በትግራይ ትምህርት ተጀምሯል፤ ተማሪዎች የናፈቁትን አግኝተዋል


“ትምህርት ተቋርጦ በነበረበት ጊዜ በጣም አዝኛለሁ፤ ከትምህርት ውጪ በቤት ውስጥ የነበረኝ ቆይታም ጥሩ አልነበረም፤ አሁን ትምህርት በመጀመሬ ደስተኛ ነኝ፤ ያለፉትን ጊዜያት ለማካካስም እየጣርኩ ነኝ፤ በቀጣይም የተሻለ የትምህርት ጊዜ እንደሚኖረን ተስፋ አደርጋለሁ፤ በመሆኑም ጓደኞቼ ወደ ትምህርትቤታችሁ ኑና አብረን እንማር፤ አገራችንንም እናድን፤” የምትለው፤ ከወራት ከትምህርት ዓለም ተለይታ ዳግም ወደ ትምህርት ገበታዋ የተመለሰችው በመቐለ ፈለገ ሕይወት ሙሉ ሳይክል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ተማሪዋ ፊላሪ በረከት ናት፡፡

ተማሪ ፊላሪ እና ሌሎች በትግራይ ክልል የሚገኙ ተማሪዎች፣ የአሸባሪው ህወሓት ቡድን የፈጸመውን የአገር ክህደት ተግባር ተከትሎ በተወሰደ የህግ ማስከበር እርምጃ በክልሉ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ወራት ተቆጥረዋል፡፡

አሁን ግን በተፈጠረ ሰላም ትምህርት ቤቶች ወደማስተማር ስራቸው በመግባት ላይ ይገኛሉ፡፡ በመቐለ ከተማ ያለው ሁኔታም ይሄንኑ የሚያሳይ ነው። ከትናንት ጀምሮ ተማሪዎች በየትምህርት ቤቶቻቸው መገኘት ጀምረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎች ምልከታ ካደረጉባቸው በመቐለ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል፤ የአፄ ዮሃንስ እና የፈለገ ህይወት ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል፡፡

ከትምህርት ቤት ርቃ በቤት ውስጥ ያሳለፈችው ጊዜ ብዙም ደስ የማይል እንደነበር የምትናገረው ተማሪ ፊላሪ፤ ትምህር የሚጀመርበትና ወደ ትምህርት ቤት የምትመለስበት ጊዜ በእጅጉ ያስጨንቃት እንደነበር ትገልጻለች፡፡

አሁን ግን ትምህርት በመጀመሯ ደስተኛ መሆኗን በመጠቆም፤ “ጓደኞቼ እባካችሁ ወደ ትምህርትቤታችሁ ኑና አብረን እንማር፤ አገራችንንም እናድን” ብላለች፡፡

ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኳቸው የመከረችው ተማሪ ፊላሪ፤ ለዚህ ደግሞ ተማሪዎች እርስ በእርሳቸው እየተነጋገሩ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመጡ ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ የመምህራን፣ የወላጆች፣ የመንግስት አካላት ድርሻና እገዛ እጅጉን አስፈላጊ መሆኑን ትገልጻለች፡፡ ይሄን አውቀውም ሁሉም የሚጠበቅበትን እንዲያደርግ ጠይቃለች፡፡

በዚሁ ትምህርት ቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ተማሪ ሮቤል ላዕከ በበኩሉ፤ ከወራት ከትምህርት ገበታ መራቅ በኋላ ዛሬ ላይ ወደትምህርት ቤት በመመለሱ እጅጉን መደሰቱን ይናገራል፡፡

ዳግም ትምህርት ተከፍቶ ለመማር ወደትምህርት ቤት በመጣበት ወቅትም ብዙ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ባይመጡም፤ ለመማር ትምህርት ቤት የተገኙ ተማሪዎች ግን በመምህራኖቻቸው አማካኝነት የቀደመ ትምህርታቸውን እንዲከልሱ እየተደረገላቸው እንደሆነ ይገልጻል፡፡

በቀጣይ ቀናትና ሳምንታት ግን ከዚህ በላቀ መልኩ ተማሪዎችም ተገኝተው፤ ትምህርታቸውንም በምላት እንደሚማሩ ያለውን እምነትም አስቀምጧል፡፡

ለዚህ ደግሞ ትምህርት መጀመሩን አውቀው ሁሉም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ እና በመማራቸው መልካም የሆነውን እውቀትን ከማግኘት የዘለለ ሊያስፈራቸው የሚገባ ጉዳይ አለመኖሩን የሚናገረው ተማሪ ሮቤል፤ “ትምህርት መማር ለእኔ ሁሉም ነገሬ ነው፤ ትምህርት ለእኔ እውቀት ማግኛዬና ሁሉንም ስራ በአቅሜ እንድሰራ እድል የማገኝበት፤ ሁሌም የተሻለ ኑሮ እንድኖር የሚያግዘኝ ነው፤” ይላል፡፡

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር አስቴር ይትባረክ እንደሚሉት፤ አሁን ላይ የመማር ማስተማር ስራው ተጠናክሮ መጀመር ስላለበት በዚህ ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ከማድረግ ባሻገር ለትምህርት የሚያስፈልጉ የደብተርና እስክሪብቶ አይነት ቁሳቁሶችም በየትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች እንዲደርስ እየተደረገ ሲሆን፤ ተማሪዎችም ወደትምህርት ቤቶች በመሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡

በዚህ ረገድ ከመቐሌ ባለፈ፣ ከመቀሌ ውጪ ባሉ ወረዳዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ቀደም ብለው ከሁለት ሳምንት በፊት ትምህርት የጀመሩ መኖራቸውን የጠቆሙት ኢንጂነር አስቴር፤ ሆኖም የኖረ ልምድ ሆኖ ትምህርት ሲጀመር የተማሪዎች መንጠባጠብ እንደሚስተዋል አመልክተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ሳምንት ጠንካራ የቅስቀሳና የማነሳሳት ስራ በመስራት ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ሙሉ የመማር ማስተማር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ በየትምህርት ቤቶች የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎችም ቢሆኑ ሲመጡ አነሱ ተብሎ የሚተዉ ሳይሆን መምህራን በቦታው ተገኝተው ትምህርት መስጠት እንዳለባቸው ያመለከቱት ኢንጂነር አስቴር፤ ተማሪዎችም ለወራት ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መሆናቸው ከሚፈጥርባቸው ተጽዕኖ ባለፈ ወላጆችም ስጋት ሊኖርባቸው ስለሚችል ይሄን ታሳቢ ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጥና ቅስቀሳ ስራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡

በወንድወሰን ሽመልስ (መቀለ)

(ኢ ፕ ድ)

Leave a Reply

%d bloggers like this: