድርጅታችን ብልጽግና፣ ሕግና ሥርዓትን አክብሮ የሚያካሂዳቸውን የድጋፍ ሰልፎች ለማደናቀፍ፣ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ሁከትና ግርግር ለመፍጠር ትንኮሳዎችን የሚፈጽሙ ኃይሎች እንዳሉ በተግባር ያስተዋላችሁ በመሆኑ፣ በተለመደ ታጋሽነታችሁና ሕዝባዊነታችሁ ጸንታችሁ ሴራውን እንድታከሽፉ፤

3) ብልጽግና ፓርቲ የህዝብ፤ ለህዝብ፤ በህዝብ የሆነ ፓርቲ ነው። የህዝባችን መሠረታዊ ጥያቄዎች የመታገያ አጀንዳ ሁነው ደረጃ በደረጃ እንዲመለሱ ለማድረግ ከፍተኛ ትግል ላይም እንገኛለን። 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫን ለማሸነፍ የምንሰራውም በዚህ እምነት ነው። ስለሆነም የፓርቲያችን አባላትና ደጋፊዎች በሙሉ በክልላችን በመካሄድ ላይ ባሉ የድጋፍ ሰልፎችና የምረጡኝ ቅስቀሳዎች ምንም አይነት ትንኮሳዎች ቢደርሱ እንኳ በሙሉ የኃላፊነት ስሜት ሕግና ሥርዓትን አክብራችሁ የምርጫ ዘመቻችንን በጽናት እንድትወጡ መልዕክታችን እናስተላልፋለን።

በመጨረሻም

ከላይ እንደተመለከተው፣ ከወትሮው በተለየ መልኩ በሰሞነኛ የምርጫ ዘመቻዎቻችን ተደጋጋሚ ትንኮሳ፣ ሁከትና ግርግር ለመፍጠር ተደጋጋሚ ሙከራዎች ተካሂደዋል። መርዓዊ ላይ የሆነውም የዚህ ቅጥያ ነው።

በመርዓዊ ያደረግነው የድጋፍ ሰልፍ የዜጎችን ፍጹም ነጻ ፈቃድ ማዕከል ያደረገ ለመሆኑ የሜጫን አርሶ አደሮችና የከተማው ሕዝብ ምስክራችን ነው። በጣም የሚያሳፍረው የአብንና የፖለቲካ ክንፎቹ መግለጫ ይህንን ነባራዊ ሀቅ በመካድ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው።

እነዚህ ኃይሎች ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንዲሉ “ብልጽግና ተማሪዎች ሰልፍ እንዲወጡ አስገደደ” የሚል የሜጫን ፣ የመራዊንና የአማራን ህዝብ የናቀ መግለጫ አውጥተዋል። ፍርዱን ለአማራ ክልል ህዝብ ቅሬታችንን ለምርጫ ቦርድ እናቀርባለን።

የክህደት ፖለቲካ አራማጆች ከንቱ ሙሾ ለፖለቲካዊ ቁርሾ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው። ከምርጫ ውጭ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ ግብግብ አገርም ህዝብም ሊጠቅም እንደማይችል ደግመን እናሳስባለን። እንደብልጽግና እምነት፣ የስልጣን ምንጭ መሆን ያለበት የህዝብ ነፃ ድምፅ ነው። ከህዝብ ድምጽ ውጭ ስልጣን ለመያዝ ሁከት ያስነሳልኛል በሚል የብልጣ ብልጥ አካሄድ ህጻናትን ገፋፍቶ ለአመጽ በማነሳሳት ከሂደቱ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ሩጫ የፖለቲካ ዝቅጠት እንጂ በፍጹም ህዝባዊ ሊሆን አይችልም። ስለሆነም ከህዝባችን በጎ ፈቃድና ነፃ ምርጫ ውጭ የሚደረግ ማንኛውንም ህገወጥ አማራጭ በጽናት እንታገለዋለን። የአማራ ሕዝብ በተስፋና ጉጉት የሚጠብቀው ምርጫ በክህደት ፖለቲካ አራማጆች አይደናቀፍም!!!

የአማራ ህዝብ ትግል ከውስጥና ከውጭ በሚሰነዘር የጥቂት ፅንፈኞች ጥቃት በፍጹም አይደናቀፍም !!!


Leave a Reply