ብሔራዊ መግባባት እንዲኖር በትኩረት እንደሚሰራ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አስታወቀ።

ፓርቲው 6ኛውን አገራዊና ክልላዊ ምርጫ አስመልክቶ ያዘጋጀውን ማኒፌስቶ በባህር ዳርና አካባቢው ለሚገኙ ደጋፊዎቹ ዛሬ አስተዋውቋል።

የፓርቲው ከፍተኛ አመራርና የባህር ዳር ከተማን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእጩነት የቀረቡት ዶክተር ደሣለኝ ጫኔ እንደገለጹት ፓርቲያቸው ብሔራዊ መግባባት እንዲኖር በትኩረት ይሰራል።

“አብን እንደ ሀገር እየገጠሙ ያሉ ችግሮች በብሔራዊ ውይይቶችና ድርድሮች መፈታት እንደሚችሉ ያምናል” ያሉት ዶክተር ደሣለኝ በዋናነት የሀገሪቱን ሕገ-መንግስት ከማሻሻል ጀምሮ ብሔራዊ የጋራ ፍላጎቶች ዙሪያ መግባባት እንዲኖር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ባለፉት 30 አመታት በዜጎች ላይ ለተፈጸሙ ጥፋቶች የሽግግር ፍትህ እንደሚያስፈልግ ፓርቲያቸው እንደሚያምንም አስገንዝበዋል።

“ባለፉት አመታት ዜጎች የተፈጸመባቸው በደል ተለይቶ አጥፊዎች በህግ ፊት ቀርበው በጥፋታቸው ልክ በህግ እንዲቀጡና ለተጎጆች በጥፋታቸው ልክ ተገቢው ካሳ እንዲከፈላቸው አብን አተኩሮ ይሰራል” ነው ያሉት።

“አብን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እኩል የሚቀበሉት ሕገ-መንግስት እንዲኖር አበክሮ ይሰራል” ያሉት ዶክተር ደሣለኝ 15 የሕገ-መንግስቱ አንቀጾች እንዲሻሻሉ አስረጅ ምክንያቶችን በመጥቀስ ለሚመለከተው አካል ማስገባት እንደተቻለ ገልጸዋል።

ፓርቲያቸው አሁን ላይ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ወርዷል ብሎ እንደሚያምን ጠቅሰው “አብን መንግስት ሆኖ ቢመረጥ የውጭ ዲፕሎማሲው በተማረና ወቅቱን በሚዋጁ ዲፕሎማቶች እንዲመራ የማድረግ ስራ ይሰራል” ብለዋል።

“አብን ያልጨነገፈና ጤናማ ሥርአታዊ ለውጥ እንዲፈጠር ይሰራል” ያሉት ደግሞ የፓርቲው የውጭ ግንኙነት ሃላፊና የአብንና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ጥምረት ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ቴወድሮስ ሃይለማሪያም ናቸው።

የሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ከጥሬ የስልጣን ግብግብ፣ ከፓርቲ መስመርና ጥቅም የላቀ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ፈተናዎችን ለማለፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

“ብሔራዊ መግባባት፣ዘላቂ ሰላም፣ ፍትህና እኩልነት የሰፈነባት ሀገርና ዴሞክራሲያዊ ስርአት እንዲፈጠር የሚያስችል አሰራር እንዲዘረጋ ለማስቻል ይሰራል” በማለት ጠቅሰዋል።

“አብንና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የጀመሩትን አስተማሪ በሆነ መንገድ በጋራ የመስራት ጥምረት ተመሳሳይ አዎንታዊ ሃሳብ ያላቸውን ሀይሎች በማሰባሰብ ሀገርን የማዳን ተልዕኮ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉም አስታውቀዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የባህር ዳርና አካባቢው ደጋፊዎች ተገኝተዋል። – (ኢዜአ)

Leave a Reply

Previous post Why China is taking a low profile on Ethiopia’s Tigray conflict
Next post የተጠርጣሪዎችን መብት በጠበቀ መልኩ ምርመራ ለማካሄድ የሚያስችል የሪፎርም ስራ ተከናውኗል … ወንጀል ምርመራ ቢሮ
%d bloggers like this: