ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በደብሊው ኤ ኢንደስትሪያል የምግብ ዘይት ኮምፕሌክስ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ከተናገሩት የተወሰዱ አንኳር ነጥቦች:-
• አንድነታችን እንደዘመኑ ጀግንነት በብልጽግና ላይ መደገም እንዲችል ምክንያት ፌስቡክ ነው፣ ዩቲዩብ ነው፣ እያልን በረባው ባልረባው እንዳንጋጭ አደራ ልላችሁ እፈልጋለሁ።
• የፋብሪካው ባለቤት ከሰራው ፋብሪካ በላይ ያለውን ለማካፈል ባለው ፍላጎት ምስጋና ይገበዋል፤ ይህ ልባም ባለጸጋ መስራት ብቻ ሳይሆን መካፈልን አስተምሯል።
• አትዮጵያ ሶስት ወሳኝ ምሰሶዎች አሏት፤የመጀመሪያው ምሶሶያችን ፈጣሪ ነው፣ ሁለተኛው ኢትዮጵያን ለማልማት ወደኋላ የማይለው የኢትዮጵያ ህዝብ ሲሆን ሶስተኛው በፈጣሪ የተሰጠን አንጡራ ሀብታችን ነው።
• እነዚህ ሀብቶች ማልማት የሚችል ህዝብ ልበ ብርሃን የሆነ ህዝብ እና ፈጣሪውን የሚፈራ ህዝብ ስንሆን ኢትዮጵያ የሚገዛትም የሚያስቆማትም ኃይል በምድር ላይ አይኖርም።
• የእኛ የኢትዮጵያዊያን ዋና አደጋ የፈጠረንን አምላክ አላማውን ስተን መጣላት ስንጀምር የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት ሲያጣ ፣ የኢትዮጵያ ሀብት እና ጸጋዎች ማልማት ሲሳነን የሌሎች መሳለቂያ እንሆናለን።
• ኢትዮጵያዊያን ፈጣሪ እንዳለን እና አንድ መሆን እንዳለብን እንዲሁም ተዝቆ የማያልቅ ሀብት እንዳለን ከተገነዘብን ግን ለዓለም ምሳሌ እንሆናለን እንጂ የማንም ሀገር መፈንጪያ አንሆንም።
• አንድነታችንን፣ ፈጣሪያችንን እንዲሁም ሀብታችን ደግሞ እንዲህ አድርጎ የሚያለማ ባለጸጎችን እንዲያበዛልን መትጋት ይኖርብናል።
• ሁለት ልበ ብርሃኖች በሁለት ወር አይተናል፤ ጎጃም ውስጥ ብዙ ሺህ ልበ ብርሃኖች እንዲፈጠሩ እንመኛለን።
• ስንፍናን በማይወዱ ተግተው በሚሰሩ ሀገራቸውን በሚወዱ አሁን አንበሳ መግደል ሳይሆን ኑሮን ማሸነፍ ነው ጀግና የሚያሰኘው ።
• ድሮ ብዙ ሰራዊት አስከትሎ መሸፈት ጀግንነት ነበር፤ አሁን ግን እንደልባሙ በለጸጋ ወርቁ አይተነው ብዙ ሰራተኞችን ቀጥሮ ስራ ማስፋፋት ነው ጀግንነት።
• አባቶቻችን ታሪክ ሰርተው አውርሰውናል፤ እኛም ብልጽግና በማውረስ የሚያኮራ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ስንዴ የማይለምን ትውልድ፣ የማይፈራ ትውልድ እንዲሁም ያሰበውን ማድረግ የሚችል ትውልድ እንድንፈጥር የትብብር መንፈስ ያስፈልጋል ብለዋል።
• ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገር የሚሸልሙ ባለሀብቶች መፍጠር ትችላለች፡፡
• ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔሮች ቋንቋቸው ቢለያይ፣ ታሪካቸው የተለያየ ቢመስል፣ ኢትዮጵያ በምትሰኝ ብልቃጥ ውስጥ አብረን እስካለን ድረስ አንዳችን ለሌላችን መከታ እና ጋሻ እንጂ አንዳችን ለሌላችን ጠላት መሆን አንችልም።
• ከውጭ ኢትዮጵያን እየነቀነቁ ጠላት የመጣ እያስመሰሉ ጎጃም ከኢትዮጵያ ለመለየት የሚጥሩ ኃይሎችን አውቀንባችኋል ብለን በጋራ መቆም እንጂ ጠላት መጣ ብለን መባላት አስፈላጊ አይደለም።
• ኢትዮጵያ መበታተን አልተቻለም፤ አይቻልምም። ኢትዮጵያን የሚበታትኑትን በታትነናቸዋል፤ ወደፊትም እንበትናቸዋለን።
• በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ሌሎች ነጋሪ መስካሪ መሆን አይችሉም፡፡