የጎንደር ከተማን በተለያዩ አቅጣጫዎች ለማጥቃት ተኩስ ከፍተው የነበሩ ታጣቂዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መመለሳቸውን የጎንደር ከተማ ወጣቶችና የከተማ አስተዳደሩ ዐስታወቁ።

ታጣቂዎቹ ከትናንት በስትያና ትናንት የጎንደር ከተማን የሽብር ማዕከል ለማድረግ በሦስት አቅጣጫዎች ተኩስ ከፍተው ጉዳት ማድረሳቸውን በጎንደር የአማራ ወጣቶች ማኅበር ፕሬዚደንት ተስፋ ታምራት ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል። «ጎንደርን የሽብር ቀጠና ለማድረግ ሥራ ተሠርቶ ነበር። ድንበር አካባቢ ሰው በማገት እየተደራደሩ ገንዘብ ሲቀበሉ ቆዩ።

አሁን ደግሞ በሕዝብ ላይ ግልጽ የኾነ ጦርነት ከፍተው በአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሺያ እንዲሁም የአካባቢው የፀጥታ ኃይል ሕልማቸው አልተሳካላቸውም። አሁን ዛሬ ነው፤ ጥሩ ሠላም ነው።»የጎንደር ከተማ የሰላምና ደህንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ናትናኤል ጎሹ በበኩላቸው በስም ያልጠቀሷቸውና «የተደራጁ ቡድኖች» ያሏቸው ኃይሎች በሦስት የጎንደር ከተማ አቅጣጫዎች ጥቃት ከፍተው በመንግሥት ታጣቂዎች መመለሳቸውን አብራርተዋል።

«አንደኛው ቁስቋም ይባላል፣ አንዱ ብላጅግ ዳብርቃ ነው፣ ሌላኛው ደግሞ አዘዞ ሳይድ (አቅጣጫ)፣ በእነዚህ ሦስቱ ቦታዎች፣ ያው ቁስቋም ትንሽ ጠንከር ያለ ነበር። በርከት ያለ የጥፋት ኃይል ገብቶ ከተማውን የማጥቃት ፍላጎት ነበረው። ይህን ያህል ሕይወት ጠፋና ይህን ያህል ቆሰለ ምናምን እንደዚህ የምጠቅሰው ነገር አይኖረኝም፣ ግን የተቃጠሉ ቤቶች አሉ ዳር ወጣ ወጣ ብለው ያሉ።

ድርጊቱን የፈፀመውን ሰው በክትትል አንዳንዶቹን በቁጥጥር ስር አውለናል፤ ክትትል እያደረግን ነው።»በነበረው የተኩስ ልውውጥ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰና የታጣቂዎችን ማንነት በተመለከተ ዶይቼ ቬለ የጠየቃቸው አቶ ናትናኤል «በጥናት ይመለሳል» የሚል ጥቅል ምላሽ ሰጥተዋል። አሁን የጎንደር ከተማና አካባቢው ሰላም እንደሆነ መምሪያ ኃላፊው ማመልከታቸውን የባሕርዳሩ ወኪላችን ዓለምነው መኮንን የላከልን ዜና ይጠቁማል።

DW Amharic


Leave a Reply