በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ የአሜሪካ ዶላር ፣ ዩሮና የእንግሊዝ ፓውንድ ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ዋለ


የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በቅንጅት ባደረጉት ክትትል የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-A 39178 አ.አ የሆነ የጭነት ተሽከርካሪ ጤፍ ጭኖ ከአዲስ አበባ ወደ ሞያሌ ሲጓዝ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በተሽከርካሪው ላይ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እየተካሄደ ስለመሆኑ በተገኘው መረጃ መሰረት ክትትል ሊደረግበት መቻሉን ያስታወሰው ኮሚሽኑ ግንቦት 16 ቀን 2013 ዓ/ም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ቱሉዲምቱ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አሽከርካሪው ከነረዳቱ ተይዞ በተሽከርካሪው የተለያየ አካል ላይ በተደረገ ብርበራ በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 209 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ 156ሺህ 160 ዩሮ እና 24ሺህ 670 የእንግሊዝ ፓውንድ በላስቲክ ተጠቅልሎ መገኘቱን ገልጿል፡፡

በሌላ ዜና በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በአንድ የእንግዳ ማረፊያ ክፍል ተከራይተው ሀሰተኛ የኢትዮጵ ብር እና የውጪ ሃገራት የገንዘብ ኖቶችን ሲያትሙ የነበሩ ሁለት የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቅንጅት ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ/ም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በተከራዩት ክፍል ውስጥ በተደረገ ብርበራ ከ81 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ብር፣ 330 የአሜሪካ ዶላር እንዲሁም የተለያዩ ሃገራት ገንዘቦች ተገኝተዋል፡፡ በተጨማሪም በሃሰት የተዘጋጀ የኢትዮጵያ ብር እና ሃሰተኛ የተለያዩ ሃገራት የገንዘብ ኖቶች ተጠርጣሪዎቹ ሃሰተኛ ገንዘቡን ለማተም ከሚጠቀሙባቸው የተለያዩ ቁሳቁሶች ፣ ቀለሞች እና ኬሚካሎች ጋር በኤግዚቢትነት መያዛቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ የብር ኖት ቅያሪ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ በህጋዊ የሀገሪቱ ገንዘቦች ላይ በተለያዩ ጊዜያት ልዩ ልዩ ወንጀሎች ሲፈፀሙ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
ወንጀል ፈፃሚዎች የተለያዩ የወንጀል ስልቶችን ተጠቅመው በህጋዊ ገንዘቦች ላይ ህገ-ወጥ ተግባር ቢፈፅሙም በህብረተሰቡ መረጃ ሰጪነትና በፀጥታ ሃይሎች የተቀናጀ ክትትል በቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሚገኙ ነው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያስታወሰው፡፡ via EBC

Leave a Reply