የሙኒክ ኦሊምፒክ ትራጄዲና የእሥራኤል አትሌቶች ጭፍጨፋ ሲታወስ

ከሁለት ሣምንታት በፊት በእሥራኤል እና ሃማስ መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ወደለየለት ጦርነት እንዳያመራ ስጋት ቢፈጥርም ዓለማቀፉ ማህበረሰብ በእሥራኤል እና ፍልስጤማውያን መካከል የተፈጠረው ውጥረት እንዲረግብ ጥሪ ሲያስተላልፍ ሰንብቷል:: ይህንንም ተከትሎ ሁለቱ አካላት ከትናንት በስቲያ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጋቸው ተነግሯል:: ባለፉት ሁለት ሳምንታ በላይ ግን እስራኤል ጋዛ ሠርጥን በተመረጡ ኢላማዎች ስትደበድብ ቆይታለች:: የሃማስ ደፈጣ ተዋጊዎችም ወደ ደቡባዊ እሥራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ሲያስወነጭፉ ከርመዋል:: ጋዛ ትንሽ ሠርጥ ናት፣ 360 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ትሸፍናለች። በሥሟ የተሰየመችው ዋና ከተማዋ ደግሞ ከትንሽም ትንሽ ከመሆኗ ባሻገር ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ ፍልስጤማዊ ተፋፍጎ ይኖርባታል። ትንሿ ግዛት፤ ትንሺቱ ከተማ የዓለም ምርጥ ጦር እሳት እየወረደባት አስከሬን ይለቀምባታል። ደምም ስታጎርፍ ኖራለች:: 2008 እንዲህ አሳልፋለች፣ 2009፤ 2012፤ ዘንድሮም ያው ናት:: ሠላም ሰፈነ ሲባል ግጭት ያገረሽባታል:: እሥራኤልና ሐማስ ጡንቻ ይለካኩባታል::

በበርካታ አረብ አገራት ተከባ የምትኖረው እሥራኤል ምንም ትንሽ አገር ብትሆንም ዘወትር ጠላቶቿን ስትገዳደር ኖራለች:: ጠላቶቿም ሲተኙላት አይታይም:: አልፎ ተርፎም ከአካባቢውና ከጦርነት ፍፁም የራቀ የስፖርት መድረክ ያውም ታላቁ ኦሊምፒክ ላይ ሳይቀር የእሥራኤልና ጠላቶቿ ግብ ግብ የማይረሳ ጠባሳ ጥሎ አልፏል:: የዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችንም በዘጠነኛው ሙኒክ ኦሊምፒክ በእሥራኤል አትሌቶች ላይ የተፈጠረውን አሳዛኝ ክስተት ያስታውሰዋል::

በጀርመን ሙኒክ ከተማ አስተናጋጅነት ተካሂዶ የነበረው ዘጠነኛው ኦሊምፒክ እንደ ስፖርት መድረክ ከውድድር አሸናፊ ጀግኖች ይልቅ በመጥፎ ገፅታውና ጥሎት ባለፈው አሳዛኝ አሻራ ይታወሳል:: ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ በጀርመን ለመጀመሪያ ጊዜ በተስተናገደው ኦሊምፒክ አውዳሚውን የሁለተኛ ዓለም ጦርነት የመራችው ጀርመን በአዲስ መንፈስ ከዓለም ሕዝብ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛ ለመራመድ ያላትን ትልቅ ፍላጎት ለማሳየት የኦሊምፒክ አዘጋጅነቱን እድል ያገኘችው ብዙ ደጅ ጠንታ ነበር:: በዚያ የኦሊምፒክ መድረክ እሥራኤልም ተሳታፊ ነበረች:: በሚሊየን የሚቆጠሩ ይሁዲዎች ሕይወታቸው በተቀጠፈበት ጀርመን፣ የናዚ መፈልፈያ በሆነችው ሙኒክ ከተማ በሚዘጋጀው ኦሊምፒክ የእሥራኤላውያን አትሌቶች መሳተፍ ለራሳቸውም ይሁን ለዓለም ሕዝብ ልዩ ደስታ ፈጥሮ ነበር:: እንደ ታሰበው ግን ኦሊምፒኩ የደስታ ሆኖ አልዘለቀም:: የሙኒክ ኦሊምፒክ እሥራኤላውያን አትሌቶች የተፈጁበት ሆነና አሰቃቂና መራር ገጠመኝ ደረሰ::

ውድድሮች ከመጀመራቸው አስቀድሞ እሥራኤል በሙኒክ ኦሊምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶችን ስታዘጋጅ ከረመች፣ በተለይም በነፃ ትግልና በሻሞላ ውድድር የሚሳተፉ አትሌቶቿ ሜዳሊያ ያስመዘግባሉ የሚል ተስፋ ጥላባቸው ነበር:: በተቃራኒው በተመሳሳይ ወቅት የእሥራኤል ጎረቤት በሆነችው የሊባኖስ ከተማ ቤሩትም ወደ ሙኒክ የሚያቀና የተለየ ተልዕኮ ያለው ቡድን ጥብቅና ከፍተኛ ተልዕኮ ያለው ልምድም እያከናወነ ነበር:: እነዚህ ሰልጣኞች የብላክ ሴፕቴምበር ወይም ጥቁር መስከረም ተብሎ የሚታወቀው ድርጅት አባላት ናቸው:: ለልዩ ተልዕኮ ወደ ሙኒክ የሚያቀኑት የዚህ ድርጅት አባላት በቤሩትና በሊቢያ በረሃዎች ከኦሊምፒኩ ቀደም ብለው ስልጠናቸውን አጠናቀቁ:: የጥቁር መስከረም አባላት የሙኒክ ተልዕኮ በተከበረው የስፖርት መድረክ ለመወዳደር ሳይሆን የእሥራኤልን አትሌቶች ለማጥቃት ነበር:: ጥቁር መስከረም የተባለው ድርጅት ከሙኒክ ኦሊምፒክ ከሁለት ዓመታት በፊት በ1963 ዓም በጆርዳን ነበር የተመሰረተው:: ንጉስ ሁሴን ፍልስጤማውያንን ከጆርዳን መንጥረው ካስወጡ በኋላ በፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅት ከለላ ስር ‹‹ጠላቶቼ›› የሚላቸውን መግደል፣ አውሮፕላን መጥለፍና ማገት ዋና ተግባሩ አድርጎ በቤሩት መቀመጫውን አደራጅቷል:: ጥቁር መስከረም በሌላው ዓለም በአሸባሪነት ሲፈረጅ በፍልስጤሙ ነፃ አውጪ ድርጅትና በራሱ እምነት ለነፃነት የሚታገል ተደርጎ ይቆጠራል:: ይህ ድርጅት ነው አባላቱን ወደ ሙኒክ ኦሊምፒክ በልዩ ተልዕኮ ያሰማራው:: ገዳይና ተገዳይ፣ አጥፊና ጠፊ በኦሊምፒክ መንደር የተገጣጠሙት በዚህ መልኩ ነበር::

በምዕራብ ጀርመን በሙኒክ ከተማ የተደገሰው ኦሊምፒክ የዓለም ሕዝብ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት አንጎበር ነቅቶ በአዲስ መንፈስ በድምቀት ተጀመረ:: የእሥራኤል የስፖርት ልዑክም ቀይ ኮትና ነጭ ሱሪ ለብሰው የይሁዲ መለያ የሆነችውን ቆብ ደፍተው በኦሊምፒኩ መክፈቻ መርሃግብር ላይ በስቴድየም ተመልካቾች ፊት በሰልፍ አለፉ:: ውድድሮችም በሠላም ተጀመሩ:: ነሐሴ 30 ቀን 1964 ዓም ሌሊቱ እየተገባደደ ከንጋቱ 10፡30 ላይ የጥቁር መስከረም አባላት የኦሊምፒክ መንደሩን አጥር ዘለው ገቡ:: በያዙት የስፖርት ትጥቅ ሻንጣ ውስጥ የጦር መሳሪያዎችን ይዘዋል:: ቀደም ብለው ከተባባሪዎቻቸው ጀርመኖች የእሥራኤላውያንን አትሌቶች መቀመጫ አውቀዋል፣ እሥራኤላውያን አትሌቶች ግን አገር አማን ብለው ተኝተዋል፣ ውጪ ሆነው የሚዝናኑም ነበሩ:: የእስራኤል የነፃ ትግል ውድድር አሰልጣኝ እንደሆነው ሙሴ ዋይንበርገር ዓይነቶቹም ቁጭ ብለው የሌሊቱን መንጋት ይጠባበቃሉ:: ሙሴ ያን እለት በሌሊት ተነስቶ ለመታጠብ እየተዘጋጀ ነበር፣ በመተላለፊያው ላይ በፍጥነት የሚጓዝ ኮቴ ሰማና ለማጣራት ጆሮውን ወደ ውጪ ጣለ፤ ወዲያው የነበረበት ክፍል በር በሃይል ተመታ፣ ያን ጊዜም በፈርጣማ ሰውነቱ በሩን ዘግቶ ጓደኞቹ ከተኙበት እንዲነቁ መጮህ ጀመረ:: ታጣቂዎቹ ግን ተረዳድተው በሩን በርግደው በመግባት በጥይት ጣሉት፣ በጓደኛው ጩኸት የተነሳው ሌላኛው እሥራኤላዊ አትሌት ከተኛበት ተወርውሮ አንዱ ታጣቂ ላይ ሰፈረበትና ጠመንጃውን ነጠቀው፣ ነገር ግን ከኋላው የነበረ ሌላ ታጣቂ ተኩሶ ገደለው:: ሁለቱን እሥራኤላውያን በመግደል የተጀመረው ጥቃት ዘጠኝ አትሌቶችን ከየክፍላቸው ሰብስቦ ወደ ማገት ተሸጋገረ:: ንጋት ላይም እሥራኤላውያንና ሌላው ዓለም አስደንጋጩን ዜና በኤቢሲ በኩል ሰሙ:: አጋቾቹ 240 የሚሆኑ በእሥራኤልና በሌላው ዓለም በእስር ላይ የሚገኙ ወገኖቻቸው ካልተፈቱ በስተቀር ከቀኑ 6፡00 ጀምሮ ታጋቾቹን አንድ በአንድ እንደሚገድሏቸው አስታወቁ:: የምዕራብ ጀርመን ባለስልጣኖች በአገራቸው የቀድሞውን ጠባሳ የሚያስታውስ ተመሳሳይ ድርጊት በእሥራኤላውያን ላይ በመፈፀሙ ተጨነቁ፣ እሥራኤልም ዜጎቿን ለማዳን ፈለገች::

ከጓደኞቻቸው አስከሬን ጋር አብረው የታገቱት አትሌቶችም ከዚህ አደጋ ለመውጣት ፈለጉ፣ ግን አልሆነም:: የእሥራኤሏ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎልዳሜር ‹‹ከአሸባሪዎች ጋር በጭራሽ አንደራደርም›› አሉ:: አጋቾቹ ደግሞ የጀርመን መንግስት ያቀረበላቸውን የገንዘብ ስጦታ ለመቀበል ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ፣ የኦሊምፒኩም መንደር በጭንቀት ተወጠረ:: የኦሊምፒኩ አዘጋጆች ለሞቱት አትሌቶች የሕሊና ፀሎት አድርገው ውድድሩን ለጊዜውም ቢሆን አቆሙት:: አጋቾቹ ያስቀመጡት የጊዜ ገደብም አለፈ፣ የምዕራብ ጀርመን ተደራዳሪዎች ከአጋቾቹ ጋር ንግግር ቀጥለዋል፣ እነሱንና ታጋቾቹን ይዞ ለጊዜው ወዳልታወቀ አረብ አገር የሚሄድ አውሮፕላን እንዲዘጋጅላቸው ስለጠየቁ የጀርመን ፖሊስ አጋጣሚውን ለመጠቀም በጎን ዝግጅት ማድረጉን ተያያዘው:: ጠቅላይ ሚኒስትር ጎልዳሜር እሥራኤላውያን ኮማንዶዎች ወገኖቻቸውን እንዲታደጉ ወደ ጀርመን እንዲገቡ ጠየቁ፣ ሆኖም የጀርመን መንግስትን ክብር የሚያዋርድ ተደርጎ በመቆጠሩ አልተፈቀደላቸውም:: ያም ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎልዳሜር የጀርመን መንግስት የሚሰራውን እንዲያዩ ብለው የሞሳዱን ሃላፊ ዛቪ ዛሚርን ወደ ሙኒክ ላኳቸው:: ታጋቾቹ እሥራኤላውያን አትሌቶች በሁለት ሔልኮፕተሮች ተሳፍረው ወደ ዋናው አውሮፕላን ማረፊያ ተጓጓዙ፣ በአውሮፕላን ማረፊያው የምዕራብ ጀርመን መንግስት አጋቾቹን ገድሎ ታጋቾቹን ለማስጣል አምስት አልሞ ተኳሾችን በሕንፃው ሰገነት የተለያዩ ቦታዎች ተገን ይዘው እንዲጠብቁ አድርጓል:: ሔልኮፕተሮቹ እጅና ወገባቸውን የታሰሩ አትሌቶችን ይዘው አውሮፕላን ጣቢያው እንደደረሱ አጋቾቹም ቦታ ቦታቸውን ያዙ፣ ያን ጊዜ አጋቾቹ አምስት ሳይሆኑ ስምንት መሆናቸው ታወቀ::

የአጋቾቹ መሪና ምክትሉ የተዘጋጀውን አውሮፕላን ተመልክተው ሲመለሱ አድፍጦ ይጠባበቅ የነበረው አልሞ ተኳሽ መሪውን ለመግደል ተኩሶ ሳተው፤ ከዚያ በኋላ አካባቢው በቀለጠ ተኩስ ተናጠ:: አልሞ ተኋሾቹ እንደታሰበው ኢላማቸውን መምታት ተሳናቸው፣ በዚህ መሃል ለመተኮስ ጊዜ ያገኙት አጋቾች ሔልኮፕተሮቹን በቦንብና በጥይት አነደዷቸው:: ምድር የናጠው የተኩስ ልውውጥ ጋብ ሲልም ሁሉም እሥራኤላውያን ታጋች አትሌቶች ማለቃቸው ተረጋገጠ:: አምስቱ አጋቾች በተኩስ ልውውጡ ተገድለው ሦስቱ እጃቸውን ሰጡ:: ለዚህ አሰቃቂ ፍፃሜ የምዕራብ ጀርመን መንግስት ክፉኛ ተወቀሰ:: ችሎታ የሌላቸው አልሞ ተኳሾች በማሰማራቱ፣ ተኩስ እንደተከፈተም ጥሶ የሚገባና ታጋቾቹን የሚያግዝ ብረት ለበስ ተሸከርካሪ ባለመመደቡ ተብጠለጠለ:: እሥራኤል ግን የጀርመኖች ተግባር ሆን ተብሎ የተፈፀመ ነው ትላላች:: ከተኩሱ በኋላ የምዕራብ ጀርመን መንግስት በቃል አቀባዩ በኩል ሁሉም ታጋቾች ነፃ እንደወጡና አጋቾቹም በሙሉ እንደተገደሉ መግለጫ ሰጠ:: በኦሊምፒክ መንደርና በመላው ዓለምም ደስታ ፈጠረ:: ከደቂቃዎች በኋላ ግን የኤቢሲ ዜና አንባቢ ሁሉም ነገር እንደተነገረው እንዳልሆነ የአስደንጋጩን ክስተት እውነታ አፈረጠ:: በየአገሩም የተቃውሞ ሰልፎች ተካሄዱ፣ የኦሊምፒክ አዘጋጆቹም የሃዘን ስርዓት አደረጉ:: ነገር ግን ኦሊምፒኩን ማቋረጥ የአሸባሪዎችን አላማ ማሳካት ተደርጎ ስለተቆጠረ ውድድሮች ከእሥራኤላውያን አትሌቶች ውጪ ቀጠሉ:: አስራ አንድ ጓደኞቻቸው የተገደሉባቸው አስራ ሰባት እሥራኤላውያን አትሌቶችም የሃዘን ማቅ ለብሰው ውድድሩን ሳይጨርሱ ወደ አገራቸው ተመለሱ::

ከዚህ ሁሉ ጉድ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎልዳሜር ለአገሪቱ ፓርላማ በሙኒክ የደረሰውን አሰቃቂ ነገር በጥልቅ ሃዘን አስረዱ:: ጎልዳሜር ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ለመልቀቅ ጊዜ እየጠበቁ በነበረበት ወቅት የአንድነትና የወዳጅነት መገለጫ በሆነው የኦሊምፒክ መድረክ በአደባባይ መጨፍጨፋቸው ያልጠበቁት ዱብዳ ነው:: በዚህ ክስተት ማዘንና መቆዘም ግን መፍትሄ እንደማይሆን አምነው ቀጣዩን ርምጃቸውን ማሰላሰል ተያያዙ:: ‹‹አሸባሪን ማሸበር›› በሚል በአገሪቱ የስለላ ተቋም ሞሳድ የሚመራ ኮሚቴ አቋቋሙ:: በአትሌቶቹ ግድያ እጃቸው ያለበት ሰዎችን ስም ዝርዝር አስመጥተውም እያንዳንዳቸው በያሉበት እየታደኑ እንዲገደሉ ትዕዛዝ አስተላለፉ:: የአትሌቶቹ አስከሬን ወደ አገራቸው በሚመለስበት ወቅትና የእሥራኤል ሕዝብ ሃዘን ላይ በነበረበት ሰዓት ገዳዮቹን የሚያድነው ሚስጥራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሞሳድ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰላዮቹን አሰማርቶ መረጃዎችን እያጠናከረ ነበር:: ሞሳድ ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥም የመጀመሪያውን ተጠርጣሪ ሮም ከተማ ውስጥ በአስራ አንድ ጥይት ደብድቦ መግደሉ ተሰማ፣ አስራ አንዱ ጥይት ለሞቱት አስራ አንድ አትሌቶች በቀል መሆኑ ነው::

ሞሳድ የአትሌቶቹን ግድያ ያቀነባበሩና እጃቸው አለበት ያላቸውን ግለሰቦች በአውሮፓ ብቻ ሳይሆን የእሥራኤል ጠላት በሆኑ አረብ አገራት ጭምር አነፍንፎ የበቀል ብትሩን ሳያሳርፍባቸው አላረፈም:: ሞሳድ በዚህ የበቀል ተልዕኮው በስህተትም ይሁን ሆን ብሎ በሚያስቀምጣቸው ፈንጂዎች የንፁሃንን ሕይወት መቅጠፉ በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ውግዘት ቢያስከትልበትም ርምጃውን ለጊዜው ገታ እንጂ ሙሉ በሙሉ ወደ ኋላ አላለም:: በ1966 ጎልዳሜር በጡረታ ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ቢገለሉም እሳቸውን ተክተው ወደ ስልጣን የመጡ ሰዎች የጀመሩትን የበቀል ርምጃ አስቀጥለዋል:: ጎልዳሜር ጡረታ ከወጡ ከአራት ዓመታት በኋላ ሕይወታቸው አለፈ:: ሕይወታቸው ካለፈ ከስምንት ወራት በኋላም የበቀል ርምጃው በስኬት ተጠናቀቀ::

በሙኒኩ ኦሊምፒክ ትራጄዲ በሕይወት ከተረፉ ሦስት አጋቾችም ሁለቱን ሞሳድ የገቡበት ገብቶ ገድሏቸዋል:: በሕይወት የተረፈው አንዱ ብቻ ገዳይ ሲሆን፤ እሱም ተደብቆ እንደሚኖር ከሰላሳ ዓመታት በኋላ በሰጠው ቃለመጠይቅ ተናግሯል:: ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በሙኒክ ኦሊምፒክ የተፈጠረውን ትራጄዲ ሁሉም እንደመሰለው ተርጉሞታል:: አንዳንዶች ድርጊቱን አረመኔያዊ አስተሳሰብ የወለደው ሽብርና ዘግናኝ ክትተት አድርጎ አውግዞታል:: ፍልስጤማውያን ደግሞ ትግላቸውን ለዓለም ሕዝብ ያስተዋወቁበትና ቀድሞ ከነበራቸው ደረጃ ከፍ ያሉበት ርምጃ አድርገው ያወድሱታል:: እሥራኤል በበኩሏ ድርጊቱ የጠላቶቿን አሸባሪነት ያረጋገጠ ከመሆኑ ባሻገር ራሷን መጠበቅ እንደምትችልና ክንደ ረጅም መሆኗን ያሳየችበት አጋጣሚ አድርጋ ትቆጥረዋለች:: እውነታው ምንም ይሁን ምን በሙኒክ ኦሊምፒክ የደረሰው አደጋ ኦሊምፒክ መሠረት አድርጎ የተነሳበትን የአንድነትና የወዳጅነት ስሜት በእጅጉ የሸረሸረ ጥቁር ጠባሳ መሆኑን መካድ አይቻልም::

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2013 ዓ.ም


Leave a Reply

%d bloggers like this: